1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

እየባሰበት የሄደው የፕሬስ ነጻነት ሲዘከር

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 24 2018

ሰሞኑን ዓለማቀፉ የፕሬስ ነጻነት ቀን የሚዘከርበት ነው እና በዓለም ላይ በአፍሪቃን ጨምሮ የፕሬስ ነጻነት በዓመቱ ምን መልክ እንደነበረው ልንዳስስ ነው። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ወይም RSF አዲስ የጎርጎርሳዊያኑን 2026 የዓለም የፕሬስ ነፃነት መረጃ ጠቋሚን ይፋ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/5D7ux
እየባሰበት የሄደው የፕሬስ ነጻነት ሲዘከር
እየባሰበት የሄደው የፕሬስ ነጻነት ሲዘከር ምስል፦ Reporter ohne Grenzen

የፕሬስ ነጻነት በኃያላኑ ጭምር የተጨቆነበት ዓመት ተዘክሯል

በመላው ዓለም ከሚገኙ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት ውስጥ ስራቸውን በነጻነት መስራትን ከመነፈግ እስከ የሕይወት መሰዋዕትነት ማስከፈልን እስከሚጠይቀው አስከፊ ሁኔታ ውስጥ የገቡ እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ ። ሰሞኑ ዓለማቀፉ የፕሬስ ነጻነት ቀን የሚዘከርበት ነው እና በዓለም ላይ በአፍሪቃን ጨምሮ የፕሬስ ነጻነት በዓመቱ ምን መልክ እንደነበረው ልንዳስስ ነው።  ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ወይም RSF አዲስ  የጎርጎርሳዊያኑን 2026 የዓለም የፕሬስ ነፃነት መረጃ ጠቋሚን ይፋ አድርጓል። ጋዜጠኝነት በፖለቲካዊ ጫና፣ በጦርነትና በቴክኖሎጂ ስጋቶች መሀል ሆኖ ነፃነቱን ለማስከበር እየታገለ ነው። በተለይ በአፍሪካ የታዩ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ምን ይመስላሉ የሚለውን ጨምሮ ከተቀረው ዓለም ተሞክሮ ጋር ለአፍታ እንመልከት ። 

የሪፖርቱ አጠቃላይ ግኝትና ትርጓሜ

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ወይም RSF "የፕሬስ ነፃነት" የጋዜጠኞች ግለሰባዊና ስብስባዊ መብት በመበየን ነው ዘገባውን የሚጀምረው። የሕዝብን ጥቅም መሠረት ያደረጉ ዜናዎችን ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ ጣልቃገብነት ነፃ በሆነ መልኩ የማሰራጨት ችሎታ ነውም ይለዋል።

ነገር ግን ድንበር ተሻጋሪው የመብት ተሟጋች በዘንድሮው ዘገባው እንዳሳየው በዓለም ካሉ ሃገራት 75 በመቶው የሚሆኑት የፕሬስ ነፃነት ሁኔታቸው "አሳሳቢ" በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል።

አሌክሳንድራ ቢየላኮቭስካ  የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች (RSF) የእስያ-ፓስፊክ ቢሮ የጥብቅና አማካሪ ቢሮ ኃላፊ  ናቸው።

"በመረጃ ጠቋሚው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ አሁን ላይ ከዓለም ሀገራት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በከባድ እና በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።"

 ከ10 ዓመት በፊት "አስቸጋሪ" የሚባሉ ሀገራት ከጠቅላላው ሲሶ የማይሞሉ የነበሩ ሲሆን፣ ዛሬ ግን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሃገራት በሚዲያ ነፃነት ረገድ ወደ አደገኛ ቀጠና መግባታቸውን ነው ኃላፊቃ የገለጹት ።

"ጠቅላላ ውጤቱ በ2026 ዓ.ም አሽቆልቁሏል፤ ይህም ትልቅ ውድቀት ነው፤ ምክንያቱም ባለፈው ዓመት ከ100 ነጥብ ውስጥ ወደ 56 ነጥብ ገደማ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ግን 54 ነጥብ ብቻ ነው። ስለዚህ በዓለም አቀፍ ውጤት ላይ የአንድ ነጥብ ቅናሽ ታይቷል። በዚህም ምክንያት አሁን ላይ 94 ሀገራት በከባድ እና በጣም አሳሳቢ ምድቦች ውስጥ ይገኛሉ።"

የፕሬስ ነጻነት እየከፋባቸው የሄዱ ሃገራት በካርታ
 ከ10 ዓመት በፊት "አስቸጋሪ" የሚባሉ ሀገራት ከጠቅላላው ሲሶ የማይሞሉ የነበሩ ሲሆን፣ ዛሬ ግን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሃገራት በሚዲያ ነፃነት ረገድ ወደ አደገኛ ቀጠና መግባታቸውን ነው ኃላፊቃ የገለጹት ።ምስል፦ Reporter ohne Grenzen

ኃላፊዋ አፍሪቃዊቷ ኤርትራን ጨምሮ በውድቀቱ ውስጥ የሚገኙ ያሏቸውን ሶስት ሃገራት በስም ዘርዝረዋል።

"ከሁሉም የከፋ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሦስቱ ሀገራት እንደ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ናቸው፤ እነሱም ቻይና፣ ኤርትራ እና ሰሜን ኮሪያ ናቸው። ምንም ሳያስደንቅ ሰሜን ኮሪያ እና ኤርትራ የፕሬስ ነፃነትን ተደራሽ በማድረግ ረገድ አምባገነን ሃገራት ናቸው፤ በእነዚህ ሀገራት ውስጥ ምንም ዓይነት የፕሬስ ነፃነት የለም።"

አውሮጵያዉያኑ ኖርዌይ፣ ኢስቶኒያና ዴንማርክ ደግሞ አሁንም  የፕሬስ ነፃነት ተምሳሌት ሆነው ቀጥለዋል፤ ብሏል።

አፍሪካዊ እውነታዎች፦ የሰሜንና የደቡብ ልዩነት

አፍሪቃ እና የፕሬስ ነጻነት ምስሉ የተደበላለቀ እንደሆነ ነው የዓመቱ የፕሬስ ነጻነት ዘገባ የተመለከተው።   ሪፖርቱ በሰሜን አፍሪካና በደቡባዊው የአህጉሪቱ ክፍል መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት እንዳለ ያሳያል። በሰሜን አፍሪካ  ጋዜጠኞች በአንጻራዊ ሁኔታ ከፍተኛ ጫናና ዝቅተኛ ነፃነት ነው የሚስተዋልባቸው።

በአንጻሩ ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ እንደ አርአያ ተጠቃሽ ሆናለች። ከጎርጎርሳዉያኑ 2013 ጀምሮ "አጥጋቢ" የሚለውን ደረጃዋን ያስጠበቀች ሲሆን፣ እንዲያውም በየዓመቱ እያሻሻለች መምጣቷ ነው የተነገረው። በጆሃንስበርግ የሚገኘው የዊትስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ግሌንዳ ዳንኤል ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያነሱት "ጠንካራ የሲቪል ማኅበረሰብ መኖርን" ነው።

የድምፅ ፕሮፌሰር ግሌንዳ ዳንኤል - ድምጽ ወንድ

"በደቡብ አፍሪካ የጋዜጠኞች መብት የሚከላከለው SANEF የተባለው ፎረም በጣም ድምፁ ከፍ ያለና ጫጫታ ያለው ነው። ይህ ጠንካራ የጥብቅና እንቅስቃሴ በመንግስትና በሌሎች አካላት የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመከላከል ትልቅ ልዩነት ፈጥሯል።"

ጦርነትና ፖለቲካዊ ጥቃቶች

 ሪፖርቱ ሌላው ትኩረት የሰጠው ለጋዜጠኞች ደህንነት ስጋት የሆነው "የትጥቅ ግጭት" ነው። እንደ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ያሉ  ሃገራት ሁኔታ ለዚህ ማሳያ ነው። ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች ጋዜጠኞች ለጥቃትና ለግድያ በቀላሉ ይጋለጣሉ።  በጋዛ ጦርነት ብቻ ከ220 በላይ ጋዜጠኞች መገደላቸውን ሪፖርቱ በአስገራሚ ሁኔታ ጠቅሶታል።

የፕሬስ ነጻነት እየከፋባቸው የሄዱ ሃገራት በካርታ
 ሪፖርቱ ሌላው ትኩረት የሰጠው ለጋዜጠኞች ደህንነት ስጋት የሆነው "የትጥቅ ግጭት" ነው። እንደ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ያሉ  ሃገራት ሁኔታ ለዚህ ማሳያ ነው። ምስል፦ Reporter ohne Grenzen

ከጦርነት በተጨማሪ ፖለቲካዊ ስልታዊ ጥቃቶች ሌላው ተግዳሮት ናቸው። በአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት ጃቪየር ሚሌይ፣ በስሎቫኪያው ሮበርት ፊኮ እና በ አሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ የሚመራው "የጥላቻ ትርክት" ጋዜጠኞችን የሕዝብ ጠላት አድርጎ የመሳል አዝማሚያ አለው። ይህ ደግሞ ወጣቶች ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ እንዳይገቡ የፍርሃት ድባብ እየፈጠረ ይገኛል።

የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች (RSF) የእስያ-ፓስፊክ ቢሮ ዳይሬክተር የሆኑት የሴድሪክ አልቪያኒ እንደሚሉት ደግሞ ለፕሬስ ነጻነት የሚሰጠው ትርጉም ተቋማት እና ግለሰቦች በሚመቻቸው መንገድ እንዲጠቀሙ መፍቀድ አይደለም ።

"የፕሬስ ነፃነት ማለት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የፈለጉትን ለማድረግ ልዩ መብት አላቸው ማለት አይደለም። በተጨማሪም የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶች ወይም ተቋማቱን በባለቤትነት የያዙ ግዙፍ ኩባንያዎች  ሚዲያውን ለግል ጥቅማቸው በሚመቻቸው መንገድ የመጠቀም መብት አላቸው ማለት አይደለም። ይህ የፕሬስ ነፃነት አይደለም።"

መፍትሔውና የትስስር አስፈላጊነት

ታዲያ ይህንን የፕሬስ ነፃነት ማሽቆልቆል እንዴምን መመከት ይቻላል? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም። የሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ቬራ ስላቭቼቫ-ፔትኮቫ  እንደሚሉት መፍትሔው "ትስስር መፍጠር" ነው ። ጋዜጠኞች ብቻቸውን ሲሆኑ ለጥቃትና ለሥነ-ልቦና ጫና ስለሚጋለጡ።

 - ፕሮፌሰር ቬራ - ድምጽ ወንድ

"ለድጋፍ የምትተማመንበት አካል እንዳለ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ጋዜጠኞች ተመሳሳይ እሴት ካላቸው ድርጅቶች፣ የመብት ተሟጋቾችና ምሁራን ጋር መተባበር አለባቸው። ይህ ሲሆን ነው በገንዘብም ሆነ በሕግ የሚመጣባቸውን ጫና መቋቋም የሚችሉት።"

ይህ ምክር በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ያሉ ዴሞክራሲዎች ውስጥ ለሚሰሩ ጋዜጠኞች ወሳኝ መልዕክት አለው። የሙያ ማኅበራትን ማጠናከርና በጋራ መቆም የነፃነት ዋስትና መሆኑን የደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ በተግባር አሳይቷል።

 የዘንድሮው  የRSF ዘገባ ከሞላ ጎደል አንድ ነገር ግልጽ አድርጓል። የፕሬስ ነፃነት በስጦታ የሚሰጥ ሳይሆን በየቀኑ የሚገነባና የሚጠበቅ እሴት ነው። ጋዜጠኞች በነፃነት መሥራት ካልቻሉ፣ ሕዝብ ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብቱን ያጣል። የተቀረው የአፍሪቃ ክፍል ከደቡብ አፍሪካ ጠንካራ የሲቪል ማኅበራት ተሞክሮ በመቅሰም፣ ጋዜጠኞቻቸውን ከጥቃት የሚከላከሉበትን መንገድ ማጠናከር ይኖርባቸዋል።

መነጋት ሹይንስኪ/ ታምራት ዲንሳ