1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ34 ኢትዮጵያውያን አስከሬን በሊቢያ የጅምላ መቃብር ተገኘ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2011

ከሶስት አመታት በፊት ራሱን "እስላማዊ መንግሥት" ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን በሊቢያ የተገደሉ 34 ኢትዮጵያውያን አስከሬን ከነበረበት የጅምላ መቃብር ተቆፍሮ መውጣቱን የሊቢያ መንግሥት አስታወቀ።የኢትዮጵያውያኑ አስከሬን የነበረበት መቃብር የተገኘው ከሲርጥ ከተማ አቅራቢያ ነው። አስፈላጊው ምርመራ ሲጠናቀቅ አስከሬኖቹ ወደ ኢትዮጵያ ይላካሉ ተብሏል

https://p.dw.com/p/3AbGc
Islamischer Staat Video Christen Libyen
ምስል picture-alliance/AP Photo

ከሶስት አመታት በፊት ራሱን "እስላማዊ መንግሥት" ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን በሊቢያ የተገደሉ 34 ኢትዮጵያውያን አስከሬን ከነበረበት የጅምላ መቃብር ተቆፍሮ መውጣቱን የሊቢያ መንግሥት ባለሥልጣናት አስታወቁ።

የኢትዮጵያውያኑ አስከሬን ትናንት ዕሁድ ታኅሳስ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ተቆፍሮ የወጣው በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለ የታጣቂ ቡድኑ አባል መረጃ ከሰጠ በኋላ መሆኑን በሊቢያ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የወንጀል ምርመራ ክፍል አስታውቋል።

ከሶስት አመታት በፊት በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተሰራጨ ቪዲዮ የቡድኑ ታጣቂዎች ብርቱካናማ መለዮ የለበሱ ሰዎችን በጥይት ደብድበው ሲገድሉ እና አንገታቸውን በስለት ሲቀሉ አሳይቶ ነበር።

በወቅቱ ይፋ የሆነው እና 29 ደቂቃ የሚረዝመው ቪዲዮ «ከጠላቲቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመስቀሉ ተከታዮች» የሚል ርእስ እንደያዘ እና ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ ታጣቂዎች በሁለት ምድብ ኢትዮጵያውያኑን በተርታ ይዘው እንደሚያሳይ ተገልጿል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ የመንግሥት ቃል አቀባይ የነበሩት አቶ ሬድዋን ሁሴን በታጣቂዎቹ የተገደሉት ሰዎች በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው ማረጋገጥ እንዳልቻሉ ተናግረው ነበር።

በሊቢያ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የወንጀል ምርመራ ክፍል ከባሕር ዳርቻ በምትገኘው የሲርጥ ከተማ የሚገኘውን የኢትዮጵያውያኑን የጅምላ መቃብር የሚያሳይ በአብራሪ አልባ አውሮፕላን የተቀረጸ ምስል ይፋ አድርጓል።

በሊቢያ የሚደረገው ምርመራ እና ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ሒደት ከተጠናቀቀ በኋላ አስከሬኖቹ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላኩ የወንጀል ምርመራ ክፍሉ ያሰራጨው መረጃ ይጠቁማል።