የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ክርስቶፎር ላንዳው እና በአፍሪቃ የአሜሪካ ጦር ዕዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን በኢትዮጵያ አየር ኃይል የአቪዬሽን 90ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኙ።
ኢትዮጵያ እና ግብጽን ጨምሮ አራት የአፍሪቃ ሃገራትን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ባለስልጣናቱ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ላንዳው በአየር ኃይል ኤክስፖ የመዝጊያ ስነስረዓት ላይ ባደርጉት ንግግር በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል የነበረው ግንኙነት «ተጠናክሮ እንደሚቀጥል » ተናግረዋል። ከእርሳቸው ጋር ቢሾፍቱ የተገኙት የአፍሪቃ ዕዝ አዛዡ ጄነራል አንድረሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ያላትን ሚና አስታውሰው ይህንኑ በጋራ አጠናክረን እንሰራለን ብለዋል። ሁለቱ ሁነኛ ባለስልጣናት ወደ አፍሪቃ መጓዛቸው በተለይ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴው ግድብ ላይ ግብጽ እና ኢትዮጵያን የማሸማገል ብርቱ ፍላጎት እንዳላቸው ማሳወቃቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ የምስረታ በዓሉን በማስመልከት ለአራት ቀናት የቆየ ከተለያዩ «ወዳጅ» ሃገራት የተሳተፉበት የአየር ኃይል ትርኢት ሲያሳዩ ቆይተዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቤርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ባዘጋጀው የመራጮች እና የዕጩዎች ምዝገባ ሥርዓት ላይ "የዕጩዎች የኢ-ሜል አድራሻ አስገዳጅ መሆን እንደሌለበት በመታሙኑ በአማራጭ እንዲሞላ መደረጉን" ገለፀ።
ቦርዱ ይህንን ያለው ስምንት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው "ግልጽነት በጎደለውና የተድበሰበሰ" ባሉት የምዝገባ አሠራርና ሂደት "አሳታፊ፣ ሐቀኛ፣ ተዓማኒ እና ዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም" ሲሉ የዕጩዎችን የምዝገባ ሥርዓት ነቅፈው ላወጡት መግለጫ በሰጠው ምላሽ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ እንዳሉት ግን ሥርዓቱ ለሥራ ቅልጥፍና ወሳኝ ነው።
በሌላ በኩል ቦርዱ ዕጩዎች የልደት የምስክር ወረቀትን በተመለለተ "በሕግም ሆነ በአሠራር ያልተጠየቀን እንደተጠየቀ በማስመሰል" መግለጫ ማውጣታቸው አግባብነት የሌለው ቅሬታ መሆኑን ጠቅሶ፤ "የሚያደናግር መመጃ አሰራጭተዋል" ሲል የፓርቲዎቹን መግለጫ አጣጥሏል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ለሁለት ሰዎች ህልፈት እና 1800 ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ያዋላቸው 22 ሰዎች ምርመራ አጠናቆ ለዓቃቤ ህግ መላኩን አስታወቀ።
ፖሊስ ዛሬ በይፋዊ የማህበራዊ መገናኛ ገጹ ባጋራው መረጃ ተጠርጣዎቹ ለ15 ሰዎች መሰወር ምክንያትም ናቸው ብሏል።
ፖሊስ በምርመራው ተጠርጣሪዎቹ «በሰዉ ልጅ ለመነገድ በማሰብ የወንጀል ቡድን በማደራጀት እና የቡድኑ አመራርና አባላት በመሆን በወንጀል» ድርጊቱ ላይ መሳተፋቸዉን አረጋግጫለሁ ብሏል።
በወንጀል መረቡ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 15 ሰዎች ደግሞ እስካሁን የት እንደደረሱ አልታወቀም ነው የተባለው ። በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ ከ2.1 ቢሊዮን ብር በላይ ከተጎጂ ቤተሰቦች መቀበላቸውን ፖሊስ በምርመራ ደርሼበታለሁ ብሏል።
የህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ በማታለል መረባቸው የገቡላቸውን ሰዎች የሚያጓጉዙ ተቀጣሪዎችን በማዘጋጀት ከሱዳን እስከ ሊቢያ ድረስ ያጓጉዟቸው እንደነበር ተመልክቷል። በሊቢያ ከሚገኙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆኑንም ተጎጂዎች በህይወት መቆየት ብቻ የሚያስችል ምግብ በመስጠት በርካቶችን ለስቅየት እየዳረጉ ቪዲዮ በመቅረጽ ከቤተሰባቸው ቤዛ ለመቀበል ተጠቅመዋል ነው የተባለው።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ በስማቸው የተመዘገበ ቤት ተሽከርካሪ እና ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ ተቆጣሪ ገንዘብ በባንክ ሂሳባቸው ላይ መገኘቱን ፖሊስ ገልጿል።
በስደተኞች ላይ ከፍተኛ ስቅየት የታከለበት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተከሰሰው ኤርትራዊ ዛሬ ኔዘርላንድስ ውስጥ በዋለ ችሎት 20 ዓመት ተፈረደበት።
አማኑኤል የተባለው ኤርትራዊ መነሻውን ከኤርትራ አድርጎ በሊቢያ በኩል ወደ አውሮጳ የሚደረግ "እጅግ አስከፊ የሆነ የሰዎች ዝውውር" የሚያካሂድ ቡድን መሪ እንደነበር የደች ዐቃቢያነ ህግ አስታዉቀዋል።
ቡድኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ሊቢያ ውስጥ በሚገኙ እጅግ በተጨናነቁ እና በቆሸሹ ማጎሪያዎች ውስጥ በማቆየት ከቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ይቀበሉ እንደነበር ተገልጿል።
የሀገሪቱ ዓቃቢያነ ህግ በግልሰቡ ላይ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ፣ ገንዘብ በመቀበል ፣ በእገታ እና የጾታዊ ጥቃት ወንጀሎች የመፈጸም ዓላማ ያለውን የወንጀል ድርጅት በመምራት ከሰውታል። ይህንኑ ተከትሎ በትንሹ የሃያ ዓመት እስራት እንዲፈረድበት ጠይቀው ይኸው ተፈጻሚ ሆኗል።
ተከሳሹ የቀረቡበትን ክሶች ከመካድ ውጭ ተጨማሪ አስተያየት እንዳልሰጠ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የሱዳን ብሔራዊ ጦር የፈጥኖ ደራሹ አር ኤስ ኤፍ በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት በምትገኘው የዲሊንግ ከተማ ላይ የነበረውን ከበባ መስበሩን አስታወቀ።
የብሔራዊ ጦር ተቀዳጀሁ ያለው ድል ከተረጋገጠ ወደ ከተማዋ የሚወስዱ ሁሉንም አውራ ጎዳናዎች ለመቆጣጠር ያስችለዋል ።
ብሔራዊ ጦሩ ትናንት ሰኞ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ በፈጥኖ ደራሹ ኃይል የነበረው ከበባ «በጠላት ኃይል ላይ ከባድ ኪሳራ » በማድረስ ወደ ከተማዋ የሚወስደውን መንገድ ከፍቻለሁ ፤ ብሏል። ለረዥም ጊዜ በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ከበባ ስር የነበረችው የዲሊንግ ከተማ በካዱግሊ እና በሰሜን ኮርዶፋን ማዕከል በሆነችው የኤል ኦቤይድ ከተማ አማካይ ስፍራ ላይ የምትገኝ እና ስልታዊ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላት ከተማ ናት ። በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ሲንሸራሸሩ የነበሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የብሔራዊ ጦሩ ወታደሮች በክፍት ተሽከርካሪዎች ላይ ሆነው በከተማዋ ውስጥ ደስታቸውን ሲገልጹ ያሳያሉ ። ይሁንና የዜና ወኪሉ የቪዲዮዎች ትክክለኛነት ገና አላረጋገጠም።
የስፔን ግራ ዘመም መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ያለ መኖሪያ ፍቃድ የሚኖሩ ግማሽ ሚሊዮን ስደተኞችን ህጋዊ የሚያደርግ አዲስ አዋጅ ዛሬ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የሀገሪቱ የስደት ሚኒስትር ኤልማ ሳይዝ እንዳሉት ዉሳኔው ስደተኞች በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል በነጻነት እንዲሰሩ ዕድል ይሰጣቸዋል፤ ይህም ስፔን ለስደተኞች ያላትን አዎንታዊ አመለካከት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የህግ ማሻሻያው እስከ የተጠናቀቀው የጎርጎርሳዉያኑ 2025 ድረስ ጥገኝነት የጠየቁ እና ቢያንስ ለአምስት ወራት ስፔን ዉስጥ የቆዩ ስደተኞችን የሚመለከት ይሆናል። የሀገሪቱ መንግስት ከሚቀጥለው ሚያዝያ ወር ጀምሮ የስደተኞቹን ማመልከቻ መቀበል እንደሚጀምርም ነው የተገለጸው።
አዲሱ የስፔን ውሳኔ፣ በርካታ የአውሮጳ ሀገራት በስደተኞች ላይ ጠንካራ ህግ እያወጡ ባሉበት ወቅት መሰማቱ የተለየ ዉሳኔ ተብሎለታል።
በኢራን የተቀሰቀሰውን አገር አቀፍ ተቃውሞ ለመግታት መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ የሟቾች ቁጥር ከ6 ሺህ በላይ መሻገሩ ተሰማ።
አሜሪካ በበኩሏ በእስያ ባህር ላይ የነበረውን ግዙፉን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አስጠግታለች።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዳሉት በኢራን በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ዓመጽ ምክንያት ኢንተርኔት ተዘግቶ በነበረበት ወቅት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 6,126 መድረሱን አመልክተዋል።
ከሟቾቹ መካከል 86 ህፃናት እንደሚገኙበትና ከ41 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ለእስር መዳረጋቸው ተገልጿል።
የኢራን መንግስት በበኩሉ የሟቾቹን ቁጥር አሳንሶ ከ3100 አይበልጥም ይላል። የተገደሉትም ቢሆኑ "አሸባሪዎች" ናቸው በማለት ነው የገለጻቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ ለሚወሰድ ለማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ ዝግጁ መሆኗን ለማሳየት "ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን" የተሰኘችውን ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አስገብታለች።
የመርከቡን መጠጋት በተመለከተ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቃባይ «አያሳስበንም » በማለት ነበር የገለጹት ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የሚፈጸመው የጅምላ ግድያ እንዲቆም ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። ይህንኑ ተከትሎ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ምናልባትም ጦርነቱ በማንኛውም ሰዓት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ግምትም እያየለ መጥቷል።