ጀርመን 80 በመቶ የሶሪያ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የያዘችው እቅድ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 22 2018
ሥልጣን ከያዙ ባለፈው ህዳር አንድ ዓመት ያለፋቸው የሶሪያ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አህመድ አል-ሻራ ትናንት ለጉብኝት በመጡባት በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ እንዲሁም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር አል-ሻራን ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል። በበርሊን ለአል ሻራ የተደረገው አቀባበል ግን በፖለቲካዋ መዲና በበርሊን በሁሉም ዘንድ በጥሩ አልታየም። በጀርመን ከፍተኛ ስርጭት ያለው ቢልድ የተባለው ጋዜጣ ጉብኝቱን "የአመቱ በጣም አወዛጋቢ የመንግስት ጉብኝት" ብሎታል።
በቀጭን ገመድ ላይ የሚደረግ ጉዞ
የዶቼቬለው የንስ ቱራው እንደዘገበው የአልሻራ የበርሊን ጉብኝት ለጀርመን መንግስት በቀጭን ገመድ ላይ እንደመራመድ የሚቆጠር ነው ። ሶሪያን ለብዙ ዓመታት የገዛው የበሽር አል አሳድ መንግሥት ከአንድ ዓመት ከአራት ወራት በፊት ከመገልበጡ አስቀድሞ የአሁኑ የሶሪያው ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ተከሰው ነበር ። የ43 ዓመቱ አል-ሻራ ቀደም ሲል ከአልቃይዳ የሽብር መረብ ጋር አጋር የነበረው የአል-ኑስራ ግንባር አዛዥ ነበሩ። ያያኔው አማጺ ቡድን መሪ አልሻራና ድርጅታቸው ፣ቀደም ሲል ከአልቃይዳ ጋር ይሰሩ እንደነበርና እሳቸውም በግል በአሸባሪነት ተፈርጀው ስለነበር ፤ ያገኛቸው ወይም ያሉበትን የጠቆመ የ10 ሺ ዶላር ሺልማት እንደሚሰጠው አሜሪካ ማስታወቂያ አውጥታባቸውም ነበር። ይሁን እንጂ የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባዮች ፣የጀርመን መንግሥት በሶሪያ ጉዳይ የሚያነጋግራቸው ዋነኛው ሰው የአሁኑ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ሲያሳውቁ ቆይተዋል። በዚሁ መሠረትም ጀርመን በሶሪያ ትልቁን ስፍራ የምትሰጣቸውን አህመድ አል ሻራን ትናንት በከፍተኛ ክብር ተቀብላ አስተናግዳለች።
አል-ሻራ ከመራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጀርመን የሶሪያው የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ለሶሪያ ሕዝብ ላደረገችው ድጋፍና እስካሁንም ለዘለቀው ወዳጅነት አመስግነዋል። «ከሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሶሪያውያን በሩን ከፍታችኋል፤ ይህም እዚህ ደህንነት እንዲያገኙና ህይወታቸውንም እዚህ እንዲቀጥሉ አስችሏቸዋል ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። አል-ሻራ ሶሪያውያን በጀርመን ቆይታቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለሶሪያ መልሶ ግንባታም የሚያስፈልጉ መሆናቸውን ጠቅሰው ፤ መቆየት የሚፈልጉት ደግሞ ጀርመን መቆየት እንዲችሉ እንዲደረግ ፍላጎታቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
«እዚህ ጀርመን ውስጥ ወደ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ የሶሪያ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ይገኛሉ፤ ወደ 6,000 የሚጠጉ ዶክተሮች አሉ፤ ብዙዎቹም ለጀርመን ኢኮኖሚ በንቃት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ሶሪያውያን ለኅብረተሰቡ አስተዋጽኦ ማድረግን በፍጥነት በመማራቸው እንኮራለን። በአስፈላጊ ሙያዎች ውስጥ ይሰራሉ፤ ከጀርመን መንግሥት ጋር ከወዳጆቻችን ጋር በመሆን እዚህ ላሉት ሶሪያውያን ወደ ሶሪያ ተመልሰው አገሪቱን እንደገና ለመገንባት እንዲችሉ ፣እዚህ ለመቆየት የሚፈልጉ ሰዎች ደግሞ እዚህ መስራታቸውን መቀጠል እንዲችሉ የሆነ መንገድ እንዲኖር እንፈልጋለን።»
«ጀርመን ከሚገኙት ሶሪያውያን ስደተኞች 80 በመቶው በቅርቡ ወደሀገራቸው መመለስ አለባቸው»ሜርስ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ ጊዜ ሳያጠፉ ነበር ከሶሪያ ጋር ባለው ግንኙነት ከጀርመን ፍላጎቶች ዋነኛ የሆነውን ጉዳይ ያነሱት። ከአል ሻራን ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጀርመን ካስጠጋቻቸው የሶሪያ ስደተኞች አብዛኛዎቹ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሀገራቸውን መገንባት እንደሚፈልጉ አውቃለሁ ያሉት ሜርስ፣
በጦርነቱ ሰበብ ጀርመንካስጠጋቻቸው ስደተኞች 80 በመቶ የሚሆኑት ሶሪያውያን በቅርቡ መመለስ አለባቸው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። አል ሻራን ከመካከላቸው ለየትኛዎቹ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። ሜርስ በተለይ ወንጀለኛ ያሏቸውን ሶሪያውያን ሶሪያ በአስቸኳይ ወደ ሀገርዋ እንደምትመልስ አሳስበዋል። ከዚህ ሌላ እዚህ መቆየት የሚችሉ ሆኖም በአገራቸውም የሚፈለጉ ሙያተኞች ጉዳይ ግን ውይይት እንደሚያሻውም መጠቆማቸው አልቀረም። «ፕሬዝዳንት አል-ሻራ ሶሪያውያን ሲቀበሉ በተለይ በጀርመን ውስጥ ትክክለኛ የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸው ሰዎች ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቄያለሁ። እዚህ ላይ ችግር የሚፈጥርብን አነስተኛ ቡድን አለን፣ አሁን በአስቸኳይ ወደ አገራቸው ለመመለስ የምንፈልገው ወንጀለኛ ሶሪያውያንን ያቀፈ ቡድን አለን። ነገር ግን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ጀርመን የሚኖሩት ወደ 80% የሚጠጉ ሶሪያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የፕሬዝዳንት አል-ሻራ ፍላጎት ነበር። »
ሜርስ እንደሚሉት ወደ ሀገራቸው መመለስ ያለባቸው በጀርመን የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ሶሪያውያን ናቸው። ሆኖም እዚህ መስራት የሚችሉ ነገር ግን ሀገራቸው ቢመለሱ ለሀጋራቸውም አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ሶሪያውያን አሉ። በሜርስ አስተያየት በነዚህ ሰዎች ጉዳይ ላይም መነጋገር ያስፈልጋል።
«ከእኛ ጋር የሚኖሩ እና እዚህ መቆየት የሚፈልጉ ሰዎች በሚገባ የተዋሃዱ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንፈልጋለን። ፕሬዝዳንት አል-ሻራ በሆስፒታሎቻችን ውስጥ ከሚሰሩ ዶክተሮች እና ነርስ ሰራተኞች ጋር ተነጋግረዋል፣ እነዚህ ሰዎች በጀርመን ቢቆዩ ጥሩ መሆኑን ጠቁመዋል። ሆኖም እዚህ የሚገኙት ብዙዎቹ በአገር ውስጥ ያስፈልጋሉ። ስለዚህ፣ስለእነዚህ ሰዎች ለመወያየት ትክክለኛው ጊዜ አሁን እንደሆነ አምናለሁ።"
አል-ሻራ በበኩላቸው ጀርመን የሚገኙ የሶሪያ ስደተኞች የጀርመንም የሶሪያም ሀብት መሆናቸውን ገልጸው የኤኮኖሚ ትስስር ድልድይ ሆነው ያገለግላሉም ብለዋል።
«በጀርመን የሚገኙ የሶሪያ ስደተኞችን እንደ ሀብትና ለሁለቱም አገሮች እንደ ሀብት ምንጭ አድርገን ማየት አለብን። በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በሁለቱ አገሮች መካከል የመግባባትና የሃሳብ መለዋወጫ ድልድይ ይወክላሉ፣ ይህም የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር ያስችላል። »
በዚህ ረገድ የጀርመን-ሶሪያ የጋራ ግብረ ኃይል በሶሪያ አሁን እንደ ሆስፒታሎች ግንባታ፣ የውሃ አቅርቦት እና ሶሪያውያንን ወደ አገራቸው መመለስን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ጠንክሮ ይሰራል ተብሏል። በዚህ ረገድ የጀርመን-ሶሪያ የጋራ ግብረ ኃይል በሶሪያ አሁን እንደ ሆስፒታሎች ግንባታ፣ የውሃ አቅርቦት እና ሶሪያውያንን ወደ አገራቸው መመለስ ባሉ ጉዳዮች ላይ ጠንክሮ ይሰራል ተብሏል።መራኄ መንግሥት ሜርስ በትናንቱ መግለጫቸው በዚህ በኩል የጀርመን መንግሥት ከአል ሻራ ጋር የተስማማባቸውን ጉዳዮች ዘርዝረውል ።
"ይህንን የመልሶ ግንባታ ጥረት ከጀርመን መደገፍ እንፈልጋለን። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ፣ አሁን ተግባራዊ እየሆነ ስላለው መልሶ ግንባታ እና ስደተኞችን ለመመለስ ትልቅ የጋራ የስራ መርኃ ግብር አዘጋጅተናል።በተጨማሪም በጀርመን እና በሶሪያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ተስማምተናል። ይህም ለጀርመን ኩባንያዎች ማራኪ የኢንቨስትመንት ሁኔታ መፍጠርን ያካትታል፣ ይህም ሕጋዊ አስተማማኝነትን የሚያረጋግጡ ተገቢ ማሻሻያዎችን በማድረግ እና በሶሪያ መስራት የሚችል አስተዳደር መመስረትን ያካትታል።»
የጀርመኑ ተቃዋሚው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ፣ሜርስ ከ80 በመቶ በላይ ሶሪያውያንን ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ ማሳወቃቸውን አጥብቆ ተችቷል። የፓርቲው መሪ ፍራንዚስካ ብራንትነር እንደተናገሩት ሜርስ ዝም ብለው ቁጥሮችን ይወርወሩ እንጂ ብዙዎቹ ሶሪያውያን ስደተኞች በአሁን ጊዜ ከጀርመን ማህበረሰብ ጋር በጥልቀት የተዋሀዱ ናቸው ። እርሳቸው እንዳሉት ከመካከላቸው ከግማሽ በላይ የሚሆኑትም በጀርመን ስርዓት አስፈላጊ በሆኑ ሙያዎች ውስጥ ተሰማርተዋል።
ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉት ጀርመን የሚገኙ የሶርያ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ይመለሱ የሚለው ሀሳብ ከወራት በፊት በጀርመን መንግሥት ውስጥ ሳይቀር ውዝግብ አስነስቶ ነበር። የሶሪያው የርስ በርስ ጦርነት በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓም ሲጀመር ጀርመን ከገቡት አብዛኛዎቹ ስደተኞች መካከል 700 ሺሁ እንደ ተገን ጠያቂዎች ይቆጠራሉ።
የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ መሪ የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስና ከርሳቸውም በላይ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ አባል የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዶብሪንት የሶሪያ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ ስልጣን እንደያዙ የርስ በርስ ጦርነቱ በይፋ ስላበቃ ሶሪያውያን ወደ ሀገራቸው መመለስ አለባቸው የሚል ክርክር አነሱ። ይሁንና የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ አባሉ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቋም ደግሞ ከነርሱ የተለየ ነበር።
ባለፈው ጥቅምት ሶሪያን የጎበኙት ሚኒስትር ቫደፉል ከዋና ከተማይቱ ደማስቆ ወጣ ያሉ አካባቢዎችን ካዩ በኋላ «በእውነት እዚህ ማንም ክብሩ ተጠብቆ መኖር አይችልም» ሲሉ አስተያየት መስጠታቸው ከወግ አጥባቂ ፖለቲከኞቻቸው በኩል ጥብቅ ተቃውሞን አስነስቶ ነበር ። ቫደፉል በዚህ ብቻ ሳያበቁ ቆይተው የክርስቲያን ዴሞክራቶች እና የሶሻል ዴሞክራቶች ኅብረት ፓርቲ የፓርላማ አባላት ቡድን የጋራ ስብሰባ ላይ በሰጡት አስተያየት ሶሪያ አሁን ጀርመን በጎርጎሮሳዊው 1945 የሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ከምትገኝበት ሁኔታ የከፋ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው ሲሉም ተናግረው ነበር።
በአል ሻራ የበርሊን ጉብኝት ወቅት የተነሱ ጉዳዮችም ከአረንጓዴዎቹ ፓርቲ በኩል ተቃውሞ ተሰንዝሮበታል። የአረንጓዴ ፓርቲ የፓርላማ አባል እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባለሙያ ሉዊዝ አምትስበርግ ሜርስ "በሶሪያ ላይ ሀገሪቱ የምትከተለውን ፖሊሲ እዚህ የሚገኙ ሶሪያውያን ወደማባረር ጉዳይ ዝቅ አድርጎ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ችላ ብሏል" ሲሉ ተችተዋል። አምትስበርግ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "...በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ የተባባሰው ወታደራዊ ግጭት እና በቅርቡ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች አናሳዎች ላይ የደረሱት እልቂቶች ሶሪያ ደኅንነትዋ ያልተጠበቀ መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ ብለዋል። የግራ ፓርቲው የሶሪያን መሪ ጉብኝት "ቅሌት" ሲል ጠርቶታል። ለስደተኞች መብት የሚታገለው ፕሮ አዙል የተባለው ድርጅት በበኩሉ የጀርመን መንግስት በሶሪያ ላይ ያለው ዋና ትኩረት በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን ወደ ትውልድ አገራቸው ማፈናቀሉ ላይ መሆኑ ያስፈራኛል ብሏል።
ሜርስ በትናንቱ የአል ሻራ ጉብኝት ወቅት ሶሪያውያን ለሀገራቸው ግንባታ ያስፈልጋሉ ። 80 በመቶ ሶሪያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የአልሻራም ፍላጎት ነው ማለታቸው ከሌላ የፓርቲያቸው አባል በኩል ተቃውሞ ቀርቦበታል። እነዚህን መሰል አሀዞችን እየጠቀሱ ህዝቡ ከመጠን በላይ እንዲጠብቅ ማድረግ ብልህነት እንዳይደለ የሜርስ ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ቃል አቀባይ ሮደሪሽ ኪስቬተር ተችተዋል። እርሳቸው እንዳሉት ይህ ለቀኝ ጽንፈኛው ለ«አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ» በጀርመንኛ ምህጻሩ AfD ድንጋይ ማቀበል መሆኑ አይቀርም። ሌላው የመንግስት ተጣማሪው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የSPDው የዛርላንድ ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትር አንከ ሬህሊንገርም የኪስቬተርን ሀሳብ ተጋርተዋል። ሶሪያውያን በጀርመን ኤኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ነው ያሉት የSPD ፖለቲከኛ ሰዎች ብዙ እንዲጠብቁ የሚያደርግ የጊዜ ገደብ ለክቶ አሀዞችን መጥቀስ ብልህነት እንዳይደለ በተለይ የተባለው ባይሳካ ደግሞ ችግር ማስከተሉ እንደማይቀር አስገንዝበዋል።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽመሐመድ