1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ጌታቸው ረዳ ጋዜጣዊ መግለጫ

ዓርብ፣ መጋቢት 15 2015

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳደር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት መሾማቸው የተገለጠው አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ የትግራይ ክልል ግዛታዊ አንድነትን ለማስጠበቅ እንደሚሠሩ ተናገሩ ። የተፈናቀሉ ያሏቸውን መልሶ ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ተግባራት እና ሌሎች ቀዳሚ አጀንዳዎችን እንደሚሠራባቸውም ዐስታውቀዋል ።

https://p.dw.com/p/4PBj4
Äthiopien, Tigray Konflikt, Getachew Reda von TPLF
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP

የትግራይ ክልል «ግዛታዊ አንድነት»ን ለማስጠበቅ እንደሚሠሩ ተናግረዋል

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳደር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት መሾማቸው የተገለጠው አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ የሚመሩት አስተዳደር የትግራይ ክልል ግዛታዊ አንድነትን ለማስጠበቅ እንደሚሠራ ተናገሩ ። የተፈናቀሉ ያሏቸውን መልሶ ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ተግባራት እና ሌሎች ቀዳሚ አጀንዳዎችን እንደሚሠራባቸውም ዐስታውቀዋል ። ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አጎራባች ከሆኑ አፋር እና አማራ ክልሎች እንዲሁም ከኤርትራ ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት እንደሚያደርግ ገልጠዋል። ከአጎራባች ክልሎች ጋር ስላለው የወሰን ጥያቄ በተመለከተም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በሕገመንግስቱ መሰረት እንዲፈታ እንደሚሠራ ተናግረዋል ። አቶ ጌታቸው ለአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ባስተላለፉት መልእክት፦ «የተጀመረው የሰላም ሒደትን ከሚያደናቅፉ ተግባራት እንዲቆጠቡ» ብለዋል ።

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ሕወሓት መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነትመሰረት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ሥራ በጀመሩት በዛሬው ዕለት በተለያዩ ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ ሰጥቸዋል ። አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው፣ ጦርነቱን ተከትሎ በትግራይ መጠነ ሰፊ ኪሳራ መድረሱን ያነሱ ሲሆን፤ የውድመቱ ጠባሳም ዘላቂ መሆኑ ገልፀዋል። ከደም አፋሳሽ ግጭቱ በኋላ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ለመፈፀም የኢትዮጵያ መንግስት እና ፓርቲያቸው ሕወሓት መተማመንን የሚያሳድጉ ርምጃዎች እየወሰዱ መሆኑን ያነሱት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፦ ሕወሓትም በተፈጠረው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ገንቢ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል ። 

ሥራውን እየጀመረ ያለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ቆይታው አጭር ቢሆንም የትግራይ ሕዝብን ኅልውናና ድህንነት የሚያስጠብቁ ሥራዎች እንደሚከውን፣ የፕሪቶርያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር እንደሚጥር፣ የትግራይ ግዛታዊ አንድነት ለማረጋገጥ እንዲሁ የተፈናቀሉት ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የማድረግ ተግባራት አጀንዳዎቹ እንደሚያደርግ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል ።  የወሰን ጉዳይ ደግሞ በሕገመንግስቱ መሰረት ብቻ መታየት እንዳለበትም ገልፀዋል። 

የተቃጠለ ከባድ ተሽከርካሪ ትግራይ ክልል፤ አደዋ ከተማ አቅራቢያ፦ ፎቶ ከክምችት ማኅደር
የተቃጠለ ከባድ ተሽከርካሪ ትግራይ ክልል፤ አደዋ ከተማ አቅራቢያ፦ ፎቶ ከክምችት ማኅደርምስል privat

አቶ ጌታቸው ረዳ ከሹመታቸው በኋላ በዛሬው የመጀመርያ ንግግራቸው «ሥራ ላይ ባለው ሕገመንግስት መሰረት፣ የትግራይ መሬት ማለት የትግራይ ነው። የሚነሳ ጥያቄ ካለ በሰላም እና በሕገመንግስታዊ መንገድ መፈፀም አለበት። በዚህ አጋጣሚ የአማራ ክልል የፀጥታ ሀይሎች ይህ እንዲገነዘቡ፣ የተጀመረው የሰላም ሂደት ከሚያደናቅፉ ተግባራት እንዲቆጠቡ አደራ ማለት እፈልጋለሁ» ብለዋል። 

ከኤርትራ ጋር በተያያዘም፣ የኤርትራ ጦር አሁንም ሙሉበሙሉ አለመውጣቱ በማንሳት «የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ከሆነው መሬታችን እንዲወጣ፣ የሕዝቦች ስቃይ እንዲያበቃ የፌደራሉ መንግስት ይሁን ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ የሚቻላቸው ሁሉ ያድርጉ» ብለዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደራቸው ለዘላቂ ሰላም እና የሕዝቦች መልካም ግንኙነት መዳበር ጥረት እንደሚያደርግ ያነሱ ሲሆን «በተለይም አጎራባች ከሆኑ አፋር፣ አማራና ኤርትራ ህዝቦች ዘልአለም ይኖራሉ። እንደሚባለው ወዳጅ እና ጎደኛ እንጂ ጎረቤት መምረጥ አይቻልም። ከዚህ በላይ ደግሞ ወንድም ህዝቦች ናቸው። ያለፈው አልፎ ስለነገው እንድናስብ፣ ለትውልድ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ፈጥረን ማለፍ አለብን። በኛ በኩል ይህ ለማድረግ በላቀ ትኩረት እንሰራለን» ብለዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የፌደራሉ መንግስት ጀመራቸው ያልዎቸው በጎ ተግባራት እንዲያዳብር ጥሪ አቅርበዋል።

በትግራይ የውስጥ ጉዳዮች ዙርያ የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ የትግራይ ትልቁ ሀብት ብሄራዊ አንድነታችን ነው ካሉ በኃላ "ጥረታችን፣ ሕይወታችን፣ ጉልበታችን፣ ሀብታችን ትግራይ እና የትግራይ ህዝብ ይሁን" ሲሉ አክለዋል። የግዚያዊ አስተዳደሩ መሪ ጨምረውም በትግራይ ካሉ የተለያዩ የፖለቲካ ሐይሎች ጋር በጋራ ለመስራት እይደሚፈልጉ አንስተዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ