ባህላዊ የደን አጠባበቅ ስልት በጌዴኦ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 5 2017አሳሳቢው የደን ይዞታ
ከጎርጎሪዮሳዊው 1990 እስከ 2010 ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ በየዓመቱ 140,900 ሄክታር የደን ሽፋን እንዳጣች መረጃዎች ያመለክታሉ። የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት እንደሚለው በዚህ ጊዜ ውስጥ የወደመው የኢትዮጵያ የደን በአጠቃላይ 2,818,000 ሄክታር ይሆናል። የወደመውን የደን ይዞታ ለመመለስ ሀገሪቱ በየዓመቱ የሚሊየኖች ችግኝ ተከላ መርሐግብር እንደምታካሂድ ይነገራል። የደን ይዞታል ለማሻሻል እንዲህ ያለው የዘመቻ ችግኝ ተከላ አንድ ዘዴ ቢሆንም ኅብረተሰቡ በእራሱ መንገድ የሚያደርገውን የደን ጥበቃ ስልት ግን ይተካል ማለት አይቻልም።
በተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት እንደሚለው ኢትዮጵያ ከ12 ሚሊየን hሄክታር በላይ የደን ሽፋን ነበራት። ከዚህ ውስጥ 511,000 ሄክታር የተተከለ ደን ነበር። ሆኖም ከጎርጎሪዮሳዊው 1990 እስከ 2010 ድረስ የደን ይዞታው ይበልጥ እየተመናመነ ሄዷል።
ወትሮም በአብዛኛው ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የደን ይዞታቸው የተሻለ እንደሆነ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት። በአረንጓዴ ከተሸፈኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ በደቡባዊ ኢትዮጵያ የሚገኘው አካባቢ የጌዴኦ ማኅበረሰብ መኖሪያ ስፍራ ነው። አረንጓዴ ለመልበሱ ደግሞ የጌዴኦ ማኅበረሰብ የሚከተለው ባህላዊ የደን መጠበቂያ ስልት በዋናነት ይጠቀሳል።
ሰሞኑን አካባቢውን የጎበኘው የሀዋሳው ዘጋቢያችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ስለተመለከተው የደን ይዞታና የኅብረተሰቡ አኗኗር ገልጾልናል።
ኅብረተሰቡ ለእርሻ ሥራ በሚል ደኑን ባለመመንጠሩም ከደኑ ዘርፈ ብዙ በረከት እየተቋደሰ ነው። ከእርሻው ምርት ጎን ለጎን ንብ በማናባት፤ ከብቶችንም በማርባት ኑሮውን ይደጉማል። በሌላ አካባቢ እንደሚታየው ምግብ ለሥራ ወይም ሴፍቲኔት የሚባለው ኅብረተሰቡን ለእርዳታ ምግብ የሚያመቻች አካሄድ እዚህ እንደሌለም ነው ዘጋቢያችን ያስተዋለው።
ሸዋንግዛው ወደ አካባቢው በሄደት አጋጣሚ የጌዴኦ ማኅበረሰብ ባህላዊ መሪዎች በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ ቆንጋ በተባለው መንደር ተገኝተው ነበር። እዚያ የተገኙትም ተፈጥሮን ማልማትና መጠበቅ ተብሎ በሚጠራው ነባር ባህላዊ እሴታቸው መሠረት ከኅብረተሰቡ ጋር ለአካባቢያቸው ይዞታ ለመወያየት ሲሆን፤ ከነዋሪዎቹ ጋር ይመካከራሉ፤ ችግሮች ካሉም በዚያው ይፈታሉ።
የጌዲኦ ማኅበረሰብ ከተፈጥሮ ጋር ያለው መስተጋብር ከሚታወቅባቸው ባህላዊ እሴቶቹ አንዱ መሆኑ ይነገርለታል። ለዚህ ደግሞ በአረንጓዴ በተሸፈነው የአካቢያቸው ገጽታ በተግባር ይገለጻል። በጌዴኦ ማኅበረሰብ ባህል ደን የተከበረ እና እንደሰው ሕይወት የሚጠበቅ ነው ይላሉ ከባህላዊ መሪዎች አንዱ የሆኑት አለማየሁ በቀለ።
«እንደ ጌዲዮ ባህል ደኑ የተከበረ ነው፤ እንደ ሰው ሕይወት ነው የሚጠበቀው። አንድ ዛፍ ያለፈቃድ የሚጥል እና የሚቆርጥ የለም። ከቆረጠ ሥርዓት አለ፤ ይህን ሥርዓት የተላለፈ ሰው የእኛ የጌዴኦ ባህል ሰንጎ አለ በሰንጎ ይቀመጡና እከሌ ያለ ሥርዓት ደን ጥሏል፤ ማሳ ገላጣ አድርጓል፤ ምድሪቱ ላይ ረሀብ እንዲመጣ አድርጓል፤ መልሶም አልተከለም ብለው ለሽማግሌዎች ሄደው ከነገሩ በኋላ ያ ሰው ተጠርቶ ይመከራል።»
ባህላዊ መሪዎቹን ሳያማክር ደን የመነጠረም ሆነ ዛፍ የቆረጠ በዋዛ የሚታለፍ አይሆንም ማኅበራዊ ቅጣት ይከተለዋል። ቅጣቱ ምን ይሆን? ባህላዊ መሪው ይናገራሉ።
የጌዴኦው አርሶ አደርና ደን
የጌዴኦ ማኅበረሰብ ከተፈጥሮ ጋር ያለው መስተጋብር ትኩረትን የሚስብ ነው። በጌዴኦ ዞን የቆንጋ መንደር ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደሩ ይታገሱ ተስፋዬ ከቤተባቸው አባላት ጋር በመሆን ነው የእርሻ ሥራቸውን የሚያከናውኑት። ኑሯቸውን በደኑ መሀል ያደረጉት አርሶ አደር ይታገሱ በደኑ ውስጥ ቡና፤ እንሰት፣ እንዲሁም ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎችን ያመርታሉ። እንዲህ ያለውን በረከት ለማፈስ ያበቃቸው ኅብረተሰቡ ለዘመናት ደኑን ለመጠበቅ ሲከተል የኖረው ባህላዊ ሥርዓቱ ነው ባይ ናቸው።
የጌዶኦ አካባቢ ደን ለመጠበቁ ዋነኛ ምክንያት ስለሆነው ባህላዊ ሥርዓት አካባቢውን የተመለከተው ባልደረባችን ሸዋንግዛው በበኩሉ ጠይቆ እንደተረዳው በባህላዊ አጠራር የባቡ ሥርዓት የሚሉት ዋነኛ ስልት ነው።
ባህላዊው የደን መጠበቂያ ስልት
ሸዋንግዛው በቅርበት ካስተዋለው ተነስቶ ደን ለጌዴኦ ማኅበረሰብ ሁሉም ነገሩ ነው ማለት ይቻል ነው የሚለው። ኅብረተሰቡ ምግቡንም ሆነ ለገባ ሽያጭ የሚያቀርበውን ምርቶቹን የሚያገኘው ከዚሁ ከደን ሀብቱ እንደሆነም ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅት የአየሩ ጠባይ በመላው ዓለም መለወጡ እየታየ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ለፀሐይ ማቃጠልም ሆነ ለአየር ጠባዩ መለወጥየደን መመናመንጉልህ ሚና ሊኖረው እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይገምታሉ። ጌዲኦ ላይ የማኅበረሰቡ ተፈጥሮን በባህላዊ መንገድ የሚጠብቅበት ሥርዓት አካባቢው ሚዛኑን ጠብቆ መዝለቅ እንዲችል የረዳው ይመስላል። በጌዲኦ ዞን ግብርና መምሪያ የጥምር ደን ግብርና አስተዳደር ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ኢሳያስ አበበ የጌዴኦ ማኅበረሰብ የጥምር ደን ግብርና እሴት ለብዙ ሺህ ዓመታት በትውልድ ቅብብሎሽ መዝለቁን ይናገራሉ።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ባህላዊው የጌድኦ ማኅበረሰብ ጥምር የደን ግብርና
ኅብረሰተቡ ይህን የደን አጠባበቅ ስልትከወላጆቹ መማሩን በይፋ እንደሚገልጽ ነው አቶ ኢሳያስ የገለጹት። እንዲህ ከሚንከባከበው ደንም ከእራሱ ፍጆታ አልፎ በኤኮኖሚም እየተጠቀመበት እንደሆነም አመልክተዋል። የጌዴኦ የጥምር ደን ግብርና በተባበሩት መንግሥታት የትምህርትና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ ባለፈው ዓመት ጥር ወር በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ይህን ዕውቅና ያገኘው ደግሞ ማኅበረሰቡ ደኑ ውስጥ እየኖረ ሳለ ባለው ነባር የደን አጠባበቅ ሥርዓት ደኑን በማራቆት ተፈጥሮን ሳይጎዳ በግብርና ሥራ ሕይወቱን መምራት በመቻሉ ነው።
በ2007 ዓም በተደረገ ብሔራዊ የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሠረት የጌዴኦ ሕዝብ ቁጥር አንድ ሚሊየን ይጠጋል። በአንድ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ከ728 እስከ 1,200 ሰዎች ይኖራሉ። ይህም አካባቢውም ከፍተኛ የሕዝብ መጠጋጋት ካለባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ቀዳሚ እንደሚያደርገው ይነገራል። እንዲያም ሆኖ ግን ኅብረተሰቡ የደን ሀብቱን ጠብቆ ከእሱም ሲሳዩን እያገኘ በበረከት ይኖርበታል። የጌዴኦ ማኅበረሰብን ባህላዊ የደን አጠባበቅ ሥርዓት በቅርብ ተመልክቶ መረጃውን ያጋራንን የሀዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁንና የተባበሩትን ሁሉ እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ