የስደተኞች ሰቆቃ የመን እና ሳውዲ አረቢያ ድንበር ላይ
ሐሙስ፣ መጋቢት 24 2018
ከአማራ ክልል ወደ ሳውዲ አረቢያ በየመን በኩል በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ በመንገድ ላይ በሚገጥሟቸው አሰቃቂ ችግሮች ህይወታቸውን እያጡ መሆኑ ተደጋግሞ ሲገለጽ የቆየ ጉዳይ ነው። ስደተኞች ዋስትና ለሌለውና ለሞት ለሚዳርገው ለዚህ ጉዞ ለደላሎች ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ እንደሚከፍሉ ይናገራሉ።
አብሯት የተሰደደውን የአጎቷ ልጅ በጥይት ተመቶ ሲሞት እየተመለከተችው አልቅሳ እንኳ ሀዘኗን መግለጽ ያልቻለችው ረህመት አሊ፣ ገዳዮቹ በተሰደዱበት የየመን እና በሳውዲ አረቢያ ጅዛን ግዛት ድንበር ላይ የፈጸሙትን ታስታውሰዋለች።
"በየመን እና በጅዛን ድንበር ላይ ነው እና ሸብካ (አጥር) አለ። መጡ፣ አሰሩት አይኑን በጥቁር ጨርቅ እንደዚህ እስር ካደረጉ በኋላ ጁምአ ነው፣ እዚጋ ነው በቃ የመቱት። ሲመቱት አንገቱ ላይ ወዲያው ነው ጸጥ ያለው። ሬሳ ማንሳት አይቻልም፣ ማልቀስ አትችልም፤ በዛን ሰአት ያው ያሞራ ነው የሚሆነው። እኔም አይኔ አይቶ ውስጤ ተሰብሮ ዝም አልኩት። ለምን ብጮህ፣ ዘመድ ነኝ ብል ያው መልሼ እገደላለሁ የሚለውን እፈራለሁኝ።"
የራያ ቆቦ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዋሲሁን ምትኩ፣ በየዕለቱ በምንሰማው የልጆቻችን ሞት በሀዘን ላይ ሀዘን እየደረሰብን ነው ይላሉ።
"በብዛት ስላሉ እዛ የኛ የራያ ልጅ ወዲያው በሶስት ቀን በሁለት ቀን ወዲያው ወደዚህ ይደወላል፣ እገሌ ሞቷል እገሌ ሞቷል እገሌ ሞቷል ይባላል። በቃ ዝም ብሎ የሚቀዘፈው መአት ነው እዛ በሰው ሀገር ህይወታቸውን ሊመሩ ሄደው እዛም ያው የባሰ ነዉ የገጠማቸዉ ባለው ችግር ሁኔታ፣ በጊዜያዊ ሁኔታ በሰው ሀገር እየረገፉ እያለቁ ነዉ። ከሀዘን ላይ ሀዘን እየተጨመረ ነው።"
የኮምቦልቻ ከተማዉ ወጣት አወል አህመድ እና የራያ ቆቦ ቀይ ጋራ አካባቢ ነዋሪው ተስፋዬ ሲሳይ፣ በተደጋጋሚ ሳውዲ አረቢያ በሕገ-ወጥ መንገድ ተጉዘዋል። ለአንድ ጉዞም በህገ-ወጥ መንገድ ከ300 ሺህ ብር ጀምሮ እንደሚያስከፍል ነው የሚናገሩት።
" አንዳንዱ በነጻ ይገባል፣ አንዳንዱ ደግሞ ያው በኢትዮጵያ እስከ 500 ሺህም እስከ 400 ሺህም ይፈጃል። ከዚህ እስከ ድንበር ድረስ 95 ሺህ ብር ይሆናል፣ ''ከዛ ድንበር ለመቁረጥ ደግሞ 45 ሺህ ብር ትከፍላለህ። ከዛ በኋላ ደግሞ ድንበር ከቆረጥክ በኋላ መሸዋር (ትራንስፖርት) የሚያነሳህ ያው ሰው ይኖርሃል። ለምሳሌ አሁን የኔ አጎት 45 ሺህ የድንበርን ጨምሮ ራሱ 300 ምናምን ሺህ ከፍሏል።"
ባህር ተሻግሮ በሚኖር የበረሃ ላይ የእግር ጉዞም እስከ ሶስት ሰው በመንገድ ላይ ሳይሞት ያሰብንበት ቦታ አንደርስም የሚለው አወል አህመድ፣ በጉዞ ወቅት እራስን ማዳን እንጂ ሌሎችን ማገዝ አይቻልም ይላል።
"ሰው ይሞታል በቃ ግድ ነው፣ እና ሶስት ሰው ሳትሸኝ ማንኛውም ሰው አይደርስም። (ትታችኋቸው ነው የምትሄዱት?) አርፈን ከሆነ የሞተው ይቀበራል፣ መንገድ ላይ እየተጓዝክ ደግሞ ቀውጢ ቦታ ላይ ከሆነ ሁሉ እራስን አውጣ ነው፤ ማንም ማንም ቸክ አያደርግም። ያው ስተርፍ ብቻ ነው እከሌ የት ነው፣ እከሌ የት ነው ብለህ የምትለው። እንደገና ደግሞ እኛ ያላየናቸውን ስንመለስ ደግሞ መሞቱንም የሚያይ አለ። አሁን አንዳንድ ቦታ ላይ ቀውጢ ቦታ ላይ እንግዲህ አንድ ሰው ሸርተት ካለ ከደከመ ሩሁ ባይወጣም ትተህዉ ልትሄድ ትችላለህ"
በአሁኑ ጊዜ በደላሎች አማካኝነት ከሀገር ለመውጣት እና ወደ ሳውዲ አረቢያ እና ሌሎች ሀገሮች ለመጓዝ በአማራ ክልል በኩል የሚያልፉ ከትግራይ ክልል ጭምር የሚመጡ ወጣቶች ናቸው የሚለው አስተያየት ሰጪም፣ ሁሉ ነገር በደላሎች አማካኝነት ይከናወናል ሲል ይናገራል።
"አሁን እኛ እንደ ማዕከልም ነን የትግራይ ክልል አዋሳኝ ስለሆነ ፍሰቱ ከትግራይ ራሱ ይጎርፋል። ይሄ ወጅራት ምናምን የሚባለው አካባቢ ከአድዋ ከምናምን መጥተው እዛ ነው። እዛ ሀራ አካባቢ ያለው የደላላ ቡድን ነው ወደዛ እንዲሄዱ የሚያደርገው። ያው ብዙ ወጣቶች እያጣን ነው በየቀኑ። እዚህ ሲጨንቀው ነው የሚወጣው፣ እዚህ ከማንም በራሱ ሰው ከሚገደል ሄዶ እዛ እድሉን ሞክሮ እንትን ቢኖር ነው የሚሻለው።"
260 ሺህ ወጣቶችን በተያዘው የበጀት አመት በሕጋዊ መንገድ ስልጠና ወስደው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች እንዲጓዙ ማድረጋቸውን የሚናገሩት የአማራ ክልል ስራ እና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አማረ ዓለሙ፣ ያለ ክፍያ በሕጋዊ መንገድ ወደ ፈለጉበት መሄድ እየተቻለ ወጣቶች የአሳ ቀለብ እየሆኑ ነው ይላሉ።
‘’ በተለይ ወንዶቹ አካባቢ ነው ይሄ ችግር እየተፈጠረ ያለው። ሴቶቹ አሁን አብዛኞቹ በህጋዊ መንገድ ነው የሚሄዱት። ወንድ አካባቢ ላይ ግን እኔ የማውቃቸው እንኳን ባህርዳር 500 ሺህ ብር ምናምን የተበሉ ልጆች አሉ። በባህር የሚሄዱት እንደተጠበቁት ሆነዉ በደላላ የሚበሉት ደግሞ ብዙ ናቸዉ ። በህጋዊ መንገድ ምንም ገንዘብ ሳትከፍል መሄድ እየተቻለ ለባህር እና ለደላላ ቀለብ እየሆኑ ነው።"
ኢሳያስ ገላው
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ