1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

በአቬሽን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ምን ደረጃ ላይ ትገኛለች?

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ሰኔ 5 2016

ከስምንት አስርተ አመታት በፊት አውሮፕላን ለመገጣጠም ጥረት ያደረገችው ኢትዮጵያ፤ በአፍሪቃ ስሙ የሚጠቀሰስ አየር መንገድ በመመስረትም ቀዳሚ ሀገር ነች።ለመሆኑ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በአቬሽን ቴክኖሎጂ ምን ደረጃ ላይ ትገኛለች? በዘርፉ ያሉ ችግሮች እና መፍትሄዎችስ?

https://p.dw.com/p/4gwV7
ባለሙያዎች እንደሚሉት ለአየር መንገዱ ስኬት በኢትዮጵያውያን መመራቱ አስተዋፅኦ አድርጓል
ባለሙያዎች እንደሚሉት ለአየር መንገዱ ስኬት በኢትዮጵያውያን መመራቱ አስተዋፅኦ አድርጓልምስል Mas Agung Wilis/Zuma/IMAGO

የአቬሽን ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ምን ደረጃ ላይ ነው?

በጎርጎሪያኑ 1935 አውሮፕላን መገጣጠም የሞከረችው ኢትዮጵያ፤ ከብዙ አስርተዓመታት በኋላ ያለፈው ነሀሴ 2023 ዓ/ም  የአውሮፕላን ክፍሎችን ለማምረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ከቦይንግ ጋር መስማማቱን የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ አስታውቋል።ሰሞኑን ደግሞ ግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ የአፍሪቃ ዋና መስሪያቤቱን  በኢትዮጵያ እንደሚያደርግ ገልጿል።
ይህም ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በአቬሽን ቴክኖሎጂ ምን ደረጃ ላይ ናት? የሚለውን ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል። ስለ ኢትዮጵያ የአቬሽን የቴክኖሎጂ ሁኔታ ሲነሳ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ትልቁ ተቋም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመሆኑ እድገቱም ከዚሁ ተቋም ጋር የተያያዘ ነው። ይህ አየር መንገድ የንግድ  በመሆኑ ደግሞ፤ የሚጠቀምባቸው ቴክኖሎጆዎች በአብዛኛው ከዚሁ ጋር የተያያዙ መሆናቸው ይነገራል።

የኢትዮጵያ ኢሮክለብ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነው የአቬሽን ባለሙያው ዮናታን መንክር  እንደሚለው በዚህ ረገድ አየር መንገዱ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።የ«ፀሐይ»አውሮፕላን ቴክኒካዊ ይዘት እና የዚያን ዘመኑ የአቬሽን ቴክኖሎጅ

አየር መንገድ ኦፕሬሽንስ ወይም አገልግሎት ራሱ ከቴክኖሎጅ ጋር የተሳሰረ ነው።የንግድ አስፔክት አለው።ትኬቶችን ለደንበኞች በጥሩ ዋጋ መሸጥ አንዱ የንግድ እንቅስቃሴ ሆኖ ነገር ግን ያን ትኬት  ለመሸጥ ደንበኞች የሚፈልጉት ግብዓት በዋነኝነት የሚመሰረተው በቴክኖሎጅ ላይ ነው።ያ ማለት አውሮፕላኑ ምን ያህል ዘመናዊ ነው?ትኬቱን የሚቆርጥበት መንገድ ምን ያህል ዘመናዊ ነው።አውሮፕላኑ ከመሳፈሩ በፊት ተርሚናል ውስጥ ያለው ለደንበኞች ግልጋሎት የሚሰጡ ፋሲሊቲዎች ምን ያህል ዘመናዊ ናቸው?ቀልጣፋ ናቸው ተደራሽ ናቸው እነዚህ ሁሉ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ናቸው።» ካለ በኋላ፤ «አንድ አየር መንገድ የቴክኖሎጅ ስርዓቱ ዘመናዊ ካልሆነ ብቁ አየር መንገድ ሊሆን አይችልም ከዚህ አንፃር  በቴክኖሎጅ ደረጃ ቀዳሚ ነው ማለት እችላለሁ በአየር መንገድ «ኦፕሬሽንስ» ባሉ ምዘናዎች።» ሲል አብራርቷል።

ዮናታን መንክር ካሳ፤ የኢሮቶጲያ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ
ዮናታን መንክር ካሳ፤ የኢሮቶጲያ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅምስል Privat

ከዚህ በተጨማሪ  ዘመኑ የፈቀዳቸውን አዳዲስ የቦይንግ እና የኤርባስ ስሪት አውሮፕላኖችን ወደ አፍሪቃ በማስመጣት አየር መንገዱ ተወዳዳሪ የለውም የሚሉት ባለሙያው፤ ቀደም ሲል በጄት ቴክኖሎጅ ቀዳሚ ከሆነው ቦይንግ 720B ከሚባለው ጀምሮ እስከ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ድረስ በርካታ አውሮፕላኖችን ከአፍሪቃ በቀዳሚነት አስገብቷል።787 የተባለውን ድሪም ላይነር አውሮፕላን ደግሞ ከዓለም በሁለተኛ ደረጃ  ማስመጣቱን ገልጿል።የኤርባስ ስሪት ከሆኑ አውሮፕላኖችም ኤር ባስ 350ን በማስመጣት  ከአፍሪቃ ቀዳሚ ነው። ባለሙያው እንደገለጸው አየር መንገዱ በቅርቡ ካዘዛቸው የቦይንግ እና የኤርባስ አውሮፕላኖች  መካከል  ቦይንግ 777-9X የሚባለው በአውሮፕላን ታሪክ እስካሁን ያልተሞከረ  እና ታጣፊ ክንፍ ያለው እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላን ይገኝበታል። ይህ አውሮፕላን ነዳጅ ቆጣቢ ፣ያነሰ የድምፅ ብክለት እና ሰፊ አካል ያለው እንዲሁም ረዥም ርቀት የሚጓዝ ነው። ይህም አየር መንገዱ ለቴክኖሎጂ ያለውን ዋጋ እና የሚሰጠውን ቦታ የሚያሳይ  መሆኑን ባለሙያው አመልክቷል።በጥገና እና በስልጠና ረገድም በተቋሙ ተመሳሳይ ስኬት መኖሩን ያስረዳል።የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አውሮፕላን ግዢ

«ሌላው በጥገና ያለው አቅም እንዲሁ ከጥገና ጋር የተያያዘ ነው።የኢትዮጵያ የጥገና ክፍል  አየር መንገድ ውስጥ ያለው  በአፍሪቃ ትልቁ የጥገና ክፍል ነው።በአውሮፕላን ስልጠና በኩልም አፍሪቃ ውስጥ የብዙ አውሮፕላኖች ምስለ በረራ ያደርጋል። ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገራት በተለይ የአፍሪቃ ሀገራትን አብራሪዎችን በማሰልጠን ውያንን በማስልጠን  እንዲሁም የምስለበረራው ቴክኖሎጂ በጣም ላቅ ያለ ነው።ለምሳሌ በጥገና የሳውዲ አረቢያ አየርመንገድን የመሳሰሉ እና ሌሎች ሀገሮች  አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየርመንገድ በመምጣት ነው አውሮፕላን የሚያስጠግኑ።» በማለት ገልጿል።

 በተለያዩ ጊዚያት በተደረጉ የስርዓት ለውጦች ውስጥ ፤ምንም እንኳ አየር መንገዱን የሚጎዳ  ሆኖ ሲያገኙት  ቶሎ እጃቸውን ቢያነሱም፤ በተለያዩ ጊዜያት የመንግስታት ጣልቃገብነት ነበረ
በተለያዩ ጊዚያት በተደረጉ የስርዓት ለውጦች ውስጥ ፤ምንም እንኳ አየር መንገዱን የሚጎዳ  ሆኖ ሲያገኙት  ቶሎ እጃቸውን ቢያነሱም፤ በተለያዩ ጊዜያት የመንግስታት ጣልቃገብነት ነበረምስል Solomon Muchie/DW

ለዚህ የአየር መንገዱ የቴክኖሎጂ ስኬት ደግሞ እንደ አቶ ዮናታን ተቋሙ በኢትዮጵያውያን እንዲመራ መደረጉ አስተዋፅኦ አድርጓል።
«እንግዲህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲቋቋም በአሜሪካውያን እገዛ የተቋቋመ ነው።በተለይ በሰው ሀይላቸው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ መንግስት ቢሆንም በቴክኒክ በኩል የአሜሪካውያን አየር መንገድ የነበረው «ቲ ደብሊዩ ኤ»የተባለው «ትራንስፈርድ ኤርላይን» ባለሙያዎቹን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ መጥቶ ነበር።በኃላ የኢትዮጵያ መንግስት በዚያን ጊዜ  አየር መንገዱን የመሰረቱት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ኢትዮጵያናይዜሽን የሚባል ፕሮግራም እንዲመሰረት አድርገው ኢትዮጵያውያን በሂደት እያንዳንዱን ስራ፣ ድርሻ ከአሜሪካውያን የሚረከቡበትን ሁኔታ እንዲመቻች በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ኮረኔል ስምረት መዳኔ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያው ዋና ስራ አስኪያጅ  በዚያን ጊዜ፤ በአሁኑ አጠራሩ ደግሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ የምንለውን ቦታ በመያዝ ኢትዮጵያውያን እንዲመሩት እንዲያስተዳድሩት መደረጉ ትልቁ ነገር ነው።ያ ባይሆን ኑሮ ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደረሰበት ደረጃ ይደርሳል ለማለት አያስችልም።ምክንያቱም በራሳቸው ዜጎች በማያስተዳድሯቸው አየር መንገዶች ውስጥ የተፈጠረውን ነገር ከብዙ የአፍሪቃ አየር መንገዶች ስለምንማር በቀላሉ መረዳት እንችላለን።»በማለት አየር መንገዱ በኢትዮጵያውያን የመመራቱን ፋይዳ አስረድቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች ማስተናገጃ ማስፋፊያ

ያምሆኖ በተለያዩ ጊዚያት በተደረጉ የስርዓት ለውጦች ውስጥ ፤ምንም እንኳ አየር መንገዱን የሚጎዳ  ሆኖ ሲያገኙት  ቶሎ እጃቸውን ቢያነሱም፤ በተለያዩ ጊዜያት የመንግስታት ጣልቃገብነት እንደነበረ ይጠቅሳል።
የባለስልጣናት ጣልቃገብነት እና በዘርፉ ተቋማዊ ነጻነት አለመኖር ደግሞ በቴክኖሎጂ እድገት ላይ  ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።ከዚህ አንጻር የመንግስት ትልቁ ድጋፍ መሆን ያለበት እንደ ባለሙያው ፤አየር መንገዱ ራሱን በራሱ እንዲመራ ማድረግ ነው።
«መንግስት ለአየር መንገዱ ሊያደርግ የሚችለው አስተዋፅኦ ዋነኛው ድጋፍ አየር መንገዱ በራሱ መንገድ በቴክኖሎጂ፣ በገበያ መር ሁኔታ ራሱን በራሱ እንዲመራ ማስቻል ነው።ሊያስፈልጉ የሚችሉ ድጋፎችን ከውጭ ሆኖ በመደገፍ በፖሊሲ በሌሎችም መንገዶች ሊደገፉ በሚችልበት መደገፍ ነው እንጅ ኦፕሬሽኑ ላያ ያን አድርግ ይህን አድርግ የሚሉ ቀጥተኛ ትዕዛዞች መምጣት ከጀመሩ ያለምንም ጥርጥር ይህ አየር መንገድ ዛሬ በምናውቀው ሁኔታ ውስጥ ይሆናል ብዬ ለመገመት በጣም እቸገራለሁ።ይህ እንግዲህ አየር መንገዱ ካሳለፈውም ታሪክ የሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት ትልልቅ አየር መንገዶችን አቋቁመው እንዳይነሱ ሆነው ከወደቁበት ታሪክ በመነሳት ይህ ለማንም ግልፅ የሆነ ነው ብዬ አስባለሁ።»ብሏል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ለአየር መንገዱ ስኬት በኢትዮጵያውያን መመራቱ አስተዋፅኦ አድርጓል
ባለሙያዎች እንደሚሉት ለአየር መንገዱ ስኬት በኢትዮጵያውያን መመራቱ አስተዋፅኦ አድርጓልምስል Solomon Muchie/DW

በሌላ በኩል  የአቬሽን ቴክኖሎጂን ለማሳደግ  በዘርፉ  የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት  ወሳኝ ነው። ያም ሆኖ በሀገሪቱ ብቸኛው ተቋም የአቬሽን ዩንቨርሲቲ ብቻ በመሆኑ፤  የሰው ሀይል እጥረትም አንዱ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው አስረድቷል።
የአቬሽን ጉዳዮችን በተመለከተ በወልስትሪት ጆርናል እና ብሪታኒያ ውስጥ ለሚታተመው አፍሪካን ኤሮስፔስ  ለመሳሰሉ  ታዋቂ መፅሄቶች ላይ የሚፅፈው ዮናታን፤ ይህንን ችግር ለመፍታት  የኢትዮጵያ ኢሮክለብን በመመስረት  በየትምህርት ቤቶቹ ፍላጎት እና ዝንባሌ ያላቸውን ልጆች በማበረታታት ካይ ይገኛል። በአቬሽን ጉዳዮች ላይ ያተኮረ «ፀሐይ አየር ሜዳ» የተሰኘ የቴሌቪዝን ዝግጅትም ያሰናዳል።በዚህ መልኩ የድርሻውን ለመወጣት እየጣረ የሚገኘው ወጣቱ የአቬሽን ባለሙያ ፤ ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን  እንዲያደርጉ ያሳስባል።

«መንግስትም ሌሎች ባለድርሻ አካላትም እንግዲህ ከወዲሁ  በተለይ ትምህርት ቤቶች እና ወላጆች ይህ ፍላጎት ያላቸውን ልጆቻቸውን እና ተማሪዎችቻቸውን እንዲሳተፉ በዚህ ውስጥ ራሳቸውን እንዲያጎለብቱ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉላቸው ከወዲሁ ጥሪ ለማቅረብ እወዳለሁ።ሌላው በመንግስት በኩል መደረግ ይገባል ብዬ የማስበው ነገር ምንድነው ለምሳሌ ኢትዮጵያን  የሚክል በአፍሪቃ ቀዳሚ አየር መንገድ ያላት ሀገር የአቬሽን ሚንስቴር  እንኳን የለንም።»ካለ በኋላ፤ ይህንን ዘርፍ የሚመለከት ሚንስቴር መስሪያ ቤት መቋቋም እንደሚገባው ይመክራል።ነገር ግን መስሪያ ቤቱን ማቋቋም ብቻ ሳይሆን የሚመሩት ሰዎችም ሙያውን በደንብ የሚያውቁ እና ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆኑ ሰዎች መሆን እንደሚገባቸው ገልጿል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ