1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የታኅሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseረቡዕ፣ ታኅሣሥ 9 2017

የታኅሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና የኢትዮጵያ መንግሥት የመብቶች እና ዴሞክራሲ ማዕከል የተባለውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ዳግም «ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ» አገደ። የአውሮጳ ኅብረት በሶሪያ ላይ የጣላቸውን አንዳንድ የኤኮኖሚ ማዕቀቦች ማንሳትን እንደገና ሊያጤን እንደሚችል አስታወቀ። የፈረንሳይ ከፍተኛ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ በሙስና እና ስልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም ተከሰው የተበየነባቸውን ውሳኔ አፀና። ፍርድ ቤቱ ሳርኮዚ እንቅስቃሴያቸውን የሚከታተል የኤሌክትሮኒክ መሳሪያ ለአንድ ዓመት እንዲያደርጉም አዟል።

https://p.dw.com/p/4oKBa

ቦን        የመብቶች እና ዴሞክራሲ ማዕከል ዳግም ታገደ

የኢትዮጵያ መንግሥት የመብቶች እና ዴሞክራሲ ማዕከል የተባለውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ዳግም «ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ» አገደ። ተቋሙ የታገደው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 በጻፈው ደብዳቤ ነው። ባለሥልጣኑ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ማዕከልን ጨምሮ ሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገደው በኅዳር የመጀመሪያ ሣምንት ነበር።  የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች እና ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች የተባሉ ሌሎች ሁለት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም በወቅቱ ተመሳሳይ ዕገዳ ቢጣልባቸውም ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ዕግዱ ተነስቶላቸዋል።የመብቶች እና ዴሞክራሲ ማዕከል ተጥሎበት የነበረው ዕገዳ የተነሳው ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን «ከፍተኛ አመራሮች ጋር ችግሩን ለመፍታት ካደረግናቸው ከፍተኛ እና ተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ» ነው በማለት አስታውቋል። ባለሥልጣኑ «ለምርመራ ለላካቸው የክትትል እና የግምገማ ቡድን አባላት ሙሉ ትብብር» ማድረጉን የገለጸው ካርድ «ከዕገዳው መነሳት ጋር ተያይዞ ማስጠንቀቂያ» እንደተሰጠው ገልጾ ነበር።ይሁንና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የመብቶች እና ዴሞክራሲ ማዕከል «በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት አሰራሩን ያላስተካከለ» በመሆኑ መታገዱን አስታውቋል። «ለባለሥልጣኑ ሕግ እና ውሳኔ ተገዢ ባለመሆን» እንዲሁም «ለመማር እና ለማስተካከል ዝግጁ ባለመሆን» የሚሉ ክሶች ካርድ መታገዱ በተገለጸበት ደብዳቤ የተካተቱ ተጨማሪ ክሶች ናቸው። «ከዚህ ቀደም የፈጸማቸውን ጥፋቶች» እንደቀጠለ የሚገልጸው ደብዳቤ  የመብቶች እና ዴሞክራሲ ማዕከልን «ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ» ማገዱን አመልክቷል።

ናይሮቢ    ደቡብ ሱዳን በዘፈቀደ ያሰረቻቸውን ሰላማዊ ሰዎች እንድትፈታ የተመድ ጠየቀ

የተ.መ.ድ ግጭት በሚካሄድባት በደቡብ ሱዳን ይፈጸማል ያለውን የመብቶች ጥሰት አወገዘ ፤ ባለስልጣናትም  በዘፈቀደ የታሰሩትን ሰላማዊ ሰዎች እንድትፈታ ጠየቀ ።በሀገሪቱ የዘፈቀደ እስር እንደሚካሄድ ያስታወቀው የተመድ ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ እና የድርጅቱ የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ እንደተናገሩት ካለፈው ዓመት ጥር እስከ ግንቦት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 87 ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 1140 ሰላማዊ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተይዘው ታስረዋል። ከመካከላቸው በግዳጅ መዳርን የተቃወሙ፣ የተፋቱ እና አመንዝረዋል የተባሉ ሴቶችና ልጃገረዶች ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ተባባሪዎቻቸው ተብለው የሚታሰቡ ወህኒ ተወርውረዋል ።የተመድ እንዳለው በመብት ጥሰቱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና ታጣቂ ቡድኖችም ቢሳተፉም አብዛኛዎ እስሮች የተፈጸሙት ግን በመንግስት ነው ። የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ሃላፊ ፎልከር ቱርክ የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ነጻነታቸውን ተነፍገው በዘፈቀደ የታሰሩትን ሰዎች በሙሉ እንዲፈቱ እና በመብት ጥሰቱ ተጠያቂ የሆኑትን ደግሞ ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

ፓሪስ     በቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ላይ ከዚህ ቀደም የተበየነባቸው ፍርድ ፀና

የፈረንሳይ ከፍተኛ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ በሙስና እና ስልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም ተከሰው የተበየነባቸውን ውሳኔ አፀና። ፍርድ ቤቱ ሳርኮዚ እንቅስቃሴያቸውን የሚከታተል የኤሌክትሮኒክ መሳሪያ ለአንድ ዓመት እንዲያደርጉም አዟል።ከዚህ ቀደም ከአንድ ዳኛ ውለታ እንዲውሉላቸው በመሞክር ጥፋተኛ ተብለው የነበሩት ሳርኮዚ አሁን የጥፋተኝነት  ብይኑን እንደሚያከብሩ ነገር ግን ጉዳዩን በሳምንታት ውስጥ ወደ አውሮጳ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ጠበቃቸው ፓትሪስ ስፒኖሲ ተናግረዋል።

የፈረንሳይ የስር ፍርድ ቤት በጎርጎሮሳዊው 2021 ሳርኮዚ እና የቀድሞ ጠበቃቸው ቴሪ ሄርዞግ ፣ጊልበርት አዚቤርት ከተባሉ ዳኛ ጋር ስለ አንድ ሕጋዊ ምርመራ መረጃ ለማግኝት እና ለመጋራት የሙስና ውል መፈጸማቸውን ደርሶበት ነበር። ያኔ ፍርድ ቤቱ የሦስት ዓመት እሥራት ወስኖባቸው ሁለቱ ዓመት ሲነሳላቸው አንዱን ዓመት ደግሞ እንቅስቃሴያቸውን የሚከታተል የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ አድርገው በቁም እስር ላይ እንዲቆዩ በይኖባቸው ነበር። ከአንድ ዓመት በፊት ጉዳዩን የተመለከተው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም ብይኑን አጽንቶት ነበር። ከጎርጎሮሳዊው 2007 እስከ 2012 ዓም የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት የነበሩት የ69 ዓመቱ ሳርኮዚ «አሁንም ንጹህ ነኝ። ትግሌንም አላቆምም » ብለዋል።

 

ሽትራስቡርግ    የአውሮጳ ኅብረት በሶሪያ ላይ የጣለቸውን ማዕቀቦች ለማንሳትን እያጤነ ነው

የአውሮጳ ኅብረት በሶሪያ ላይ የጣላቸውን አንዳንድ የኤኮኖሚ ማዕቀቦች ለማንሳት እያጤነ መሆኑን አስታወቀ። የኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ዛሬ እንደተናገሩት ኅብረቱ ይህን የሚያደርገው የሶሪያን መልሶ ግንባታ ለማመቻቸት ነው።ግለሰቦችንም ዒላማ ያደረገው በተገለበጠው የአሳድ አገዛዝ  በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት ኅብረቱ የጣለው ማዕቀብ መጠነ-ሰፊ የወጪና ገቢ ንግድ እገዳንና በፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ የተቀመጡ ገደቦችን ያካትታል። በዚህም ከኅብረቱ ወደ ሶሪያ የሚላኩ መጠነ ሰፊ የቴክኒክና የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የጀት ነዳጅ ፣ለነዳጅ ዘይትና ለጋዝ ኢንዱስትሪ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች እና የነዳጅ ዘይት ውጤቶች ብድርና የንግድ እገዳዎች ይገኙበታል። ፎን ዴር ላየን ሽታርስቡርግ ፈረንሳይ ውስጥ ለኅብረቱ ምክር ቤት አባላት እንደነገሩት አዲሱ የሶሪያ አመራር ቃሉን ከጠበቀ ኅብረቱ የሶሪያ መልሶ ግንባታን ለመደገፍ ይፈልጋል። ለሶሪያው የቀድሞ መሪ በሽር አልአሳድ መገልበጥ ትልቁን ሚና የተጫወተው ሃያት ታህሪር አል ሻም የተባለው ቡድን የተመድ በአሸባሪነት ከመዘገባቸው ቡድኖች አንዱ ነው። ቡድኑ የአውሮጳ ኅብረት በሶሪያ ላይ የጣለው ማዕቀብ ከሚመለከታቸው ቡድኖች አንዱ ነው።

ባንዱ አቼ    ከ220 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለው የሱማትራን ደሴት የመታው ኃይለኛው ሱናሚ 20 ዓመት ሊደፍን ነው

ከ220 ሺህ በላይ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች የሞቱበት ፣የህንድ ውቅያኖሱ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስነሳው ሱናሚ በሚቀጥለው ሳምንት 20 ዓመት ይደፍናል።በጎርጎሮሳዊው ታኅሳስ 26 ቀን 2004 ዓም የኢንዶኔዥያን ምዕራባዊ የባህር ዳርቻ የሱማትራን ደሴት በመታው በሬክተር መለኪያ 9.1 በተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ከተነሳው  ሱናሚ የተረፉ እና የጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦች 20ኛውን ዓመት በሚቀጥለው ሐሙስ ያስቡታል።በወቅቱ ቢያንስ 1,200 ኪሎ ሜትር የሚደርሰው የባህሩ ወለል ሲከፈት 30 ሜትር ርዝመት ያለው ማዕበል አስነስቶ ከባድ ጥፋት አድርሷል። በዚሁ ዓለም አቀፍ አደጋ በተባለው  ሱናሚ በአጠቃላይ 226 ሺህ 408 ሰዎች ሲሞቱ ከመካከላቸው ከ120ሺህ የሚበልጡት በአደጋው ክፉኙ ከተጎዳው ከሰሜን ሱማትራ የነበሩ ናቸው። በአጠቃላይ ኢንዶኔዥያ ውስጥ የሞቱት ደግሞ 165 ሺህ 708 ሰዎች ናቸው,። ህንድ ውቅያኖስን የዞረው ይኽው ሱናሚ ሲሪላንካን ህንድንና ታይላንድንም ከሰዓታት በኋላ መቷል። ሱናሚ ከገደላቸውe በተጨማሪ 1.5 ሚሊዮን ሰዎችንም አፈናቅሏል። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶችንም እንዳልነበረ አድርጓል። እስካሁn በኢንዶኔዥያዋ አቼ ከ100 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተዋል።

መቅዲሾ      ሶማሊያ ከፕላስቲክ ነጻ ለመሆን እየጣረች ቢሆንም አልተሳካላትም

ሶማልያ ከፕላስቲክ የተሰሩ እቃ መያዣ ፌሽታሎችን ለማስወገድ እየጣረች ቢሆንም እንዳልተሳካላት ተነገረ ። በመገባደድ ላይ ባለው በጎርጎሮሳዊው 2024 ዓ.ም. በየካቲት ወር   ፌሽታሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ሶማሊያ ብታግድም ገቢራዊነቱ ግን ቀላል እንዳልሆነላት የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ኬንያንና ታንዛንያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራትም ፌሽታሎች  ካገዱ በኋላ ተመሳሳይ እርምጃ በወሰደችው በሶማሊያ ሕጉ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ግን ባለፈው ጥቅምት ወር ነበር። ከዚያን ወዲህም ሕጉን የጣሱ ጥቂት ሰዎች ከመታሰራቸው ውጭ እርምጃው ተጽእኖ የማድረጉ ምልክት አነስተኛ መሆኑን  የAFP ዘገባ ያስረዳል ። ዜና አገልግሎቱ ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ፌሽታሉን የሚጠቀሙበት ምክንያት ርካሽና ሰዉም በቀላሉም የሚያገኛቸው ስለሆነ ነው ብለዋል። ፌሽታሎችን መጠቀም የሚያስከትለውን መዘዝ  ሁሉም ቢያውቅም ችግሩ ሌሎች አማራጮች ውድ መሆናቸው እንደሆነም ተናግረዋል። ከህዝብዋ ግማሹ ከድኅነት ወለል በታች የሆነ ህይወት በሚገፋባት በሶማሊያ ፌሽታሎችን ይተኩ የተባለው የወረቀት እቃ መያዣዎች ውድ ናቸው። የሀገሪቱ የአካባቢ ጉዳዮች ሚኒስትር በበኩላቸው ፌሽታሎች አሁንም በሶማሊያ ጥቅም ላይ የሚውሉበት ምክንያት ነጋዴዎች ከእገዳው በፊት ለሽያጭ በማከማቸታቸው መሆኑን ገልጸው ይህ እስኪያልቅ ድረስ እንዲሸጡ እንደተፈቀደላቸው ተናግረዋል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።