1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«የኦሮሞ ታሪክ በተጨባጭ ማስረጃ መደገፍ ይኖርበታል» ምሑራን

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ሚያዝያ 16 2018

በኢትዮጵያ ውስጥ «ተዛብተው ተጻፉ» የተባሉትን አንዳንድ የታሪክ መዛግብት በማስረጃ በማስደገፍ አርሞ የመጻፍ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኦሮሞ ምሁራን ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/5Cm6D
የኦሮሞ ምርምር ማሕበር ጉባኤ
የኦሮሞ ምርምር ማሕበር ጉባኤ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

«የኦሮሞ ታሪክ በተጨባጭ ማስረጃ መደገፍ ይኖርበታል» ምሑራን

 

በኢትዮጵያ ውስጥ «ተዛብተው ተጻፉ» የተባሉትን አንዳንድ የታሪክ መዛግብት በማስረጃ በማስደገፍ አርሞ የመጻፍ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኦሮሞ ምሁራን ተናግረዋል። የኦሮሞ ምርምር ማሕበር (ORA) ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የባህል ጥናት ምርምር ማዕከል ጋር ለሁለት ቀናት አዲስ አበባ ውስጥ ባዘጋጁት ጉባኤ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል። ትናንት ሐሙስ ሚያዚያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. የተጠናቀቀውን መድረክ በማስመልከት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ምሁራን የኦሮሞን ታሪክ በማስረጃ «በትክክል» ለመጻፍ የተጀመረው እንቅስቃሴ ለክርክር ሳይሆን መግባባት ለመፍጠር ነው። ታርሞ እንዲጻፍ ይሠራል ያሉት የታሪክ ጭብጦችም በማስረጃ እንዲደገፉና ተዓማኒ እንዲሆኑም በትኩረት እንደሚሠራባቸው ነው የተነገረው።

ከሦስት ዓመታት ግድም በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የተቋቋመው የኦሮሞ ምርምር ማሕበር (ORA) ባለፉት ሁለት ቀናት አዲስ አበባ ላይ ከአገር ውስጥ እና ከተለያዩ ሃገራት ምሁራንን በማሳተፍ 2ኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤውን አካህዶ ትናንት ሐሙስ አጠናቋል። የኦሮሞ ባህል፣ ታሪክ እና አገር በቀል እውቀቱን በማጥናት በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተጽእኖ ላይ እውቀት ለመጨመር ተቋቋመ የተባለው ማሕበሩ በሰሞነኛው ጉባኤው 24 ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበውበት ተመክሮባቸዋል።

«ኦሮሞ ከሰሜን ወደ ደቡብ ነው የፈለሰው»

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ፕሮፌሰር እና የምርምር ማሕበሩ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፈሰር በቀለ ጉተማ በተለይም ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት የምርምር ማሕበሩ በኢትዮጵያ ተዛብቶ ተጽፏል ያሉት ኦሮሞን የተመለከቱ ታሪኮችን በማስረጃ ደግፎ አርሞ መጻፍ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ «ሆን ተብሎ ኦሮሞን ወደ ዳር የመግፋት ሥራ ነው የተካሄደው» ያሉት ፕሬፈሰር በቀለ፤ ኦሮሞ ከውጭ ነው የመጣው በሚል ጭምር የተጻፈው ታሪክ ማስረጃ አልባ ነው ሲሉ ገልጸዋል። «እሱን እያሸነፍነው ነው» በማለት የኦሮሞ ሕዝብ አገር በቀል አለመሆን ላይ ማስረጃዎች አለመኖራቸውንም ገልጸው፤ «እንደውም መጀመሪያ ኦሮሞ ከደቡብ ወደ ሰሜን ሳይሆን ከሰሜን ወደ ደቡብ የተንቀሳቀሰ ነው» በማለት በዚህ ላይ ጥናቶች በማስረጃ መቅረባቸውን ጠቁመዋል። ከውጭ ወጥተው የኦሮሞን ታሪክ ያጠኑ አሳሾች የኦሮሞን ታላቅነት መስክረዋል ነው ያሉት።

ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ
ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማምስል፦ Seyoum Getu/DW

«የተዛባን ታሪክ በማስረጃ ለማረም እየጣርን ነው»

በተቃራኒው ግን አንዳንድ የአገር ውስጥ ጸሐፊዎች የኦሮሞን ታሪክ ያለ በቂ ማስረጃ አዛብተው መጻፋቸውን ገልጸው፤ ይህ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውንም ሕዝብ እንደማይመለከት አስረድተዋል። «ይሄ ለምን ሆነ የሚለው፤ ምናልባት በመሃል አገር ትልቅ የተፈጥሮ ሃብት ላይ ስለሆነ የገዢመደቦች ተጠቃሚ ለመሆን ያደረጉት አካሄድ ይመስለኛል» በማለትም፤ ይህ ማንም ሕዝብ ላይ ያተኮረ ግን እንዳልሆነ በአስተያየታቸው አክለዋል። ይህን የሥራው በተወሰነ መልኩም ቢሆን እራሱ የኦሮሞ ሕዝብ እና ሌሎችም ያሉበት የገዢ መደብ የሠራው ነገር በመሆኑ፤ ይህንን በትክክል ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ተመሳሳይ አስተያየታቸውን በዚህ ላይ ያጋሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ እና የድህረ ምሬቃ ተማሪዎችን የሚያማክሩ ፕሮፌሰር ተሰማ ተዓ ናቸው። እንደሳቸውም አስተያየት ከ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በፊት በምሥራቅ አፍሪካ ነባር ሕዝብ የሆነው ኦሮሞ፤ ከሰሜን የ ኢትዮጵያ ክፍል ወደ መሃል እና ደቡብ የአገሪቱ ክፍል መንቀሳቀሱን የሚያሳዩ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉ። «በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚባለው የኦሮሞ እንቅስቃሴ ከደቡብ ወደ ሰሜን ሲሆን ከዚያ በፊት ከሰሜን ወደ ደቡብ በሚደረግ እንቅስቃሴ በሰሜን በነበሩት ውስጥ ተሰራጭቶ የኖረ መሆኑን ነው በምርምር ያረጋገጥነው» ብለዋል። «ከውጭ መጣ ከማዳካስካር መጣ የሚሉት በስነመንግሥት ውስጥ ተቀምጠው ተረትና ትርክት የጻፉት ናቸው» በማለት ለዚያ የታሪክ ማስረጃ ማቅረብም እንደማይቻል ተናግረዋል።

 ፕሮፈሰር ተሰማ ኦሮሞ ከሌሎች ሕዝብም ጋር በጉዲፈቻ እና ሞጋሳ ብዙ ጊዜ የቆየ ሕዝብ መሆኑን ታሪክ ማስረጃ አለው ነው ያሉት።

ታሪክ በማስረጃ መደገፍም አለበት የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ተሰማ ተዓ፤ «የኦሮሞን ታሪክ ዳግም ስንጽፍ ለዚህ ትኩረት በመስጠት ነው» ብለዋል። «ተረት ተረት አይደለም። ተጨባጭ ምንጭ እየተጠቀምን ነው ምንሠራው እኛ። በጥንቃቄ ነው የምንሠራው። ጭቅጭቅም ለመፍጠር አይደለም። ኦሮሞ እንዴት ነው እዚህ የደረሰው የሚለውን ለማረጋገጥ ብቻ ነው» በማለት እየጣሩ ያሉት የተዛባ ያሉትን ታሪክ ለማረም ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ በቃል፣ ከነገሥታት ጤና መዋዕል ውስጥ የተሰነዱ ማስረጃዎች በጥቅም ላይ እንደሚውሉ አስረድተዋል፡፡ ጥረቱ ትልቅ ሕዝብን የሚመጥን በማስረጃ የተደገፈ ታሪኩን ለመጻፍ እንጂ ተረት ተረት ለማውራትም አይደለም ሲሉም በምርምር ማሕበሩ እየተከናወነ ነው ያሉትን ሥራ ዘርዝረዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ