1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ማንን ይጫናል?

ዓርብ፣ ሚያዝያ 8 2013

በኢትዮጵያ አገልግሎት የሚሰጡና በምሥረታ ላይ የሚገኙ ባንኮች የተከፈለ ዝቅተኛ ካፒታል ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወስኗል። ባንኮቹ የተከፈለ የካፒታል መጠናቸውን 5 ቢሊዮን ለማድረስ የተለያየ የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ ቀደም የተከፈለ ዝቅተኛ ካፒታል መጠን ከፍ ሲል በምሥረታ ላይ የነበሩ ባንኮች ፈርሰው ነበር።

https://p.dw.com/p/3s8as
Video Still TV Magazin The 77 Percent
ምስል DW

የባንኮች የተከፈለ ዝቅተኛ ካፒታል ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ተወስኗል

የባንኮች የተከፈለ ዝቅተኛ ካፒታል ከዚህ ቀደም ከነበረበት ሁለት ቢሊዮን ብር ወደ 5 ቢሊዮን ከፍ እንዲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሚያዝያ 4 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ባስተላለፈው መመሪያ ወስኗል። በመመሪያው መሠረት በሥራ ላይ የሚገኙ ባንኮች የተከፈለ ዝቅተኛ ካፒታላቸውን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እስከ ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ቀነ-ገደብ ሰጥቷቸዋል። 

የገንዘብ አስተዳደር ባለሞያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት በሥራ ላይ ከሚገኙት ባንኮች «ትልልቆቹ» የተከፈለ ዝቅተኛ የካፒታል መጠናቸውን አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ ባይቸገሩም የሚፈትናቸው መኖራቸው አይቀርም። 

አቶ አብዱልመናን «ተለቅ ተለቅ ያሉትን ባንኮች ላያስቸግር ይችላል። አምስት ዓመትም ተሰጥቷቸዋል። ነገር ግን በሥራ ላይ ከሚገኙት በ2010 እና 2011 ገደማ ለተቋቋሙ ትንንሾቹ ባንኮች በጣም ፈታኝ ሊሆን ይችላል። አብዛኞቹ ካፒታላቸው ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ገደማ ነው» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ በምሥረታ ላይ የሚገኙትን ባንኮች ጭምር ይመለከታል። በአገሪቱ 20 ገደማ ባንኮች ገበያውን ለመቀላቀል በሒደት ላይ ናቸው። በመመሪያው መሠረት እነዚህ በምሥረታ ላይ የሚገኙት ባንኮች ሥራ ከሚጀምሩበት ቀን አንስቶ ባሉት ሰባት ዓመታት የተከፈለ ዝቅተኛ ካፒታላቸውን 5 ቢሊዮን ብር ማድረስ ይጠበቅባቸዋል። 

«ከአማራ ባንክ በስተቀር አሁን በመቋቋም ላይ ያሉት ሌሎቹ 500 ሚሊዮን ብር ለማሟላት እየታገሉ ያሉ ስለሆነ በሰባት ዓመት አምስት ቢሊዮን ብር ይደርሳሉ ተብሎ የሚታሰብም አይደለም። አምስት ሚሊዮን ብሩን ያላሟሉት የሰባት ዓመቱን ተጠቃሚ ለመሆን አምስት መቶ ሚሊዮኑን በስድስት ወር ውስጥ ማሟላት አለባቸው። አለበለዚያ ማሟላት ያልቻሉ እንደሆነ ልክ ባለፈው እንደሆነው መፍረስ ነው የሚሆነው። ከዚህ በፊትም ማሟላት ስላልቻሉ የተወሰኑ ባንኮች ፈርሰዋል» ይላሉ አቶ አብዱልመናን። 

ኢትዮጵያ ለተጨማሪ 20 ባንኮች ገበያ አላት?

በኢትዮጵያ ገበያ 16 የግል እና ሁለት የመንግሥት ባንኮች በሥራ ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው ሁሉም ባንኮች በአጠቃላይ 6 ሺሕ 511 ቅርንጫፎች አሏቸው። ከእነዚህ መካከል 70.5 በመቶው የግል ባንኮች ቅርንጫፎች ናቸው። ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ባንኮች 34.1 በመቶው ቅርንጫፎች በአዲስ አበባ ከተማ ይገኛሉ። 

ከዐሥር ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በርከት ያሉ ባንኮች ተመስርተው ወደ ገበያው ለመግባት ሲንደረደሩ የተከፈለ ዝቅተኛ የካፒታል መጠን ከ75 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር ከፍ እንዲል አድርጓል። ጭማሪው «በጣም ትልቅ» እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አብዱልመናን ውሳኔው በወቅቱ ምሥረታ ላይ የሚገኙትን እንዳፈረሰ ተናግረዋል። 

«ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2011 ዓ.ም. ዐሥር ባንኮች አካባቢ የተመሠረቱበት ጊዜ ነበር። ብሔራዊ ባንክ የብዙ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው መግባት አሳስቦት ነው በአንድ ጊዜ የጨመረው። በዚህም በምሥረታ ላይ የነበሩት ብዙ ባንኮች ፈርሰዋል» የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው የአሁኑ ውሳኔም ተመሳሳይነት እንዳለው ያምናሉ። 

Äthiopien Addis Abeba Tsehay Insurance & Nib Bank
ባንኮቹ የተከፈለ የካፒታል መጠናቸውን 5 ቢሊዮን ለማድረስ የተለያየ የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል።ምስል DW/E. Bekele Tekle

«ባለፉት ሦስት ዓመታት በጣም ብዙ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው እየመጡ ናቸው። ምን አልባት አሁን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ባንኮች ቁጥርን ያህል የሚሆኑ እየተመሠረቱ ነው። የእነዚህ ሁሉ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው መግባት ለኢንዱስትሪው ጤንነት እና መረጋጋት በጣም አሳሳቢ ስለሆነ ብሔራዊ ባንክ ያደረገው ካፒታሉን በመጨመር ሌሎች እንዳይቀላቀሉት በር መዝጋት ነው» ሲሉ አመክንዮውን አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ አጠቃላይ ካፒታል እስከ ግንቦት 2012 ዓ.ም. ወደ 112 ቢሊዮን ብር አድጓል። በመንግሥት እጅ ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገበያው ያለው ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነው። የባንኮች፣ የቅርንጫፎቻቸው እና አጠቃላይ ካፒታላቸው ከዓመት ዓመት ዕድገት ቢያሳዩም አቶ አብዱልመናን ግን አገልግሎቶቻቸው «መሠረታዊ» ሆነው እንደዘለቁ ይተቻሉ። 

አቶ አብዱልመናን «የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በጣም መሠረታዊ ነው። የቁጠባ አገልግሎት፣ ሐዋላ፣ ኤልሲ መክፈት የመሳሰሉ አገልሎቶች ላይ ያተኮረ የተለየ ነገር የሌለው ነው። ባንዴ ባንክ መሥርቶ ኢንደስትሪ ውስጥ መግባት የሚቻለውም የተለየ አገልግሎት ስለሌለው እና በጣም ተመሳሳይ ስለሆነ ነው። በጣም የተለየ አገልግሎት የሚቀርብበት ቢሆን ኖሮ እንደሌላው ዓለም በቀላሉ የምትገባበት አይሆንም። በቀላሉ በሚገባበት እና ብዙ ባንኮች ኢንዱስትሪው ውስጥ በሚገቡበት ሰዓት ውድድር ይኖራል። ውድድሩ ሲጠነክር የብድር አሰጣጥ አገልግሎቱ ብልሃት የተሞላበት ላይሆን ይችላል። ይኸ ውድድር ደግሞ የፋይናንስ አለመረጋጋት የመፍጠር ነገር አለው» ሲሉ ተናግረዋል። 

በገበያው ሥራ የሚያከናውኑትም ሆነ በምሥረታ ላይ የሚገኙት ባንኮች የተከፈለ ዝቅተኛ ካፒታላቸውን ለማሳደግ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ዕቅድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቅረብ እንዳለባቸው በዚሁ ሳምንት የተላለፈው መመሪያ አሳስቧል። 

እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ