የቀጠለው የምርጫ ውጤት ገለጻ እና ኦፌኮ የሰነዘረው ትችት
ዓርብ፣ ሰኔ 5 2018
የቀጠለው የምርጫ ውጤት ገለጻ እና ኦፌኮ የሰነዘረው ትችት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድበድህረ ምርጫ ሂደቱ ውጤት ማሳወቅ ስራውን በመቀጠል፤ የቅረቡለትንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታን በአጽኖት እየተመለከታቸው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በምርጫው ላይ መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ግን “ነፃና ፍሕታዊ” ምርጫ መካሄዱ ላይ ጠንከር ላይ ጥያቄ በማንሳት፤ የኢትዮጵያ ውስብስብ የፖለቲካ ቀውሶች በዚህ አይፈታም ሲል አቋሙን ገልጿል፡፡
ኦፌኮ በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ጋር በጦርነት ላይ ያሉ ታጣቂ ኃይሎችን አካትቶ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች በማሰባሰብ በድርድር ለይ ለተመሰረተ አዲስ የፖለቲካዊ ስምምንነት ፍኖተ ካርታ መሰረት አንዲጣል ሲል ጠይቋልም።
ከየምርጫ ክልሎቹ ወደ ማዕከል የሚመጡትንየምርጫ ውጤቶችተቀብሎ በትክክል የተቀመጡ ስለመሆናቸው በማጣራት የማረጋገጥ ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ትናንት ሓሙስ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ለዚህ ስራ የተመደቡ ሰራተኞቹ ጠንክረው እየሰሩበት እንዳሉ ገልጿል፡፡
የቦርዱ የማጣራት አሰራር ሂደት
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ “በማጣራት ሂደቱ ከየምርጫ ክልሉ የሚመጡ ውጤቶች የሚቀበል የስራ ክፍል ማረጋገጫ ለሚሰጡት የስራ ክፍል ያቀርባል፤ እነዚያ ባለሞያዎች ደግሞ አጣርተው ጥያቄ ወይም የሚያጠራጥር ነገር ካለ የበለጠ ማጣራት ይገበዋል ብለው ሲያስቡ ደግሞ ወደ ኦዲት ክፍል ይልኩታል፤ ኦዲት ክፍልም በሕጉ መሰረት መርምሮ ውሳኔ የሚሰጥትበትን አቅጣጫ ከቦርዱ የሚቀበል ይሆናል ወይም ደግሞ፤ የሚጣራው ነገር ተጣርቶ በአረጋጋጮቹ በኩል ለቦርዱ እንዲቀርብ ይደረጋል ማለት ነው” ሲሉ ሂደቱን አብራርተዋል፡፡
ለቦርዱ የደረሱ የምርጫ ክልሎች ውጤት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመግለጫው ምርጫው ከተካሄደባቸው 1 ሺህ 139 የምርጫ ክልሎች ውጤቶች አሁን ላይ ከስምንት ያህል የምርጫ ክልሎች ውጤት በስተቀር 1 ሺህ 131 ውጤቶች ወደ ማዕከል መምጣታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ “ከ501 የህዝብ ተወካዮች ውጤቶች 497 ደርሰው አራት ብቻ ቀርተዋል” ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ከ638 የክልል ምክር ቤት ውጤቶች ደግሞ 634ቱ ውጤት ማዕክል ደርሰው አራቱ ብቻ መቅረታቸውን፤ በአጠቃላይም የስምንት የምርጫ ክልሎች ውጤቶች ብቻ ማዕክል ያልደረሱ መሆናቸውን አረጋግጠው አሁን ላይ በምርጫ ክልል ደረጃ ያልተለጠፈ ውጤት አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ቀሪ ውጤቶች ወደ ማዕክል ሳይመጡ ጠቅላላ ውጤቱ ይፋ የማይደረግ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በፓለቲካ ፓርቲዎች የቀረበው ቅሬታ እና እልባቱ
ወደ 120 የምርጫ ክልሎች ላይ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረበው ቅሬታም በቦርዱ የህግ ባለሙያዎች እየታየ እንደሚገኝም ቦርዱ በመግለጫው አብራርቷል፡፡ እነዚህ ቅሬታ የቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ተጣርተው እልባት ሳያገኙ የእነዚህ የምርጫ ክልሎች ውጤት ይፋ እንደማይደረግም የገለጹት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ሆኖም ግን በማጣራት ሂደቱ በተለይም በምስክሮች አቀራረብ ላይ እስካሁን ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን አስረድተዋል፡፡ “እስካሁን 148 ምስክሮች በፖለቲካ ፓርቲዎቹ በቀረቡ ቅሬታዎች ላይ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል” በማለትም ሂደቱን የሚያጣሩ ባለሙያዎች ከምስክሮቹ በተጨማሪ ሰነድ ምርመራዎችም እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ የማሳለፍ ስልጣኑ የቦርዱ እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡
ይፋ የተደረጉ አዳዲስ ውጤቶች
ቦርዱ አሁን ወደ ማእከል መጥተው የማጣራት ስራ ተደርጎባቸዋል የተባሉትን ውጤቶች ግን ከስር ከስር ይፋ ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ ቀድም ሲል በተከታታይ ሁለት ቀናት ይፋ ከተደረጉ የ46 ምርጫ ክልሎች ውጤት በተጨማሪ ትናንት ሐሙስ የተጨማሪ 32 የምርጫ ክልሎች፤ በአጠቃላይም ከጠቅላላው 1 ሺህ 139 ምርጫው ከተደረገባቸው የምርጫ ክልሎች የ76 ምርጫ ክልሎች ውጤትን ይፋ አድርጓል፡፡ በአዲስ አበባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል 18 ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ባልተሳተፈበት፣ ነገር ግን በርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እጩዎቻቸውን ባቀረቡበት የተፎካካሪ ፓርቲ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሪ ኢዮብ መሳፍንት ከፍተኛውን ድምጽ በማግኘት የፓርላማ መቀመጫቸውን ያረጋገጡበት ውጤት ተጠቃሽ ነው፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ የምርጫ ክልል ከጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት መኮንን ጎላሳ፣ ለድሬደዋ ከተማ ምክር ቤት ረመዳን መሃመድ ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ጀማል ዑመር እና አብዱላህ ፋራህ ከነጻነትና እኩልነት ፓርቲ መቀመጫ ካገኙ ሌላው የተፎካካሪ ፓርቲ እጩ ናቸው፡፡
ኦፌኮ በምርጫው ላይ ያቀረበው ትችት
ምርጫው “ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ” እንደነበር የገለጹትን የአፍሪካ ህብረት እና የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎችን “የዴሞክራሲን መርህ ያቃለለ” ሲል ክፉኛ የነቀፈውኦፌኮ፤ በኢትዮጵያ ምርጫ መካሄዱን በበጎ በመመልከት መግለጫ ያወጣውን የአውሮፓ ህብረትንም “ታዛቢ ልዑክ እንኳ ሳይልክ” እንዲሁም “መሬት ላይ ያለው የፖለቲካ አፈና” ያለውን ችላ በማለት ወቅሶ መግለጫውን አጣጥሏል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየትም፤ “ምርጫው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርኣትን የማያሰፍን እንደሆነ አንስልተናል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ስላልተደረገባቸው አከባቢዎች እጣፈንታ ትናንት ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተጠይቀው፤ “ምርጫ ባልተካሄደባቸው አከባቢዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስቻይ ሁኔታ መኖራቸውን እያየ እየገመገመ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ምርጫውን ያካሂዳል” ብለዋል፡፡ #ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026
ሥዩም ጌቱ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ፀሐይ ጫኔ