1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሚያዝያ 3 ቀን 2018 ዓ.ም የዓለም ዜና

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 3 2018

ኢትዮጵያ ውስጥ የከርቤ ዛፍ በድርቅ ምክንያት እየተመናመነ እንደሆነ አሶሺየትድ ፕረስ ዘገበ። የጅቡቲው ፕሬዝደንት ጉሌሕ 97.81% የመራጭ ድምፅ በማግኘት አሸነፉ። የእስራኤል ጦር ባለፉት 24 ሰዓታት ሊባኖስ ውስጥ ከ200 በላይ የሂዝቦላ ኢላማዎች መደብደቡን አስታወቀ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊዎች በመካከለኛው ምስራቅ የሚደረግ የአለም አቀፍ ህግ ጥሰት እንዲቆም ጠይቁ። የኢራን እና የዩናይትድ ስቴትስ የፊት ለፊት ድርድር ዛሬ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ጀምሯል። ከ50 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ አቅራቢያ የነበሩት የጠፈር ተመራማሪዎች በሰላም ወደ ምድር ተመለሱ።

https://p.dw.com/p/5C25M

 

ኢትዮጵያ ውስጥ የከርቤ ዛፍ እየተመናመነ እንደሆነ ተገለጸ

 

ኢትዮጵያ ውስጥ የከርቤ ዛፍ እና ከዛፉ የሚገኘው እጣን መሳይ ግብዓት በድርቅ ምክንያት እየተመናመነ እንደሆነ አሶሺየትድ ፕረስ ዘገበ።

ከርቤ  ለሽቶ መዓዛ እና ለህክምና እንዲሁም ለተለያዩ ነገሮች አገልግሎት ላይ ይውላል። ለከርቤ ዛፍ መመናመን በዋና ምክንያትነት የተጠቀሰው የዝናብ እጥረት እና የከባቢ አየር ለውጥ ቢሆንም በእንስሳቶች ግጦሽ ምክንያት ወጣት የሆኑት ዛፎች እየተጎዱ ነው ተብሏል። 

የዘርፉ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ከርቤ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛፉ ሳይቆረጥ በባህላዊ መንገድ መሰብሰቡን  እንደሚያወድሱ እና ይህም ሊቀጥል እና ሊበረታታ እንደሚገባ መናገራቸውን ዜና ምንጩ ዘግቧል።

የከርቤ አምራቾች በኪሎ ከ 3,50 እስከ 10 የአሜሪካን ዶላር የሚያገኙ ሲሆን  የሽቶ አምራቾች ግን ለዘይቱ እስከ 500 ዶላር እንደሚጠይቁም ተዘግቧል። ኢትዮጵያ ለከርቤ ግብር እንደማትጠይቅ እና አብዛኛውን ጊዜም ከምስራቁ ክፍል ከኢትዮጵያ ከርቤ የሚገዙት የጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ነጋዴዎች እንደሆኑ አሶሺየትድ ፕረስ ተዘግቧል።

 

የጅቡቲው ፕሬዝደንት ጉሌሕ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ለ 6ኛ ጊዜ አሸነፉ

 

የጅቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ ትናንት የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደተጠበቀው አሸነፉ። የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ ዛሬ እንዳስታወቀው ጉሌሕ  ምርጫውን ያሸነፉት 97.81% የመራጭ ድምፅ በማግኘት ነው።

ለስድስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን የተመረጡት የ78 አመቱ ጉሌህ 1ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ ያላትን ትንሿን የአፍሪካ ቀንድ ሀገር ከሁለት አስርት አመታት በላይ መርተዋል። ጉሌህ በዚህ አመት ከስልጣን እንደሚለቁ አስታውቀው የነበረ ቢሆንም ባለፈው ህዳር ወር የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት ጉሌሕ እንደገና እንዲወዳደሩ መንገዱን ጠርጓል። ትናንት በምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ የሰጡት ጉሌሕ ለመገናኛ ብዙኃን እንዲህ ሲሉ ነበር ምኞታቸውን የገለፁት"ድልን፣ ወንድማማችነትን፣ ብልጽግናን ፤ ሁሉም ሰው ኃላፊነቱን እንዲወጣ እመኛለሁ፣ እናም ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ እስካሁን ድረስ ለነበረው ሂደት እናመሰግናለን፣ ይህም ምርጫ በመላ ሀገሪቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ እመኛለሁ።"

 

የጅቡቲ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ብዙም ፉክክር ያልታየበት ነበር። በትናንቱ ምርጫ የመራጮች ተሳትፎ  ዝቅተኛ እንደነበርም ተገልጿል።  የጉሌሕ ተፎካካሪ የቀድሞ የገዢው ፓርቲ አባል እና በምህፃሩ (CDU) የሚባለው ፓርቲ መሪ ሞሐመድ ፋራህ ሳማታር ነበሩ።

 

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ለአለም ዋንጫ የተመረጡትን ዳኛ አርታን እንኳን ደስ አለህ አሉ

 

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ ፊፋ  ለዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ በዳኛነት ለመረጣቸው

ሶማሊያዊ የእግር ኳስ ዳኛ ኦማር አብዱልቃድር አርታን „የእንኳን ደስ አለህ መልዕክት“ አስተላለፉ። የ 34 ዓመቱ አርታን በሶማሊያ ታሪክ ለዓለም ዋንጫ በዳኛነት የተመረጡ የመጀመሪያው ሶማሌያዊ ናቸው።

በመጪው ሰኔ እና ሀምሌ ወራት በካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ዩናይትድ ስቴትስ በሚደረጉት የፍጻሜ ጨዋታዎች ላይ ፊፋ  ከመረጣቸው 52 ዳኞች መካከል አርታን አንዱ ናቸው።

ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ አርታን የሶማሊያን ስም በአለም አቀፍ መድረክ ከፍ ያደረገ ነው ብለዋል።
"ዳኛ ዑመር ያሳየውን ጥረት፣ ሙያዊ ብቃት አደንቃለሁ " ያሉት ፕሬዚደንቱ ዳኛ ኦማር አብዱልቃድር አርታን ለአዲሱ የሶማሊያ ትውልድ አርዓያ እንደሆኑም ገልፀዋል።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ዳኞችን ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገው ባለፈው  ሀሙስ ዕለት ነበር።

 

 

የእስራኤል ጦር በሊባኖስ  ከ200 በላይ የሂዝቦላ ኢላማዎችን  ደበደብኩ አለ


የእስራኤል ጦር ባለፉት 24 ሰዓታት ሊባኖስ ውስጥ  ከ200 በላይ የሂዝቦላ ኢላማዎች  መደብደቡን አስታወቀ።  ጦሩ እንዳለው የእስራኤል አየር ኃይል የሂዝቦላህን መሠረተ ልማት መምታቱን እና ደቡብ ሊባኖስ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የምድር ጦር ኃይሎቹን ማገዙን ይቀጥላል" ።

በሂዝቦላህ በኩል በእስራኤል ላይ የሚደረገው ጥቃት ቢቀንስም አለመቆሙን ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

በዛሬው የእስራኤል ጦር ጥቃት ዳግም በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ዛሬ የሊባኖስ ባለስልጣናት ገልጸዋል። በደቡባዊ የሊባኖስ ክፍል በናቲያህ አካባቢ በተደረጉ ጥቃቶች 10 ሰዎች መሞታቸውን የቤይሩት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቃል። ከተጎጂዎች መካከል የሕክምና ባለሙያዎች ይገኙበታል ተብሏል። የጀርመን ዜና ምንጭ እንደዘገበው ባለፉት ስድስት ሳምንታት ውስጥ በሊባኖስ 2000 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።

የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ትናንት ዓርብ እንደተናገሩት በእስራኤል- ሄዝቦላ ጦርነት ላይ ለመምከር በሚቀጥለው ሳምንት ከእስራኤል ጋር በዋሽንግተን ቀጠሮ ተይዟል። ይሁንና እስራኤል በዋሽንግተኑ ቀጠሮ ከሂዝቦላህ ጋር ስለሚደረግ የተኩስ አቁም እንደማትደራደር ዛሬ አስታውቃለች።

 

 

በመካከለኛው ምስራቅ የሚደረግ አለም አቀፍ የህግ ጥሰት እንዲቆም ተጠየቀ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊዎች በመካከለኛው ምስራቅ የሚደረግ የአለም አቀፍ ህግ ጥሰት እንዲቆም ጠይቁ።  በመንግስታቱ ድርጅት ስር የሚገኙ የተለያዩ  ኤጁንሲዎች ኃላፊዎች ዛሬ ባወጡት የጋራ መግለጫ ዓለማቀፍ ህግ ሊከበር ይገባል ብለዋል።

 "ባለፈው ወር ብቻ በመካከለኛው ምስራቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል ያለው መግለጫው ጦርነቶችም ህግጋት አሏቸው ፤ እነዚህ ህጎችም መከበር አለባቸው ይላል። በመግለጫውም  ባለፉት አራት ወራት ውስጥ 14 የእርዳታ ሰራተኞች በፍልስጤም ግዛት፤ ስምንት በኢራን እንዲሁም አምስት በሊባኖስ ተገድለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊዎች  ባወጡት የጋራ መግለጫም የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገራትም ሆኑ ታጣቂ ቡድኖች ሲቪሎችን፣ የሰብአዊ ርዳታ ሰራተኞችን እና የሲቪል መሠረተ ልማትን የመጠበቅ ህጋዊ ግዴታቸውን እንዲያከብሩ እንጠይቃለን" ብለዋል ።

 

የኢራን እና የዩናይትድ ስቴትስ የፊት ለፊት ድርድር በፓኪስታን ጀመረ

ከኢራን ጋር የሚካሄደውን ጦርነት በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የኢራን እና የዩናይትድ ስቴትስ የፊት ለፊት ድርድር ዛሬ ፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ላይ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ጀምሯል። የዩናይትድ ስቴትስ ልዑካን ቡድን በምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ሲመራ  የኢራን ልዑካን ቡድን ደግሞ በምክር ቤት አፈ ጉባኤ መሀመድ ባገር ጋሊባፍ እንደሚመራ ተገልጿል። የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ እና የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር እንደሚያደራድሩ የሀገሪቱ ዜና አገልግሎት ኢሪብ ዘግቧል።  

ልዑካን ቡድናቸው ፓኪስታን ውስጥ  በመደራደር ላይ ሳለ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ „በርካታ በዓለም ላይ አሉ የሚባሉ ግዙፍ ታንክር ያላቸው መርከቦች ወደ ዮናይትድ ስቴትስ  ምርጥ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ለመጫን እያቀኑ ነው“ ሲሉ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴያቸው ፅፈዋል።  „ኑ እየጠበቅናችሁ ነው“ ሲሉም ትራምፕ አክለዋል። ትራምፕ እንዲሁ ዛሬ ቀደም ብለው ባሰራጩት መልዕክት የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይል የሆርሙዝ ሰርጥን ነፃ ማድረግ ጀምሯል። የኢራን ፈንጅ ቀባሪዎችም በሙሉ እንዲሰምጡ ተደርጓል ብለዋል።

ትራምፕ ይህን ይበሉ እንጂ የሆርሙዝ ሰርጥ ነፃ ስለመሆኑ በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም።

 

 

ጨረቃ አቅራቢያ የነበሩት የጠፈር ተመራማሪዎች በሰላም ወደ ምድር ተመለሱ

ከ50 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ አቅራቢያ የነበሩት የጠፈር ተመራማሪዎች በሰላም ወደ ምድር ተመለሱ። እንደ ብሔራዊ የበረራ ሳይንስ እና የኅዋ አስተዳደር (NASA) ገለፃ የጠፈር ተመራማሪዎቹ በታቀደው መሰረት በፓስፊክ ውቅያኖስ ማረፋቸውን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት አራቱ «አርተሚስ 2»የተባለው  ጠፈር ተመራማሪዎች በሀገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ትናንት አርብ ከአመሻሹ 11 ሰዓት 07 ደቂቃ ላይ እንደታቀደው ሳንዲያጎ አቅራቢያ ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በፓራሹት አርፈዋል።

ሶስት አሜሪካዊ እና አንድ ካናዳዊ የጠፈር ተመራማሪዎቹ  ወደ ምድር የተመለሱት ከአስር ቀናት ቆይታ በኋላ ነው።  የጠፈር ተመራማሪዎቹ በአጠቃላይ ከ 2.3 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ መጓዛቸውም ተገልጿል። ጨረቃን ዙሪያዋን የዞሩት እና ከመሬት ለመጀመሪያ ጊዜ ያን ያህል ርቀው የተጓዙት ጠፈርተኞች ወደ ምድር ሲመለሱ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደነበሩ ናሳ አስታውቋል።

ወደ መሬት የሚደረገውን ጉዞ ከባድ የሚያደርገው ጠፈርተኞቹ ያሉበት ካፕሱል በሰዓት 38,400 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ፍጥነት ስለሚኖረው እና ጠፈርተኞቹን ለከፍተኛ የአካል ጭንቀት ሊዳርግ ስለሚችል ነው።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።