1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢሰመኮ የቅድመ ምርጫ ሂደቶች ላይ ጥሰቶች እንደነበሩ ገለፀ

ሰለሞን ሙጬ
ዓርብ፣ ሚያዝያ 30 2018

ኮሚሽኑ ፓርቲዎች በምርጫ ጉዳይ ስብሰባም፣ሰላማዊ ሰልፍም ለማድረግ ክልከላ እንደተፈፀመባቸው እንደገለፁለት እና በፖሊስ ጣቢያዎች እና በመጠጥ ቤት ግቢ ውስጥ ምርጫ ጣቢያዎች መደራጀታቸውን መመልከቱን ጠቅሷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኢሰመኮ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የምርጫ ጣቢያ መቋቀሙን የጠቀሰበትን የዳሰሳ ግኝት አልተቀበለውም።

https://p.dw.com/p/5DUdb
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎምስል፦ Solomon Muche/DW

ኢሰመኮ የቅድመ ምርጫ ሂደቶች ላይ ጥሰቶች እንደነበሩ ገለፀ


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅድመ ምርጫ ሂደቶች ላይ ከትግራይ ክልል በስተቀር አደረግኹት ባለው የክትትል ቅኝት ጉልህ ጥሰቶችን ለይቶ መሰነዱን ገለፀ።
ኮሚሽኑ ትናንት ውስን የመገናኛ ብዙኃንን ብቻ ጠርቶ ይፋ ባደረገው ውጤት፣ "በአብዛኛዎቹ ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች በተረጋጋ ኹኔታ እና አሳሳቢ የፀጥታ ሥጋት ሳይደርስ ፣የመራጮች ምዝገባ ሂደት መከናወኑን" ጠቅሷል። 
ፓርቲዎች በምርጫ ጉዳይ ስብሰባም፣ ሰላማዊ ሰልፍም ለማድረግ ክልከላ እንደተፈፀመባቸው እንደገለፁለት እና በፖሊስ ጣቢያዎች እና በመጠጥ ቤት ግቢ ውስጥ ምርጫ ጣቢያዎች መደራጀታቸውን መመልከቱን ጠቅሷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕግ ጥሰት ፈጽመዋል ያላቸውና በአምስት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 22 ምርጫ ጣቢያዎችን መዝጋቱን አስቀድሞ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

"በተረጋጋ ኹኔታ እና አሳሳቢ የፀጥታ ሥጋት ሳይደርስ የመራጮች ምዝገባ ሂደት" ተከናውኗል - ኢሰመኮ  

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ተቋማቸው "የተዓማኒነት ጥያቄ የማያስነሳ" ያሉትን የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅድመ ምርጫ ሂደቶች ክትትል ማድረጉን ገልፀዋል።
ይሄው ክትትል ከመደበኛው የዕጩዎች ምዝገባ እስከ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ የሚደርስ ነው ተብሏል። የኮሚሽኑ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ዳይሬክተር ወይዘሮ መቅደስ አመኑ እንዳሉት ቃለ መጠይቆችን እና የቡድን ውይይቶችን በማድረግ የተከናወነው ይህ ክትትል ከትግራይ ክልል ውጪ የተሠራ ነው።
95 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚመርጡባቸው የምርጫ ጣቢያዎች መቋቀማቸው በበጎ ከተለዩ ግኝቶች መካከል አንዱ ሆኖ ተገልጿል።
"በአብዛኛዎቹ ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች በተረጋጋ ኹኔታ እና አሳሳቢ የፀጥታ ሥጋት ሳይደርስ የመራጮች ምዝገባ ሂደት መከናወኑ» ነው።

በዳሰሳው የተለዩ ዋና ዋና ችግሮች ምንድን ናቸው? 

ኃላፊዋ የኢንተርኔት መቆራረጥ የምዝገባ ሂደትን ማስተጓጎሉን፣ ተጋላጭ ለሚባሉ ዜጎች ተደራሽ ያልሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን፣ የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ምልክቶች እና የምርጫ ጣቢያ መመርያዎች በግልጽ  ያልተመላከተባቸው መሆኑን፣ ሕዝባዊ ትእይንቶች ላይ ዜጎች በግዳጅ እንዲሳተፉ መገደዳቸውን፣ የምርጫ ቁሳቁስ ዘግይቶ መድረስ እና የምዝገባ ሂደት ዘግይቶ መጀመር ምዝገባ ለሦስት ቀናት ብቻ የተደረገባቸው የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን ዘርዝረዋል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ቢሮ በአዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ቢሮ በአዲስ አበባ ምስል፦ Solomon Muchie/DW

መሰል ችግሮች በፓርቲዎችም፣ በምርጫ ቦርድም ተለይተው ነበር

እንዲህ ያሉ ግልፅ የሕግ ጥሰቶች መስተዋላቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል። ስምንት ክልላዊ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያሰባሰበው "ሠላም ለኢትዮጵያ" የተባለው ጥምረት አንዱ ሲሆን ከዚህ በፊት ይህንኑ በጥምረቱ ዋና ፍፈጻሚ አቶ ዳሮታ ጉምአ በኩል ለዶቼ ቬለ ደጋግሞ ገልጾ ነበር።

"አንድ ሰው ከአንድ በላይ ካርድ የወሰደበት እና የተመዘገበበት ጣቢያ፣ የካርዱ ፎቶም ጭምር ደርሶናል።" 


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚሁ ከኢሰመኮ የዳሰሳ ውጤት በፊት በመራጮች ምዝገባ ሂደት ወቅት የሕግ ጥሰት ፈጽመዋል ያላቸውና በአምስት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 22 የምርጫ ጣቢያዎችን መዝጋቱን ይፋ አድርጎ ነበር። አቶ ዳሮታ ጉምአ በወቅቱ እንደነገሩን በአባሎቻቸው፣ በደጋፊዎቻቸው እና በዕጩዎቻቸው ላይ "ጥቃት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ደርሷል።

የኢሰመኮ የዳሰሳ ውጤት ሲቀርብ ውስን መገናኛ ብዙኃን ብቻ ነው የተጋበዙት

ብሔራዊዉ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት እንዲህ ያሉ መሰረታዊ የምርጫ ወቅት የዳሰሳ ግኝቶች ሲገለፁ ውስን መገናኛ ብዙሃንን ብቻ መጋበዙ ጥያቄ የሚያጭር ሆኗል። 
ዶቼ ቬለ ባሰባሰበው መረጃ ኢሰመኮ ካገኘው የቅድመ ምርጫ ሂደት የዳሰሳ ውጤት በተጨማሪ ዕድሜያቸው ለምርጫ ያልደረሱ ሰዎች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ የተገደዱባቸው ቦታዎች አሉ። ይህም ብቻ አይደለም በአዲስ አበባ በየቤቱ እየዞሩ ዜጎች ካርድ እንዲወስዱ ያደርጉ የነበሩ የገዥው ፓርቲ እና የመንግሥት ተወካዮች መኖራቸውን ለመረዳት ችለናል።

ኮሚሽኑ የፀጥታ አካላትም ሆነ መንግሥት በቀጣይ ከሚኖሩ የምርጫ ሂደቶች ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ መክሯል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድኢሰመኮ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የምርጫ ጣቢያ መቋቀሙን የጠቀሰበትን የዳሰሳ ግኝት አልተቀበለውም።

ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ