1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ድልድይ መደርመስ

ሰኞ፣ መስከረም 30 2015

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመተላለፊያ ድልድይ ተደርምሶ የአንድ ተማሪ ሕይወት ሲያልፍ በመቶዎች በሚቆጠሩት ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል። አደጋው ሊደርስ የቻለው ተማሪዎቹ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ለመፈተን ከዋናው ግቢ ወደ ቴክኖሎጂ የትምህርት ክፍል በሚወስደው ድልድይ በመሸጋገር ላይ ባሉበት ወቅት ድልድዩ በመውደቁ ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4I0aV
የተደረመሰ ድልድይ ጋር ሰዎች ቆመዋል
ከዋናው የዩንቨርስቲ ግቢ ወደ ቴክኖሎጂ የትምህርት ክፍል የሚወስደው የተደረመሰው ድልድይ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሀዋሳው አሳዛኝ ክስተት

ዛሬ ጠዋት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የደረሰው አደጋ ያልተጠበቀ ብቻ ሣይሆን ልጆቻቸውን ወደ ፈተና ለላኩ ወላጆች አስደንጋጭ የሚባል አይነት ነው። በዩኒቨርሲቲው ግቢ የሚገኘው የመሸጋገሪያ ድልድይ የመደርመሱ ወሬ ከተሠራጨ በኋላ የዩኒቨርሲቲውን አጥር ከበው የሚያለቅሱ ሰዎችን ማስተዋሉን በሥፍራው የነበረው የዶቼ ቬለ DW  ወኪል ዘግቧል። እስከ ረፋድ ድረስም ተከታታይ የአምቡላንስ ምልልሶችንም  መመልከቱንም እንዲሁ። አደጋው እንደተከሰተ በሥፍራው ቀድመው ከደረሱት አንዱ ሄኖክ ገረመው ሁኔታውን «አስደንጋጭ»›  ሲል ነው ለዶቼ ቬለ DW  የገለጸው።  ወደ ግቢው ስገባ ድልድይ ተደርምሶ ነው በሚል ግርግር መፈጠሩን የሚናገረው ሄኖክ «በሥፍራው በርካታ የተጎዱ ተማሪዎችን ተመልክቼያለሁ። አብዛኞቹ ራሳቸውን የሳቱ ናቸው። ይህን ተከትሎ  የተፈታኝ ወላጆችና ሌሎች ነዋሪዎች የዩኒቨርስቲውን ዋና በር በኃይል በመስበር  ወደ ውስጥ ገቡ፤ ተጎጂዎች ወደ ህክምና ከተወሰዱ በኋላ ተጨማሪ የፀጥታ አባላት ወደ ዩኒቨርሲቲው በመግባትና ሰዎቹን በማስወጣት ግቢውን አረጋግተዋል። ያም ሆኖ አሁንም በርካታ ሰዎች ከአጥር ውጪ በመሆን ይላቀሱ ነበር»› ብሏል። 
አደጋውን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቲዎስ አደጋው በዩኒቨርሲቲው የተከሰተው ዛሬ ከጠዋት አንድ ሰዓት ከሃያ አካባቢ መሆኑን አስታውቀዋል። አደጋው ሊደርስ የቻለው ተማሪዎቹ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ለመፈተን ከዋናው ግቢ ወደ ቴክኖሎጂ የትምህርት ክፍል በሚወስደው ድልድይ ላይ በመሸጋገር ላይ ባሉበት ወቅት ድልድዩ በመውደቁ መሆኑን አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል። በአደጋው የአንድ ተማሪ ሕይወት ሲያልፍ በሌሎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን ነው የቢሮው ኃላፊ የገለጹት። 
የዶቼ ቬለ DW  ታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጡት በአሁኑ ወቅት በአደጋው በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጎጂዎች  በከተማው በሚገኙ የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል። የሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል አስተዳዳሪ አቶ ዝናው ሳርሚሶ እሳቸው በሚስተዳድሩት ሆስፒታል ብቻ ከ70 በላይ ተጎጂዎችን ተቀብሎ የህክምና እርዳታ እየሰጠ እንደሚገኝ ለዶቼ ቬለ DW አረጋግጠዋል። አብዛኞቹ ተጎጂዎች በመረጋገጥ የተጎዱና ቀላል የሚባል አይነት ጉዳት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዝናው « ሁለት ተማሪዎች ግን በከባድ ጉዳት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን የቀዶ ህክምና ተደርጎላቸዋል» ብለዋል። 
በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅኖ ማሳደሩ አልቀረም። በተለይ በአደጋው የተደናገጡ ጥቂት ተማሪዎች ሻንጣዎቻቸውን በመያዝ ጊቢውን ለቀው ሲወጡ መመልከታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።፡

የሀዋሳ ዩንቨርስቲ
የሀዋሳ ዩንቨርስቲምስል DW/S. Wegayeh

የተፈታኞች ዝግጅት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ

ዶቼ ቬለ DW በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የፈተናውን አስተባባሪዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አስተባባሪዎቹ ስልክ ባለመመለሳቸውና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ወደ ግቢው እንዲገቡ ባለመፈቀዱ ሊሳካ አልተቻለም። ያም ሆኖ የሲዳማ ክልል ሰላም ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቲዎስ  የፈተና መስተጓጎል ያጋጠመው አደጋው በደረሰበት አካባቢ በሚገኙት የመፈተኛ ክፍሎች ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው እርሻ ኮሌጅ ፣ ሪፈራል ሆስፒታል ፤ ወንዶ ገነት ደን ኮሌጅ ፣ የበንሳና የይርጋዓለም አዋዳ ካምፓሶች ፈተናው በተያዘው መረሃግብር መሠረት እየተሠጠ እንደሚገኝም አቶ ዓለማየሁ ገልጸዋል። ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ላይ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ የሲዳማ ክልላዊ መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው። በጅጅጋ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘውን የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ስብስባ አቋርጠው ወደ ሀዋሳ የተመለሱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ከቀትር በኋላ በሆስፒታሉ ተገኝተው የተጎዱ ተማሪዎችን ጎብኝተዋል። 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ