የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥሪ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 12 2016የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሌላ መንገድ እየታገሉ ይገኛሉ ያላቸው አካላት ወደ ምክክር መድረኩ እንዲገቡ ጥሪ አቀርበ ፡፡ ኮሚሽኑ በምክክር ጉባዔው የሚሳተፉ የኦሮሚያ ክልል ማህበረሰብ ተወካዮች የማጠቃለያ ልየታ መድረክ በሻሸመኔ ከተማ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ የሥራ ሃላፊዎች የኮሚሽኑን የሥራ ሂደት አስመልከተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ በሌላ መንገድ እየታገሉ ይገኛሉ “ ያሏቸው አካላት ወደ ምክክር መድረኩ እንዲገቡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
የጥበቃ ዋስትና
የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በምክክሩ ለሚሳተፉት የታጠቁ አካላት ኮሚሽኑ ተገቢውን የጥበቃ ዋስትና እንደሚያመቻች ነው ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ሒሩት ገብረስላሴ የገለጹት ፡፡
በትጥቅ ትግል ያሉ ወገኖቻችን አሁንም ሳይመሽ ቶሎ ወደ ድርድሩ እንዲገቡ በትህትና እንጠይቃለን ያሉት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ “ የሚያዋጣን ይሄ ነው ፡፡ በየታች ድረስ ሄደን ያገኘነው ህዝባችን ሰላምን እንደሚፈልግ ነው የገለጸለን “ ብለዋል ፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሳታፊዎች ልየታ በአዳማ
ዋናው ነገር እንዲህ አይነት ምክክርን ትልቅ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ሒሩት ገብረስላሴ በበኩላቸው “ ይህን አጋጣሚ በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ሊጠቀሙበት ይገባል ፡፡ በተለይ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ አካላት ወደ መድረኩ ሊመጡና ሀሳባቸውን ሊገልጹ ይገባል ፡፡ እነሱ መጥተው በሚሳተፉበት ጊዜ ኮሚሽኑ ተገቢውን የዋስትና ጥበቃ / safe space / የሚያመቻች ይሆናል “ ብለዋል ፡፡
ይሁንአንጂ የታጠቁ የሚባሉት ቡድኖች እስከአሁን በአገራዊ የምክክር ጉባዔው ላይ ሥለመሳተፍ አለመሳተፋቸው በይፋ የገለጹት ነገር የለም ፡፡
አስቻይ ሁኔታዎች
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አገራዊ ምክከር መድረኩን ለማካሄድ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ሥጋት ባየለበት ሁኔታ ነው ፡፡ የፀጥታ ችግሮች ባሉባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎችን ለመለየት ምን ያህል አስቻይ ሁኔታዎች አሉ የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ለኮሚሽነሮቹ ተነስቶላቸዋል ፡፡የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
በአማራ ክልል ከአሥር ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ ሙሁራን የአሰልጣኞች ሥልጠና ሰጥተናል ፡፡ አሁን ላይ አንዳንድ የክልሉ ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ እየጠበቅን እንገኛለን ፡፡ በትግራይ ያለው ሁኔታ የክልል አስተዳደር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ስላሉ ያን አገባዶ ጥሪውን ሲያደርግልን ሥራችንን እንጀምራለን ፡፡ በእነኝህ ሁለቱ ክልሎች ሥራዎችን ካጠናቀቅን በቀጣይ ተግባራችን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክርን ጉባዔን ማካሄድ ነው “ ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ