የድህረ ምርት ብክነት
ረቡዕ፣ ጥር 13 2018
የድህረ ምርት ብክነት አጠቃላይ ገፅታ
የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ FAO ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው በየዓመቱ 1.3 ትሪልዮን ቶን የምግብ ምርት ይባክናል። ይህ የምግብ ብክነት ምርቱ በሚመረትበት ጊዜ፣ በሚሰበሰብበት፣በመጋዘን አቀማመጥና ለተጠቃሚ በሚጓጓዝበት ጊዜ ባሉ ሰንሰለቶች በተለያየ መጠን የሚታይ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር «የምግብ ደህንነትና ጥራት እና የድህረ ምርት አያያዝ ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት» በሚል ርዕስ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ በድህረ ምርት የአያያዝ ጉድለት ምክንያት ከሚመረተው ሰብል በአማካይ ከ20 እስከ 30 በመቶ፤ በሆርቲካልቸር ማለትም አበባን ጨምሮ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች ከ30 እስከ 50 በመቶ፤ በእንስሳት ምርት እስከ 40 በመቶ ብክነት እንዳለ አመላክቷል። ከዓለም አቀፍ የእንስሳት ግብይት አንጻርም በአመት ከ723 ሚልዮን ዶላር በላይ አገሪቱ እንደምታጣ በማከል።
የድህረ ምርት ብክነት ምንነት
ዶክተር ተክለወይኒ ገብረመድህን የምጣኔ ሐብት ባለሙያና በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በጀርመን አገር ሙዩኒክ ከተማ በሚገኘው የዶይች ባንክ ይሰራሉ። ለመሆኑ የድህረ ምርት ብክነት ሲባል ምንድነው? አልናቸው።
« አንድ ምርት በአርሶ አደሮች ከተመረተ በኋላ ለረዥም ጊዜ ሳይባክን ለተጠቃሚዎች ወደ ገበያ በማቅረብ ያሉ ሂደት ሰንሰለቶች ናቸው የድህረ ምርት አያያዝ የሚባሉት።»
በቅድመ ምርት ያሉ ህጸጾች እንደ ብክነት ባይታዩም የምግብ ምርትን ከፍ በማድረግና በጥራቱ፣ በብዛቱ እንዲሁም በምግባዊ ይዘቱ ላይ ግን ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥሩ የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ይናገራሉ። ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የግብርና ፖሊሲ፤ የአየር ለውጥ የሚያስከትለውን የዝናብ እጥረት፣ የማዳበሪያና የጸረ ተባይ ኬሚካል አቅርቦት፤ የባለሙያ ክትትልና ድጋፍ፣ ጦርነትና ግጭት በቅድመ ምርት የሚከሰቱን ምርታማነትን ከሚጎዱ ዋናዋናዎቹ መሆናቸውን ባለሙያው አክለዋል።
የድህረ ምርት ብክነት የሚባለው በግል ከሚያርሰው ገበሬ ማሳ ይሁን በማሽኖች የተደገፈ ሰፋፊ መሬቶች ከሚያርሱ ባለሐብቶች፤ ከምርት መሰብሰብ ጀምሮ ለተጠቃሚው እስኪደርስ ባለው ሰፊ ሰንሰለት ላይ የሚከሰት እንደሆነ ዶክተር ተክለ ወይኒ ያስረዳሉ።
« ለገበሬው ለራሱ ፍጆታ ከሆነ በቤተሰብ ደረጃ እንዴት ነው የሚጠቀመው? ወደ ተጠቃሚዎች ወደ ገበያ የሚያቀርበው ከሆነ ደግሞ በምን መልኩ? በሚለው ላይ ነው ክፍተቶች የሚፈጠሩት። ለምሳሌ ብሰጥህ ስቶሬጅን ማንሳት ትችላለህ። ምርቱን የሚያሰባስብበት አኳኋን ብክነት ሊያስከትል ይችላል። እነዚህ የተለያዩ ተህዋስያን የሚያስከትሉት ብክነት አለ። በአጠቃላይ የተገኘው ምርት ለተጠቃሚው ከፍተኛው ጥቅም ማስገኘት ሲገባው ያንን ሳታደርግ ስትቀር የሚፈጠር ክፍተት ነው።»
ስለሚወጡ መረጃዎች
የምግብ ደህንነትና ጥራት፣ እንዲሁም የድህረ ምርት አያያዝ ላይ ያሉ ተግዳሮቶች በሐገራዊ ልማት፣ በምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደሚገኙ የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል።በአንጻሩ ደግሞ የመንግስት ባለስልጣናት፤ ኢትዮጵያ በተለይም የስንዴ ምርት ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች የሚሉ መግለጫዎች ሲሰጡ ይደመጣሉ። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ተክለወይኒ በመንግስት ባለስልጣናት የሚወጡ መረጃዎች ስለትክክለኛነታቸው አብዝተው ይጠራጠራሉ።
«እነዚህን በአጠቃላይ በፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲህ አይነት ችግሮችን በእንዲህ አይነት ለመፍታት፤ ከዚህ ጀምሬ እዚህ ለመድረስ ይሄን ዕቅድ አዘጋጅቻለሁ የሚል ሰነድ እንኳን አታገኝምኮ። በዛ ፈንታ የምታየው ምንድነው? የመንግስት ሃላፊዎች በየጊዜው እየወጡ ሚራክል ኢኮኖም አስመዘገብን እያሉ ታያለህ፤ አሁን ይሄ ምን ልትለው ትችላለህ? ይህ ዳታ አደለም፤ ፋክት አደለም፤ ቁጥር አደለም። እሚጨበጥ የሚያዝ ነገር የለውም። ለዚህ ነው እንደባለሙያ እነዚህን መሰረት ባደረገ ትንተና ለመስጠት ሰው ሚቸገረው ማለት ነው።»
ይበጃሉ የተባሉ መፍትሔዎች
የግብርና ሚኒስቴር የምግብ ደህንነት ጥራትና የድህረ ምርት አያያዝ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ከመሰረቱ በመፍታት በምግብና ሥርአተ ምግብ ፅሕፈት ቤት አስተባባሪነት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የ7 ዓመታት ማለትም እአኣ እስከ 2030 የትግበራ ጊዜ ያላቸው 3 ስትራተጂዎች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ መገባቱን በሰነዱ አመላክቷል። ስትራተጂዎቹም ብሔራዊ የምግብ ደህንነትና ጥራት ለተቀዳሚ ግብርና ምርቶች፤ ብሔራዊ የድህረ ምርት አያያዝና የብሔራዊ የድህረ ምርት አያያዝ እንዲሁም ብሔራዊ የሥርዓተ ምግብ ተኮር የግብርና ምርት ስርዓት ስትራተጂዎች መሆናቸውን ዘርዝሯል፤ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ።
የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ዶክተር ተክለወይኒ የቅድመ ምርት የግብርና ማሳደጊያና የድህረ ምርት ብክነትን በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚቀረጹ ፖሊሲዎች ከፖለቲካ ትርፍ የዘለሉ፣ በመንግስታት መቀያየር ከባዶ የማይጀምሩ፤ ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላትን ያሳተፈና ውጤታማነቱን የተረጋገጠ ፖሊሲ መቅረጽ ያስፈልጋል ይላሉ።
« የመጀመሪያው የፖሊሲ ማዕቀፎች ናቸው የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት ። ሐገሪቱ አንድ ተከታታይነት ያለው፤ ከሥርአቶች ጋር የማይለዋወጥ ፖሊሲ ሊኖራት ይገባል። የፖለቲካ ትርፍ የሚገኝበት አውድ ተደርጎ ሳይወድ ሊሂቃኖች፣ ባለሙያዎች ተሰብስበው ድራፍት የሚያደርጉት፤ በሰፊው ውጤታማነቱን የተረጋገጠ፤ ሁሉን የባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መንግስትንም ጨምሮ ማለቴ ነው ይህ ቀዳሚ ይመስለኛል።»
እንደ የድህረ ምርት ብክነት ሁሉ በቅድመ ምርት ላሉ ሥራዎችም ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ባለሙያው ይመክራሉ። የማዳበርያ አቅርቦትን ጨምሮ ምርትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ግብአቶችን ለግብርናው ዘርፍ ተዋናዮች በአግባቡና በወቅቱ ማድረስ እንደሚያስፈልግ በማከል።
«ከአርሶ አደሩ ጀምረህ እስከ የግል ሴክተሩ ምርትን የሚያሻሽሉ የምርት ግብአቶች አቅርቦት ብዙ ሥራዎች መሰራት ያለባቸው ይመስለኛል።»
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ