1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ለተጨማሪ 20 ባንኮች ገበያ አላት?

ረቡዕ፣ ጥቅምት 11 2013

የፋይናንስ ገበያውን ለመቀላቀል ሒደት የጀመሩት በሙሉ ከተሳካላቸው የኢትዮጵያ ባንኮች ቁጥር ወደ 38 ከፍ ሊል ይችላል። የቁጥር መብዛት በውድድርና አገልግሉት አሰጣጥ ምን ይዞ ይመጣል? ዶክተር ደረሰ መርሻ የኢትዮጵያ ባንኮች "ቁጥራቸው በዛ እንጂ አቅማቸው አምስቱ ባንኮች ከሌሎች አገሮች ጋር ሲወዳደሩ አንድ ባንክ ላይሆኑ ይችላሉ" ሲሉ ይተቻሉ።

https://p.dw.com/p/3kEvU
Äthiopien Commercial Bank of Ethiopia in Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

ተጨማሪ 20 ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት ዝግጅት ላይ ናቸው

ጠቅላይ ምኒስትርዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት በተያዘው አመት ተጨማሪ 20 ባንኮች የፋይናንስ ገበያውን ለመቀላቀል ሒደት ላይ ናቸው። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ከእነዚህ 20 ገደማ ባንኮች አብዛኞቹ ሒደቱን ጨርሰው ወደ ፋይናንስ ኢንደስትሪው ከተቀላቀሉ በኤኮኖሚው ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል" ሲሉ ተናግረዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ደረሰ መርሻ የባንኮች ቁጥር መበራከት እምብዛም አያሳስባቸውም። "በኬንያ ወደ 43 የሚጠጉ ባንኮች አሉ። ከእነዛ ውስጥ ወደ አስር የሚጠጉት በጣም ግዙፍ የውጭ ባንኮች ናቸው" የሚሉት  ዶክተር ደረሰ የኢትዮጵያን የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት ከሌሎች አገሮች አኳያ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ይተቻሉ። ዶክተር ደረሰ እንደሚሉት "ቁጥራቸው በዛ እንጂ አቅማቸው ሶስት፣ አራት፣ አምስቱ ባንኮች ከሌሎች አገሮች ጋር ሲወዳደር አንድ ባንክ እንኳ ላይሆኑ ይችላሉ።"

የፋይናንስ አማካሪው አቶ ቴዎድሮስ ጣሰውም ቢሆኑ የኢትዮጵያ ገበያ ለተጨማሪ የባንክ አገልግሎት አቅራቢዎች የሚሆን ገበያ እንዳለው እምነታቸው ነው። የባንክ አገልግሎቱን ከኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር እና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች እያነጻጸሩ ብቁ አለመሆኑን የሚተቹት የፋይናንስ አማካሪው የኢትዮጵያ ባንኮች ተደራሽነታቸውን በቅጡ ሳያሰፉ፤ ብርቱ ውድድርም ሳይገጥማቸው ትርፋ መሆናቸውን ይናገራሉ። "ለቤት ፈላጊዎች፣ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት የሚቀርበውን ብድር፣ የግብርና ፋይናንሲንግ ስታይ ገበያው ገና አልተነካም" የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት አዳዲሶቹ ባንኮች ገበያውን በቅጡ አጥንተው የራሳቸው የሆነ አገልግሎት ማቅረብ ይገባቸዋል።

"ዝም ብሎ ባንክ ወይም ቅርንጫፍ መክፈት ብቻ ሳይሆን የተለየትኩረት የሚያስፈልጋቸው የስራ ዘርፎች አሉ። አርባ ባንክ፤ ሐምሳ ባንክ ቢኖር ሁሉም የባንክ አካውንት ማስከፈት፣ ለንግድ ሥራዎች ብድር መስጠት ብቻ ከሆነ" ውጤት እንደማይኖረው ተናግረዋል።  

Äthiopien Addis Abeba Tsehay Insurance & Nib Bank
የመንግሥቶቹን ጨምሮ በኢትዮጵያ ገበያ 18 ባንኮች በሥራ ላይ ይገኛሉምስል DW/E. Bekele Tekle

"ባንኮች ትርፋቸውን የሚያገኙት ተቀማጭ ሰብስበው ለደንበኞቻቸው በማበደር ነው። ሲያበድሩ ደግሞ ወለዱ ከፍተኛ ነው። ሲያበድሩ ንብረት በዋስትና ይዘው ነው" ያሉት ዶክተር ደረሰ ባንኮቹ ገንዘብ መበደር ለፈለገ ሥራ ፈጣሪ "ያለ ምንም ማስያዣ ብድር አይሰጥም። አንዳንዴ እንዲያውም እስከ አራት እጥፍ ድረስ ማስያዣ ጠይቀው ነው ብድር የሚሰጡት። መክፈል ባይችል እንኳ ንብረቱን ሸጠው ዋናቸውን ያስመልሳሉ" ብለዋል።

በዚሁ ምክንያት እስካሁን ባለው ገበያ የኢትዮጵያ ባንኮች እምብዛም የኪሳራ ሥጋት ያለባቸው አይመስልም። የፋይናንስ አማካሪው አቶ ቴዎድሮስ "ገበያው ምንም ያልተነካ ከመሆኑ የተነሳ ምንም አይነት ሥጋት የሌላቸው ሥራዎች ብቻ በመስራት ትርፋማ መሆን እንደምትችል ነው እስካሁን ያለው [ገበያ] የሚያሳየው። ባንክ ከከፈትክ ተቀማጭ ትሰበስባለህ፤ ከዚያ በኋላ ታበድራለህ፤ ትርፍ ታገኛለህ" ሲሉ የኢትዮጵያ ባንኮች የተከተሉትን አካሔድ ሸንቆጥ አድርገውታል።

ያለፈው አመት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በኮሮና ወረርሽኝ ጫና ውስጥ ቢቆይም ለባንክ ተቋማት ግን የከፋ አልነበረም። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አህመድ "ባለፈው አመት የባንኮች ቅርንጫፎች 5341 ብቻ ነበሩ። በዚህ አመት ከአንድ ሺህ በላይ ቅርንጫፎች በመጨመር 6628 ቅርንጫፎች በሀገር ደረጃ ተከፍተዋል። የባንኮች ቅርንጫፎች መበራከት ሥራ አጥነትን [በመቀነስ] ከሚጫወተው ሚና በተጨማሪ ከፍተኛ ሐብት ለመሰብሰብ እና ለመቆጠብ፤ ያንን ሐብትም መልሶ ኢንቨስት ለማድረግ ዕድል የሚሰጥ ስለሆነ ቅርንጫፎች በ18 በመቶ ገደማ ማደጋቸው በፋይናንሺያል ዘርፉ ውስጥ ጎልተው ከሚታዩ ዕድገቶች አንዱ ነው። በዚህም ሳቢያ ባለፈው አመት የተቀማጭ ሒሳብ ያላቸው ዜጎች ቁጥር 38.7 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን ከቅርንጫፎች መበራከት ጋር ተያይዞ ወደ 50.7 ሚሊዮን ዜጎች የተቀማጭ ሒሳብ ከፍተዋል። ይኸ ብቻ ሲወሰድ ወደ 31 በመቶ ገደማ ዕድገት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

Äthiopien Währung Birr
ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት ባለፈው አመት የኢትዮጵያ ባንኮች አንድ ትሪሊዮን ብር ገደማ ሰብስበዋልምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ጠቅላይ ምኒስትሩ ባንኮቹ አንድ ትሪሊዮን ብር ገደማ መሰብሰባቸውን አስረድተዋል። አብዛኛው ገንዘብ የተሰበሰበው ከአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ ቅርንጫፎች መሆኑን የጠቀሱት ዐቢይ ከአንድ ትሪሊዮን ብሩ በኦሮሚያ 13.7 በመቶ፤ በአማራ 7.3 በመቶ፤ በደቡብ 5.2 በመቶ መሰብሰቡን አስረድተዋል። ዐቢይ እንዳሉት "በዘንድሮው አመት ከተሰበሰበው ሐብት ውስጥ 271 ቢሊዮን ብር ባንኮች አበድረዋል። ካበደሩት 271 ቢሊዮን ብር ውስጥ 70 በመቶው ወይም 189 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ ነው።" 

ጠቅላይ ምኒስትሩ በፋይናንስ ዘርፉ ተሳክተዋል ላሏቸው መሻሻሎች የመንግሥትን ከፍተኛ ድጋፎች እና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሚና ጠቅሰዋል። ብሔራዊ ባንክ የግሎቹ ባንኮች የገንዘብ እጥረት እንዳይገጥማቸው 14 ቢሊዮን ብር ማበደሩ፤ የግል ባንኮቹ ካበደሩት በ27 በመቶው ቦንድ እንዲገዙ የሚያስገድደው መመሪያ መቋረጡ እና በቦንድ ግዢው "የተሰበሰበ 15 ቢሊዮን ብር እንዲመለስላቸው መወሰኑ" በምሳሌነት ያቀረቧቸው ናቸው።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ