እስካሁን የተቋረጠ የአገር ውስጥም ሆነ ዓለማቀፍ በረራ አለመኖሩንም ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
ማክሰኞ፣ መጋቢት 22 2018
ኢትዮጵያ አየር መንገድ በመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ጦርነት ምክንያት ያቋረጣቸውን በረራዎች ወደ ሌላው ዓለም ባሉ መዳረሻዎች በረራውን በማጠናከር ከዚህ አከባቢ የሚያጣውን ገቢ ለማካካስ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
አየርመንገዱ የመካከለኛውን ምስራቅ ወቅታዊ ሁኔታ እየቃኘ በተወሰኑ አገራት የሚያደርገውን በረረራዎች ዳግም መጀመሩንም አመልክቷል፡፡
ባጋጠመው የነዳጅ አቅርቦት ችግርም የአየርመንገዱ መደበኛ በረራዎች እንዳይቋረጥ የአውሮፕላን ነዳጅ በሌላ አማራጭ የማቅረቡ ስራን የኢትዮጵያ መንግስት እየሰራበት ነው ተብሏል፡፡
የመካከለኛውን ምስራቅ ፈተና በሌሎች በረራዎች ለማካካስ
አንድ ወር ባስቆጠረው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት እጅግ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ከገቡ ዘርፎች የአቪየሽን ኢንደስትሪው ዘርፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህም ወደ አከባቢው የሚበሩ በርካታ የአውሮፕላን በረራዎች ተቋርጧል፡፡ የኢትዮጵያ አየርመንገድም በዚሁ በገልፍ እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ሲያደርግ የነበረውን በርካታ በረራውን በጊዜያዊነት መግታቱ ይታወሳል፡፡ ይህ አየርመንገዱ በሚያጓጉዛቸው የመንገደኛው ቁጥር ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ማምጣቱን ለዶይቼ ቬለ የገለጹት የአየርመንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ በዚህ ያጣውን ገቢ ግን በሌሎች መዳረሻዎች ለማካካስ እየጣረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “የበረራው መቋረጥ በመንገደኛ ቁትራችን ላይ የተወሰነ ተጽእኖ አሳድሯል” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ይሁን እንጂ አየርመንገዱ በሚበርባቸው ሌሎች ዓለማቀፍ መዳረሻዎች ላይ ያለውን በረራዎች በማጠናከር ከመካከለኛው ምስራቅ ያጣውን የመንገደኛ ቁጥር በሌሎች በረራዎች በተወሰነ ደረጃወም ቢሆን ለማካካስ እየተሞከረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በረራ ዳግም የተጀመረባቸው
በመካከለኛው ምስራቅ እና ገለፍ አገራት ዙሪያ እያሰጋ ያለው ጦርነት ሁኔታው እየታየ በተወሰነ መልኩ በረራ እየተጀመረባቸው ያሉ አገራትም ስለመኖራቸው አቶ መስፍን በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡ “የመሻሻል ነገሮች በምናይባቸው አከባቢዎች በተወሰነ ደረጃ እንደገና አስጀምረናል” ያሉት የኢትዮጵያ አየርመንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በረራ ተቋርጦ ከነበረባቸው አከባቢዎች መካከል አሁን ዩናትድ አረብ ኢምሬትስ፤ ዱባይ፣ አቡዳቢ፣ ሻርጂያ በቀን በእያንዳንዳቸው ከተሞች አንዳንድ በረራዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሳውድ አረቢያ ምስራቃዊ አስተዳደር ከተማ ወደ ሆነችው ደማም እና ጆርዳን-አማን ተቋርጠው የነበሩ በረራዎች አሁን በአንዳንድ እለታዊ በረራዎች ዳግም መጀመራቸውንም አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡
በረራ ተቋርጦ የቀጠለባቸው
አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ አየርመንገድ በረራ ዳግም ያልጀመረባቸው የመካከለኛ ምስራቅ እና ገልፍ አገራት መዳረሻዎች በርካታ ናቸው፡፡ አቶ መስፍን “ዶሃ-ቋታር፣ ባህሬን፣ ቁየት፣ እስራኤል-ቴላቪቭ እና ቤሩት አየርመንገዱ አሁንም በረራ እንዳቋረጠባቸው ቀጥሏል” በማለት በነዚህ አከባቢዎች በቂ የመረጃ ትንተና ተደርጎ ለበረራ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ስባል ብቻ እንደሚበሩ ገልጸዋል፡፡
የነዳጅ አቅርቦት ፈተናውን ለመቋቋም
የመካከለኛውን ምስራቅ ጦርነት ተከትሎ በበርካታ አገራት ላይ ደንቃራ የሆነው ሌላው ጉዳይ ከነዳጅ አቅርቦት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግን በዚህ በነዳጅ እጥረት በረራውን እንዳያቋርጥ አስቀድሞ አማራጭ መፍትሄዎች ተፈልጎለታልምነው የተባለው፡፡ “ግጭቱ በአቪየሽን ኢንደስትሪው ላይ ያደረሰው ሌላው ተጽእኖ ከነዳጅ አቅርቦት ጋር የተያያዘ ነው” ያሉት አቶ መስፍን ከገልፍ አገራ የሚመጣው የአውሮፕላን ነዳጅ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል የኢትዮጵያ መንግስት ለአየርመንገዱ ከአማራጭ ቦታዎች ነዳጅ እያቀረበ ነው ብለዋልም፡፡
እንዲያም ሆኖ ጦርነቱ ባስከተለው የበረራ እና ነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል አየርመንገዱ የተወሰኑ በረራዎች ላይ ማስተካከያዎች በማድረግ፤ ሲበርባቸው በነበሩ ቦታዎች ሁሉ እንዲበር እየተደረገ ነውም ተብሏል፡፡ በአስገዳጅ የጦርነቱ ሁኔታ ምክንያት ከተቋረጡ የገልፍ አገራት በረራዎች በተጨማሪ ግን፤ በነዳጅ አቅርቦት እጥረቱ ምክንያት እስካሁን የተቋረጠ የአገር ውስጥም ሆነ ዓለማቀፍ በረራ አለመኖሩንም ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
በነዳጅ ጭማሪው የሚመጣ የአውሮፕላን በረራ ዋጋ
ኢንደስትሪው ላይ የተደቀነውንየነዳጅ ዋጋ ከፍ ማለትንምለመወጣት አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚው፤ “በኢንስትሪው ውስጥ ባለው አሰራር የነዳጅ ዋጋ በጣም ከፍ ሲል ያንን በከፊል ለማስተካከል የሚጨመር የነዳጅ ፕሪሚየም የሚባል አለ፤ ያ በተወሰነ ደረጃ ስለተጨመረ በሁሉም አየርመንገዶች ተጨመሯል” በማለት ይህ እርምጃም የተወሰደው በዓለማቀፍ በረራዎች ላይ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አየርመንገድ ጥገና ክፍል (MRO) ከአፍሪካ አየርመንገዶች ማህበበር (AFRAA) ጋር በመተባበር ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥባዘጋጀው ኮንፈረንስ በአፍሪካ አውሮፕላኖችን መጠገን ስለሚቻልበት እድል ተመክሯል፡፡ በዚህም የአፍሪካ አየርመንገዶችን የሚፈትኑ ተግዳሮቶች ላይ ጠንካራ ውይይት ተደርጎ የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጡን የኢትዮጵያ አየርመንገዶች ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አስረድተዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ነጋሽ መሐመድ