የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት አፍሪካን በእጅጉ እንደሚጎዳ መሐሙድ አሊ ዮሱፍ ተናገሩ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 1 2018
በመካከላቸው ምስራቅ ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሳስቦናል ሲሉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዮሱፍ ተናግረዋል።በተለይ የነዳጅ ዋጋ በእጅጉ ማሻቀብ በአህጉሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ሲሉ ሊቀመንበሩ ለ DW አስረድተዋል።ከዚህ አንጻር፣የአፍሪካ የውጭ ጉዳይና የኢኮኖሚ ሚኒስትሮች ስብሰባ በቅርቡ በሞሮኮ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤልበኢራን ላይ የከፈቱትን ጥቃትና ኢራንም በበኩሏ እየወሰደች ያለችውን የአጸፋ ጥቃት ተከትሎ የቀጠለው ግጭት፣የአፍሪካን አህጉርም በእጅጉ አሳስቧል። በጉዳዩ ላይ ያነጋገርኳቸው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዮሱፍ ይሄንኑ አስረድተዋል።
የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ እና የአፍሪካ ስጋት
በመካከለኛው ምስራቅእየተካሄደ ያለዉ ጦርነት፣ በአለምአቀፍ የንግድ መስመሮች ላይ መስተጓጐል ፈጥሯል፣አንዳንድ አገራት ለገበያ የሚያቀርቡት የነዳጅ መጠን እንዲቀንስም ምክንያት ኾኗል።የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዮሱፍ ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት፣ ይህ የነዳጅ ገበያ መዛባት በአህጉሪቱ ላይ ትልቅ ጉዳት ያስከትላል።
"በከፍተኛ ፍጥነት በሚጨምረው የነዳጅ ዋጋ ምክንያት እንጎዳለን።ከዚህ ጋር አብሮ ከሚመጣው የዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ፣ሁኔታው በአገሮቻችን ላይ አጥፊ ውጤት ያስከትላል" በማለት አስረድተዋል ።
ዶይቼ ቬለ ሰሞኑን ያነጋገራቸው አንጋፋየኢኮኖሚ ባለሙያና "ኢኒሼቲቭ አፍሪካ" የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና፣ አፍሪካ በተፋላሚዎቹ ወገኖች የሚሰነዘረው ጥቃት ኢላማ ባትኾንም፣ከአለም የንግድ ስርዓት ጋር የተሳሰረው ኢኮኖሚዋ ግን መጎዳቱ እንደማይቀር ገልጸዋል።
ከነዳጅ ዋጋ መናር በተጨማሪ፣የወጭና ገቢ ንግድ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊኖር እንደሚችልም አመልክተዋል።ምርታቸውን ወደ ውጭ የሚልኩና ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገራት "በዋጋም ኾነ በተለያየ ሁኔታ መጎዳታቸው አይቀርም" በማለትም አአስረድተዋል ።
የአፍረካ ዝግጅትና ምላሽ
በተለይ አሁን በመካከለኛው ምስራቅ ከተፈጠረው ሁኔታ አንጻር፣ ለአፍሪካ አገራት የሚበጀው የበለጠ በኢኮኖሚ መተሳሰር እንደኾነ አቶ ከቡር ገና ይናገራሉ።የጀመሩትን የመሰባሰብ ሁኔተ የበለጠ ለማጠናከር የሚችሉበት አዲስ አጋጣሚ አለ ብለው እንደሚያምኑም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዮሱፍ እንደገለፁት፣ አገራቱ በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተው ሁኔታ ባስከተለው ተጽዕኖ ላይ በቅርቡ ይነጋገራሉ።
"የውጭ ጉዳይና የኢኮኖሚ ሚኒስትሮች ስብሰባ በቅርቡ በሞሮኮ ይካሄዳል። ጦርነቱ በኢኮኖሚዎቻችን ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ መቀነስ እንድንችል፣የመቋቋሚያ እርምጃዎችን ማዘጋጀት ይኖርብናል።የጦርነቱ ውጤት አሁንም እየተሰማን ነው።ዛሬ የነዳጅ ዋጋ ከመቶ ዶላር በላይ ነው" ብለዋል።
ሊቀመንበሩ ትናንት ባወጡት መግለጫ፣ግጭቱን ተከትሎ በኃይልና ትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንደሚያሳስቧቸው ገልጸዋል።እንደዚህ አይነት ጥቃት በአካባቢያዊና አለምአቀፋዊ የኢኮኖሚ መረጋጋት ላይ ስጋት እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።በጦርነቱ ምክንያት የሚከሰት የነዳጅ ዋጋ መናርና ሌሎች አሉታዊ ውጤቶች በአፍሪካውያን ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ ማድረግ እንደሚገባም ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።"እነዚያ አሉታዊ ውጤቶች በተለይ ከምግብ ዋስተና አንጸር ይበልጥ ተጋላጭ በኾኑ ሕዝቦቻችን ላይም ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ ማድረግ አለብን" በማለት አስረድተዋል።
የአፍረካ አቋም ምንድን ነው?
ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጥቃትና ኢራንም እየወሰደች ባለችው የአጸፋ እርምጃ ምክንያት የተፈጠረውን ስጋት ተከትሎ፣ ከአፍሪካ አገራት የተሰማው ምላሽ የተበታተነ ነው። ይሄንኑ ሁኔታ የጠየኳቸው የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዮሱፍ፣ በተለይ ግጭቱ በአህጉሪቱ ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
"በዚያ ላይ እየሠራንበት ነው። የሠላምና ፀጥታ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ስብሰባ አድርጓል።ግጭቱ በአህጉራችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እንዴት መመከትና የመቋቋሚያ አቅም መፍጠር እንደምንችል በመካከላችን የምናደርገውን ምክክር እንቀጥላለን" በማለት አስረድተዋል።ሊቀመንበሩ ትናንት በወጡት መግለጫ፣የአፍሪካ ሕብረት "ለአለም አቀፍ ሕግ መከበር፣ለግጭቶች በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንደዚሁም ለአለምአቀፍ ሰላምና ፀጥታ መጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል"
እስክንድር ፍሬዉ
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር