የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት መሰረተልማት ስርቆት ለአደጋ ያሰገዋልን?
ዓርብ፣ መጋቢት 4 2018
ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ባለው ሰበታ አከባቢ በመነሳት ወደ ድሬዳዋ ጅቡቲ በሚያመራው የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡርመስመር መሰረተልማት ላይ በተለያዩ ጊዜያት በደረሱ የስርቆት ወንጀሎች የባቡር አገልግሎቱ እንዳይደናቀፍ በስጋት አስተያየታቸውን የሚያጋሩ በርካቶች ናቸው፡፡ የባቡሩ መነሻ መንገድ በሆነው ሰበታ-ዲማ አከባቢ 20 ሜትር ያህል የባቡሩ ሃዲድ ብሎኖቻቸው ተነቃቅለው በማህበራዊ ሚዲያ በመጋራታቸውም ምናልባት ጉዳዩ ትኩረት በማጣት አደጋን እንዳያስከትል የሚሉ ስጋቶች በሰፊው ነው የተስተጋባው፡፡
ጉዳት የደረሰበት የሃዲስ መስመሩ መሰረተልማት
በዚህ ላይ ዶይቼ ቬለ (DW) አስተያየታቸውን የጠየቃቸው በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ታጠቅ ነጋሽ፤ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጩትን መረጃዎች መመልከታቸውን በማንሳት ይህ እውነታ ከዚህ ቀደም የነበረን እንጂ አሁናዊ የባቡር መስመሩን ሁኔታ የሚገልጹ አይደሉም ብለዋል፡፡ “ብሎን የተፈታበት ሃዲድ ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያው የሚንሸራሸሩት ምስሎቹ ከዚህ በፊት የነበረ ነው” ያሉን ኃላፊው ይህ አከባቢ ከአመታት በፊት ችግሩ የተከሰተበት “ከዲማ-ሰበታ” አከባቢ መሆኑንና ይህ ስፍራ አገልግሎት ከሚሰጥ የሃዲዱ መስመር ውጪ የሚገኝ አነስተኛ ቦታ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ “እናም በዚህ የባቡር ትራንስፖርቱ ከሚጠቀመው ውጪ የሆነውና ከዚህ በፊት ስርቆት ተፈጽሞበታል” ያሉት የሃዲዱ ብሎኖች አሁናዊውን የባቡር ትራንስፖርቱን አገልግሎት እንደማያስተጓጉል አስረድተዋል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው የመስመሩ መሰረተ-ልማቶች እጣፈንታ
መነሻውን ከሰበታ አድርጎ እስከ አዳማ የሚሄደው የባቡር መንገድ ሁለት ባቡሮች የሚተላለፉበት መስመሮች ያሉት ነው የሚሉት አቶ ታጠቅ፤ በብሎኖች መፈታት የተጠቀሰው ቦታ ግን ባቡር የማያልፍበት፤ ምናልባትም ወደፊት ለማስፋፊያ ተብሎ በመታሰብ ከፕላኑ ውጪ ብዙ ሃብት ፈሶበት የተገነባ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ከዓመታት በፊት የብሎኖች መፈታት ስርቆት አጋጥሞታል የተባለውና ለጊዜው አገልግሎት የማይሰጥ የተባለው ሌላው የባቡር ሃዲድ መስመር ከለቡ-ፉሪ ባቡር ጣቢያ እስከ ዲማ-ሰበታ የሚወስደው 15 ኪ.ሜ. ግድም ርቀት ያለው የባቡሩ አንደኛው መስመር ሲሆን ይህ መስመር ጥገና እስኪደረግለት ለጊዜው አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑም ነው የተገለጸው፡፡ ሃብቱ አሁንም ቢሆን በስርቆት እንዳይባክን ምን ታስቧል የተባሉት አቶ ታጠቅ፤ “አሁን እሱን ሙሉ በሙሉ የማንሳት እንቅስቃሴ ተጀምሯል” ሲሉ መልሰዋል፡፡ አገልግሎት የማይሰጠውን የባቡር ሃዲዱን ለማንሳትና ጥገና የሚያስፈልገውን ደግሞ ለመጠገን እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው “አገልግሎት የማይሰጥ ተብሎ የተለየና ባቡር እንቅስቃሴ የማይደረግበት፤ ግን አሁን ላይ ስርቆት ተፈጽሞበታል የተባለው የባቡር መስመሩ ከግንባታው ጀምሮ ማስተካከያ ሊደረግለት የሚገባ ቦታ ነው” በማለት በዚህ ስፍራ ላይ ያለውን ሃብት ወደ ፊት ሙሉ በሙሉ በማንሳት በሌሎች አገልግሎት ልሰጡ በሚችሉ መሰረተልማቶች ላይ ለመጠቀም እቅድ መያዙንም አክለው አብራርተዋል፡፡
የባቡር መስመሩ አሁናዊ አገልግሎት
መነሻውን ከዲማ-ሰበታ አድርጎ ወደ ጂቢቲ እና ከጅቡቲ አዲስ አበባ የተዘረጋው የኢትዮ-ጅቡቲየባቡር መስመርየመንገደኞች እና የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ እቃ ማጓጓዣ አገልግሎቶች እየተሰጠበት መሆኑን ዶይቼ ቬለ በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡ ዛሬ በፉሪ-ለቡ የባቡር ጣቢያ ተገኝተን በተመለከትንበት ወቅት ወደ ሰበታ ሚወስደው ጉዳት የደረሰበት 15 ኪ.ሜ. ርቀት ያለው አንደኛው የሃዲዱ መስመር አገልግሎት እየሰጠም አይደለም፡፡
የባቡር ትራንስፖርቱ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ታጠቅ ነጋሽ በመስመሩ ከዚህ በፊት በስፋት ተፈጽሟል ያሉት ስርቆት ከመሰረቱ ተቋርጧል ባይባልም አሁን ላይ አስጊ ነው የሚባል ስርቆት ግን አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ “ከአምስት-ስድስት ኣመታት በፊት የብሎን ስርቆቶች በስፋት ይታዩ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከጸጥታ አካላት ጋር በተሰሩ ስራዎች ሊቀረፉ ችለዋል” በማለትም የሚቀሩ ስራዎች ቢኖሩም አሁን ላይ ግን አገልግሎቱን ለመፈተን የሚያሰጋ የብሎን ስርቆች እንደ ተቋሙ እንደሌለባቸውም ገልጸዋል፡፡ “የተሰራጨው መረጃ አሁናዊውን የባቡር መስመሩን ተጨባጭ ሁኔታ አይገልጽም” ያሉት አቶ ታጠቅ፤ ችግር ይደርስባቸው የነበሩ የባቡር ሃዲድ ማቀፊያ ብሎኖችን ይሰረቁ የነበሩባቸው አከባቢዎች ላይ አንድም ግንዛቤ በመስጠት፤ ሁለትም በህግ “ተመጣጣኝ እርምጃ በማስወሰድ” ችግሮቹ ተቀርፈዋልም ነው ያሉት፡፡
የክትትል ስራዎች ወሳኝነት
756 ኪ.ሜ. በሚረዝመው የኢትዮ-ጅቢቲ የባቡር መስመር ላይ የተቀመጡ የመስመሩን ደህንነት የሚቆጣጠረው የስራ ክፍል ባለሙያዎች ባቡሩ መንገደኞች እና የእቃ ጭነት ከማከናወኑ በፊት የደህንነት ማረጋገጫ ሳይሰጡ እንቅስቃሴ የማይደረግበት አሰራር ስለመኖሩም ተጠቁሟል፡ የባቡር መስመሩ የደህንነት እና ሕግ ማስከበር (Safety and Compliance) ዳይሬክተር አቶ ለሊሳ በቀለ፤ ከዚህ በፊት ለከፍተኛ ስርቆት ተጋልጦ የነበረው መስመሩ በስፋት ተጠግኖ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንና ወደ አገልግሎት ያልተመለሱ ውስን ቦታዎች በመለዋወጫ ችግር አለመጠገናቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ አሁን ላይ አገልግሎት በማይሰጡ የባቡሩ መስመሮችእስኪጠገኑ አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገዋልም ብለዋል፡፡ ያም ሆኖ እስከ ጅቡቲ ያለውን የባቡር መስመሩን ደህንነት በከፍተኛ ትጋት እንደሚከታተሉት አስረድተዋል፡፡ “የክትትልና ቁጥጥር ማዕከሉ በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ነው” ያሉን ኃላፊው ባቡሮች መስመር ስቀይሩም ሆነ በሃዲድ ላይ እክል ካለ ከጉዞ በፊት ማረጋገጫ ይወሰዳልም ብለዋል፡፡ በዚህ አሰራር እየተሰራ እስካሁን በመስመሩ ያጋጠመ አደጋ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር