1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማገዶ ፍጆታ የደንን ሀብት ከሚያመናምኑ ርምጃዎች ዋነኛዉ ነዉ፤

ማክሰኞ፣ የካቲት 21 2009

ከሱዳን የሚሰደዱ ወገኖች በርክተዉ በሚገኙበት በጋምቤላ ክልል የተመናመነዉን የደን ይዞታ ለማገዝ ያለመ አንድ ዕቅድ መነደፉን የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅፍ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ FAO ከጥቂት ሳምንታት በፊት ይፋ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/2YOeY
Äthiopien, Massaker in der Region Gambela
ምስል DW/Y. Gebregziabeher

ደን የሚያራቁተዉ የማገዶ ፍጆታ

 

 እንደ FAO ዕቅድ ከሆነም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሱዳን ስደተኞች ለማገዶ ፍጆታ የሚያዉሉትን ዛፍ ከስር ከስር ለመተካት በ150 ሄክታር መሬት ላይ ወደ አንድ ሚሊየን የሚሆኑ የዛፍ ችግኞችን ለመትከል ታስቧል። FAO እንደሚለዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም አንስቶ ባሉት ጊዜያት ወደ 300 ሺህ የሚሆኑ የእርስ በርስ ጦርነት ያፈናቀላቸዉ የደቡብ ሱዳን ዜጎች በጋምቤላ ክልል ዉስጥ ይገኛሉ። እነዚህ ወገኖች ለምግብ ማብሰያ ሙሉ ለሙሉ የሚጠቀሙት እንጨት በመሆኑ በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኘዉ የደን ይዞታ ላይ አሉታዊ ጫና ማሰደሩን የድርጅቱ የኃይል እና የደን ልማት ባለሙያ አርቱሮ ጃንቬኑቲ ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል። እሳቸዉ እንደሚሉትም በሺዎች የሚገመቱ ሰዎች በአንዲት አነስተኛ አካባቢ በድንገት ሰፍረዉ ለምግብ ማብሰያ ማገዶ መቆራረጥ ሲጀምሩ በአካባቢዉ የተፈጥሮ ይዞታ ላይ ሊከተል የሚችለዉ ተፅዕኖ በቀላሉ እና በአጭር ጊዜ ዉስጥ የሚታይ ነዉ። ከዚህም በተጨማሪ ለቤተሰቦቻቸዉ ምግብ ለማብሰል ማገዶ ፍለጋ ከአካባቢያቸዉ ርቀዉ ለመሄድ የሚገደዱት ሴቶች ለፆታዊ ጥቃት እየተጋለጡ መሆኑንም FAO ይገልጻል። እርግጥ ነዉ ተሰድደዉ ወደ አካባቢዉ የመጡት ወገኖች ብቻ ሳይሆኑ ሀገሬዉም ቢሆን የማገዶ ምንጩ የአካባቢዉ ደን ሆኖ መቆየቱ እና አሁንም መሆኑ የሚታይ እዉነታ ነዉ። በዚህ ምክንያት የስደተኞቹ መጠለያ በሚገኝባቸዉ አካባቢዎች ለሚታየዉ ከፍተኛ የማገዶ ፍላጎት ዘላቂነት ያለዉ የኃይል አቅርቦት እና አማራጭ እንዲኖር ያለመ ጥናት ነዉ FAO በማካሄድ ይህን የዛፍ ተከላ ሃሳብ እንደ አንድ መፍትሄ ያቀረበዉ። ሮም በሚገኘዉ የFAO ዋና ጽሕፈት ቤት ችግሮችን የመቋቋም መርሃ ግብር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሽኩሪ አህመድ የድርጅታቸዉን ዕቅድ ምንነት  ያስረዳሉ።

FAO, Food and Agriculture Organisation of the United Nations, Logo

እሳቸዉ እንደሚሉት FAO ይህን በማሰብ አስቀድሞ ተሰዳጆቹን ጨምሮ ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት በአካባቢዉ የት ምን መደረግ እንዳለበት የሚያመላክት ጥናት ተካሂዷል። በዚህም በቶሎ ለታሰበዉ ዓላማ ሊደርሱ የሚችሉትን እና ለአካባቢዉ የሚስማሙትን የዛፍ አይነቶች የመምረጥ ኃላፊነትም ለባለሙያዎች ተሰጥቷ። እንደታሰበዉ ከሄደም ዕቅዱ ተግባራዊ እንዲሆን የታሰበዉ በመጪዉ የዝናብ ወቅት ማለትም የበልግ ዝናብ ወቅት ነዉ።

 የFAOን የአንድ ሚሊየን ዛፍ ጋምቤላ ዉስጥ የመትከል ዕቅድ በመጥቀስ አስተያየታቸዉን የጠየኳቸዉ የደን ምርምር ባለሙያ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ዕቅዱ የሚደረግፍ እንደሆነ ነዉ የሚናገሩት። በኢትዮጵያ የአካባቢ እና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የአየር ንብረት ሳይንስ የምርምር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር አደፍርስ FAO የነደፈዉ ይህ ፕሮጀክት አስፈላጊነቱ ባያነጋግርም ሊታሰብበት የሚገባ ዋና ጉዳይ ግን አለ ይላሉ።

ቆላማ በሆኑ እና ሰዎች በብዛት በሚሰፍሩባቸዉ አካባቢዎች እንደ ልቅ ግጦሽ፣ የመሬት ርጥበት እጥረት እንዲሁም የድርቅ በተከታታይ መከሰት ወይም የፀሐዩ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ የተተከሉ ችግኞች ዛፍ የመሆን እድላቸዉ መመናመን የደን መራቆትን ሊያባብሱ የሚችሉ ችግሮች መሆናቸዉን የጠቆሙት ዶክተር አደፍርስ፤ ይህ በኢትዮጵያ የደን ሀብት ዘርፍ ዋና እንቅፋት እንደሆነም አብራርተዋል። ዛፍ የመትከል ዕቅድ አሁንም የሚበረታታ መሆኑን ያመለከቱት የደን ምርምር ባለሙያዉ እንዴት እና ምን ዓይነት ክትትል የሚለዉ ጉዳይ ግን ትኩረት እንደሚያሻዉ ያሳስባሉ።

አክለዉም የደን ምርምር ባለሙያዉ የዛፍ ተከላዉ ከመከናወኑ በፊት የሚተከልበት ስፍራ በቅድሚያ መዘጋጀት እንደሚኖርበት፤ መትከያዉን ጉድጓድም አስቀድሞ መቆፈር እንደሚገባ፤ ከተተከለ በኋላም አስፈላጊዉ ክትትል ሊደረግ እንደሚገባም ዘርዝረዋል። ዝግጅቱን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ 

አዜብ ታደሰ