«እስላማዊ መንግሥት» 30 ኢትዮጵያውያን ገደለ | ኢትዮጵያ | DW | 19.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

«እስላማዊ መንግሥት» 30 ኢትዮጵያውያን ገደለ

እራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ሊቢያ ውስጥ ዛሬ በአሰቃቂ ኹኔታ መግደሉን የሚያሳይ ቪዲዮ ማሰራጨቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገበ።

29 ደቂቃ የሚፈጀው ቪዲዮ «ከጠላቲቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመስቀሉ ተከታዮች» የሚል ርእስ እንደያዘ እና ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ ታጣቂዎች በሁለት ምድብ ኢትዮጵያውያኑን በተርታ ይዘው እንደሚያሳይ ተገልጿል። ሽጉጥ የያዘ አንድ ታጣቂ፤ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ወደ እስልምና እስካልቀየሩ ድረስ ቡድኑ እንደሚዋጋቸው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ዝቷልም ተብሏል። በመቀጠል ቪዲዮው ውስጥ 12 ሰዎች ያሉበት ቡድን አንገታቸው በካራ ሲቆረጥ፤ ሌሎች ቢያንስ 16 ሰዎች ደግሞ በጥይት ሲገደሉ እንደሚያሳይ የፈረንሳይ ዜና ምንጭ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ የመንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ሬድዋን ሁሴን በ«እስላማዊ መንግስት» የተገደሉት 30 ሰዎች ማንነት ማጣራት አለመቻላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ቃል አቀባዩ አክለው ሲናገሩ «ቪዲዮውን ተመልክተነዋል፤ ሆኖም የተገደሉት ሰዎች ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው ካይሮ የሚገኘው ኤምባሲያችን ማረጋገጥ አልቻለም» ማለታቸውን የዜና ምንጩ አክሎ ተናግሯል። ቃል አቀባዩ «እንዲያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ይኽን አሰቃቂ ድርጊት ያወግዛል» ብለዋል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ሊቢያ ውስጥ ኤምባሲ ባይኖራትም ከሊቢያ ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት ዝግጁ ናት ማለታቸውም ተዘግቧል። ቀደም ሲል ይኽ እራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን 21 የግብጽ ኮፕት ክርስቲያኖችን አንገት የሊቢያ ባሕር ዳርቻ ላይ በስለት መቁረጡ ይታወሳል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ