1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ህወሓት የሁዩማን ራይትስ ዋችን ጥያቄ ዉድቅ አደረገዉ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ሰኔ 19 2018

የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም ግን፤ “መግለጫው የተጋነነነና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ” ብለዋል፡፡ “እንደ ትግራይ የህልውና አደጋ ተጋርጦብን ያለን ብሔር ነን” ያሉት አቶ ሚካኤል የሚደረገውን የቶርነት ዝግጅት “እንደብሔር ሊመጣብን የተዘጋጀውን አደጋ ለመቀልበስ የሚደረግ” ሲሉ ማብራሪያቸውን ሰትጥዋል፡፡

https://p.dw.com/p/5G8id
ህወሓት አዲስ ያወጣዉ ሕግ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን በግዳጅ ለዉጊያ የሚያሰልፍ ነዉ የሚል ትችት ቀርቦበታል
የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፍተኛ ባለሥልጣናት-በአንድ ጉባኤያቸዉ ወቅትምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ህወሓት የሁዩማን ራይትስ ዋችን ጥያቄ ዉድቅ አደረገዉ



ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሑዩማን ራይትስ ዋችን ምክርና ወቀሳ ዉድቅ አደረገዉ።ሑዩማን ራይትስ ወች በቅርቡ ባወጣዉ መግለጫ ህወሓት አዲስ የደነገገዉን ደንብ እንዲሽር ጠይቆ ነበር።ዓለም አቀፉ ድርጅት ጥያቄዉን ያቀረበዉ ደንቡ ዜጎችን በጦርነት እንዲካፈሉ የሚያስገድድ ነዉ በማለት ነበር።የህወሓት ቃል አቀባይ ግን መግለጫውን መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ በማለት አጣጥለውታል፡፡

የሁማን ራይትስ ዎች (HRW) ማሳሰቢያ

የትግራይ ባለስልጣናት በአስገዳጅ ሁኔታ ወጣቶችን ለጦርነት እንዲመለመሉ እና ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ሕወሓት)ን የሚቃወሙ እንዲቀጡ የሚያዝ ነው የተባለውን ከሰሞኑ በአወዛጋቢነቱ ስነሳ የቆየውን አዋጅ የክልሉ ባለስልጣናት በአስቸኳይ እንዲሰርዙት ሲል ሁማን ራይትስ ዎች (HRW) ከሰሞኑ ባወጣዊ ይፋዊ መግለጫ ጠይቋል፡፡
ለሰብዓዊ መብት መጠበቅየሚሟገተው ዓለማቀፋዊ ተቋሙ ከሶስት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫው እንዳመለከተው፤ ሕወሓት ይህን አዋጅ ያወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት የሾመውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርን ከስልጣን ካነሳ በኋላ ነው፡፡ ሰብዓዊ ተቋሙ ሕወሓት ያወጣን አዲሱን አዋጅ የኤርትራ መንግስት የአገራዊ አገልግሎት ግደዴታ ብሎ ወጣቶችን ለአስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ከሚጠቀሙ ህግ ጋር ተመሳሳይ ብሎታል፡፡
የሁማን ራይትስ ዎች አፍሪካ ቅርንጫፍ ምክትል ዳይሬክተር ላቲትያ ባድር የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ለሁለት አመታት ተካህዶ በነበረው ጦርነት አስከፊ ዋጋ መክፈላቸውን አስታውሰው፤ የክልሉ ባለስልጣናት አሁንም በክልሉ የነገሰውን ውጥረት ተከትሎ ሲቪል ዜጎች የውትድርና አገልግሎት እንዲሰለጥኑና ይህን የተቃወሙ እንዲቀጡ የሚያደርገው ህግ ሊሰረዝ የሚገባ ነው ብለውታል፡፡

ከፍተኛ ትችት የቀረበበት አዋጅ

በጉዳዩ ላይ ለዶይቼ ቬሌ አስተያየት የሰጡት የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም ግን፤ “መግለጫው የተጋነነነና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ” ብለዋል፡፡ “እንደ ትግራይ የህልውና አደጋ ተጋርጦብን ያለን ብሔር ነን” ያሉት አቶ ሚካኤል የሚደረገውን የቶርነት ዝግጅት “እንደብሔር ሊመጣብን የተዘጋጀውን አደጋ ለመቀልበስ የሚደረግ” ሲሉ ማብራሪያቸውን ሰትጥዋል፡፡
በብዙ የተተቸውና ሰብዐዊ መብቶችን የሚደፈደጥጥ ነው የተባለውና የሕወሓት ባለስልጣናት እንዲረቅ ያደረጉት አዋጅ ላይም ማብራሪያቸውን የሰጡት አቶ ሚካኤል፤ “አዋጁ የወጣው ሰው ለመግደልና ለማፈን አይደለም” በማለት “አዲስ የተዋቀረ” ያሉት የክልሉ መንግስት ህጋዊነት ለማስፈን ያወጣው እንደሆነ ገፈልጸዋል፡፡

ህወሓት አዲስ የደነገገዉን ሕግ እንዲሽር የቀረበለትን ጥያቄ ዉድቅ አደረገዉ
የህወሓት ፅሕፈት ቤት።መቀሌ።ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

አዋጁ ስላስከተው ስጋት

የትግራይ ሕዝብ ኅልውና እና ደኅንነትንለማረጋገጥ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያወጣው አዋጅ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው አዋጁ፤ ገቢራዊ እንዲሆን ከጸደቀ በኋላ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን ለዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን የገለጹት የክልሉ ነዋሪዎች እና የህግ ባለሙያዎች ባሳለፍነው ሳምንት ገልጸው ነበር፡፡ የክልሉን ፖለቲካዊ ሁናቴ በቅርበት የሚከታተሉት የህግ ባለሙያው አቶ የማነ ካሳ፤ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. አዋጅ 366 ሆኖ በጸደቀው “ጨቋኝ” ያሉት ሕጉ በጦርነት ላይ ከርሞ የተለያዩ ዘርፈብዙ ፈተናዎችን እያሳለፈ የሚገኘውን ማህበረሰብ፤ በተለይም ወጣቱን ሰቀቀን ላይ የጣለ ሲሉ ወቅሰውታል፡፡ “ማንኛው ሰው ሃሳቡን የሚገልጽ አሊያም በሌላ ሰው የተጻፈን ሃሳብ በማህበራዊ ሚዲያ ማጋራት በወንጀል ተጠያቂ የሚደርግ፤ ከጥቅምት 23 ቀን 2013 ጀምሮ አምስት አመታትንም ወደ ኋላ ተመልሶ በመስራት ህግጋትን የጣሰ ነው” ይላሉ፡፡

አዋጁ በአንቀጽ 05 ላይ ማንኛውም እድሜና ጤናው የሚፈቅድለት ሰው ለጦርነት እንዲዘጋጅና ስልጠና እንዲወስድ እንደሚያስገድድም ነው የተገለጸው፡፡ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብት የተሰኘው አገር በቀል ተቋምም በትግራይ አስገዳጅ የጦርነት ምልመላን የሚመስሉ ተግባራት እየተፈጸሙ ነው ብሎ ነበር፡፡
የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል ግን፤ የቀድሞ የህወሓት ባለስልጣናትን በዚህ ተግባር በመክሰስ የቀረበባቸውን ክስ ግን አስተባብለዋል፡፡ “ወጣትን ያስገደዱ ሀራ መሬት ብለው ካምፕ ያቋቋሙ ናቸው” ሲሉም ወንጅለው፤ “ባነሳሳናቸው መጠን የህልውና አደጋ አለ ብለው አምነው ከሚታገል ወጣት ውጪ በአስገዳጅ ሁኔታ የተመለመለ የለም” ይላሉ፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ