1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመጋቢት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseረቡዕ፣ መጋቢት 9 2018

የመጋቢት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና የኢትዮጵያ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው በዋስ እንዲለቀቁ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰጥቶት የነበረውን ውሳኔ ዛሬ ውድቅ አደረገው። የተከ የእስራኤል ጦር ኃይል የኢራንን የስለላ ጉዳይ ሚንስትር ኢስማኢል ኻቲብን መግደሉን አስታወቀ። ኢራን ግድያዉን አላረጋገጠችም። የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና እሥራኤል በኢራን ላይ ስለከፈቱት ጦርነት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለጀርመን አማክራ ቢሆን ኖሮ፣ እርምጃው እንዳይወሰድ እንመክራቸው ነበር ሲሉ አስታወቁ። ሜርስ እንዳሉት ዋሽንግተን ስለጦርነቱ ጀርመንን አላማከረችም።

https://p.dw.com/p/5Ae0X

ዶክተር ሲሳይ አውግቸው በዋስ እንዲለቀቁ የተሰጠውን ውሳኔ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ

የኢትዮጵያ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው በዋስ እንዲለቀቁ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰጥቶት የነበረውን ውሳኔ ዛሬ ውድቅ አደረገው። የተከሳሽ ጠበቃ፣ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ምድብ ፀረ ሽብር እና ሕገ-መንግሥታዊ ችሎት ፣ያሳለፈውን ውሳኔ በመሻር የዋስትና መብታቸውን ዛሬ አግዶታል ብለዋል። የተከሳሽ ጠበቆች ዶክተር ሲሳይ የተከሰሱበት አንቀጽ ዋስትና መጠየቅን ወደማያስከለክል በመዞሩ "አዲስ ነገር ተከስቷል" በሚል ይህንኑ ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ አስገብተው እንደነበር ከተከሳሽ ጠበቆች መካከል አንዱ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል። ጠበቃው ዛሬ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ግን ከፍተኛው ፍርድ ቤት አሳልፎት የነበረውን የዋስትና መብት ሽሮታል።

ፍርድ ቤቱ በሽብር ወንጀል ተከሰው በማረሚያ ቤት የሚገኙት  ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው የካቲት16 ቀን 2018 ዓ.ም. በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ብይን የሰጠ ቢሆንም በወቅቱ ከማረሚያ ቤት ሲወጡ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ነበር።

በዚሁ መዝገብ ሥር ተከሰው በእሥር ላይ የሚገኙት ገነት አስማማው እና መስከረም አበራ እንዲሁም በሌላኛው የክስ መዝገብ  ተመሳሳይ የሽብር ክስ የቀረበባቸው የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያሌው በጠና ሕመም ላይ መሆናቸውን ጠበቃቸው ሰለሞን ገዛኸኝ ነግረውናል። በ2015 ዓ.ም. በእነ ዶ/ር ወንደውሰን አሰፋ መመዝገብ ሥር ከተከሰሱት 51 ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው የፌደራል መንግሥቱን ሥልጣን በኃይል ለመቆጣጠር የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸውን መከታተል ከጀመሩ ሦስት ዓመታት ሊሞላቸው ወራቶች ይቀራሉ።

ኢራን በእስራኤል ለተገደሉት የደኅንነት ሃላፊዋ አጸፋ ቴላቪቭን በሚሳይል መታች  

የእስራኤል ጦር ኃይል የኢራንን የስለላ ጉዳይ ሚንስትር ኢስማኢል ኻቲብን መግደሉን አስታወቀ።የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር እስራኤል ካትስ እንዳሉት ጦራቸዉ በሁለት ቀናት ዉስጥ ሶስተኛዉን የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ኢስማኢል ኻቲብን ገድሏል።ኢራን ግድያዉን አላረጋገጠችም።እስራኤል ትናንት የኢራን  የፀጥታ ላዕላይ ምክር ቤት ሊቀመንበር ዓሊ ላርጃኒንና የኢራን የሚሊሺያ ጦር አዛዥ ጎላምሬሳ ሱሌማይኒን መግደሏን ኢራን አረጋግጣጠላች።

ኢራን፣ የደኅንነት ሃላፊዋን አሊ ላሪጃኒንና ሌሎች ቁልፍ ባለሥልጣናትዋን እሥራኤል ብትገድልባትም ወዲያውኑ በሌሎች ባለሥልጣናት ስለሚተኩ ዘመቻዎቼን አያደናቅፍም ስትል አስታወቀች። አርካቺ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ሞት አገረ መንግሥቱን እንደማያናጋ እና መንግሥትም ስራውን እንደማያቆም ለአልጀዚራ በሰጡት እና በኢራን መንግሥታዊ መገናኛ ብዙሀን በወጣው ቃለ ምልልስ ላይ ገልጸዋል። የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርካቺ ዩናይትድ ስቴትስ እና እሥራኤል የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠንካራ የፖለቲካ ስርዓት እንዳለውና በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ እንደማይመካም ተናግረዋል።

በዛሬው እለት ኢራን ለላርጃኒ ግድያ አጸፋ ቴላቪቭን ዒላማ ያደረገ የሚሳይል ጥቃቶች መፈጸሟን የኢራን አብዮታዊ ዘብ በኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ አስታውቋል።  የእስራኤል ባለሥልጣናት ሰዎች በብዛት በሚኖሩበት በቴላቪቭ በደረሰው በዚሁ ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል። ይህም ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ እሥራኤል ውስጥ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር ወደ 14 ከፍ አድርጓል። 

የእስራኤል የአየር ድብደባ በኢራንና በሊባኖስ

የእስራኤልና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይላት ዛሬም ለ18ኛ ቀን የተለያዩ የኢራን ከተማና መንደሮችን ደብድበዋል።የእስራኤል ጦር ከኢራን በተጨማሪ ደቡባዊ ሊባኖስንና ርዕሠ-ከተማ ቤይሩትን መደብደቡን ቀጥሏል።በዛሬዉ ድብደባ የሒዝቡላሕ ቴሌቪዥን ጣቢያ አንድ ኃላፊና ባለቤቱን ጨምሮ 8 ሰዎች መገደላቸዉን የሊባኖስ የጤና ሚንስቴር አስታዉቋል።ኢራናን፣ ሒዝቡላሕና ኢራቅ ዉስጥ የሸመቁ የተለያዩ አፍቃሬ-ኢራን አማፂያን እስራኤልን፣ በባግዳድ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲን ጨምሮ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ሐገራት ዉስጥ የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ተቋማትን ደብድበዋል።በዛሬዉ ድብደባ ቴል አቪቭ አጠገብ ቢያንስ ሁለት ሰዎች መገደላቸዉን የአሜሪካዉ ዜና አገልግሎት AP ዘግቧል።

እየሩሳሌም   እሥራኤል የጦር ኃይሏ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እንዲገድል ፈቀደች

እሥራኤል የጦር ኃይሏ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እንዲገድል መፍቀዷን አሳወቀች ። የጦር ኃይሏ ማናቸውንም የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ከፍተኛ ባለሥልጣን የመግደል ሥልጣን እንደተሰጠው የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ተናግረዋል። የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ  እርሳቸውና ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የእስራኤል የመከላከያ ኃይል  ተጨማሪ ፈቃድ ሳያስፈልገው የስለላና የአሠራር ክበቡ የተዘጋበትን ማንኛውንም ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣን እንዲያስወግድ ፈቅደናል» ሲሉ ተናግረዋል። ሁሉንም ማደናቀፍ እና ማጥቃታችንንም እንቀጥላለንም ብለዋል።    

ሜርስ ዩናይትድ ስቴትስ ስለ ኢራን ጦርነት አማካራን ቢሆን ኖሮ እንቃወም ነበር አሉ

የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና እሥራኤል በኢራን ላይ ስለከፈቱት ጦርነት ዩናይትድ ስቴትስ አማክራቸው ቢሆን ኖሮ፣ ይህ እርምጃ እንዳይወሰድ እንመክራቸው ነበር ሲሉ አስታወቁ።  ለጀርመን ምክር ቤት አባላት ዛሬ ባደረጉት ንግግር እሥራኤል እና ዩናይትድ ስቴትስ ፣ኢራን የወደፊት ስጋት እንዳትሆን የያዙትን ግብ እንጋራለን ያሉት ሜርስ የኢራን አገዛዝ ለዓመታት ሕጎችን መጣሱን በዓለም ላይም ሽብርን ማስፋፋቱንና አካባቢውንም ማናጋቱን ገልጸዋል። ይሁንና አሁንም ስለ ጦርነቱ ብዙ ጥያቄዎች አሉን ሲሉ የተናገሩት ሜርስ አሜሪካንና እስራኤል ይህ ዘመቻ  እንዴት ሊሳካ እንደሚችል አንድም አሳማኝ የሆነ እቅድ አላሳዩም ሲሉ ወቅሰዋል። ዋሽንግተን ጀርመንን ስለ ጦርነቱ  አላማከረችም ሲሉ  ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል።

 « እስከዛሬ ድረስ ይህ ዘመቻ እንዴት ሊሳካ እንደሚችል አሳማኝ ሃሳብ የለም። ዋሽንግተን እኛን አላማካረችንም ፤የአውሮጳውያን ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነም አላሰበችም።  ክቡራትና ክቡራን (ጦርነቱ) አሁን በሚካሄድበት መንገድ መከናወኑን ተቃውመን እንማክር ነበር ።ለዚህም ነው ጦርነቱ እስከቀጠለ ድረስ በዚህ ጦርነቱ ውስጥ አንሳተፍም ስንል ያወጅነው።»

ጦርነቱ በተቻለ መጠን በአፋጣኝ እንዲቆም ጥሪ ያቀረቡት ሜርስ አውሮጳ ጦርነቱ ቶሎ እንዲቆም፣  በአካባቢው እንዳይባባስም መከላከልና እንደ አገር የኢራንን መበታተን የማስቀረት ፍላጎት እንዳለውም ጠቁመዋል።

የአሜሪካ ድምጽ VOA ሠራተኞች ወደ ቀድሞ ስራቸው እንዲመለሱ አንድ ዳኛ አዘዙ።

አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ዳኛ የአሜሪካ ድምጽ VOA ሠራተኞች ወደ ቀድሞ ስራቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ ሰጡ። ዳኛ  ሮይስ ላምበርት ከስራ  የተባረሩት ከአንድ ሺህ በላይ የVOA ሠራተኞች እስከ ፊታችን መጋቢት 14 ቀን ድረስ ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ እና ጣቢያው የሚያስተላልፋቸው ዝግጅቶችም መሰራጨታቸው እንዲቀጥል ትናንት ማዘዛቸውን የጀርመን ዜና  አገልግሎት DPA ዘግቧል።

ላምበርት በትናንቱ ውሳኔያቸው VOAን የሚያስተዳድረው የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ በምህጻሩ USAGMን ለመዝጋት የተደረገው ሙከራም ሕገ ወጥ ነው ብለዋል።

ዳኛ ላምበርት ባለፈው መስከረም ወር USAGM  ለጊዜው ሠራተኞችን እንዳያባርር የሚያስቆም የእግድ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር። በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ  ሁለተኛው የስልጣን ዘመን መጀመሪያ ላይ የተሾሙት፣ የቀድሞው የኤጀንሲው ኃላፊ ካሪ ሌክ፣ ሠራተኞች   ከስራ መባረራቸውን በነሐሴ ወር ነበር ያሳወቁት ። ቅነሳው የተደረገው ትራምፕ በመጋቢት ወር በአሜሪካን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ በሚተዳደረውና በውጭ ለሚገኙ አድማጮች በበርካታ ቋንቋዎች ፕሮግራሞችን በሚያሰራጨው በአሜሪካን ድምጽ ራድዮ ጣቢያ ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ቅነሳ እንዲደረግ ልዩ ትዕዛዝ ካወጡ በኋላ ነበር።  በ1942 የናዚ ፕሮፓጋንዳን ለመቃወም የተመሰረተው VOA ለረጅም ጊዜ የአሜሪካንን እሴቶች በውጭ አገር ለማስተዋወቅ እንደ ቁልፍ መሣሪያ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል።  ትራምፕ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ጣቢያው የቻይናን ፕሮፓጋንዳ ያስተጋባል በሚል ክስ ሰንዝረው በተደጋጋሚ ሲጋጩ ቆይተዋል።

ኂሩት መለሰ

ጸሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።