«በትግራይ አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላው ተጠናክሮ ቀጥሏል»
ማክሰኞ፣ ሰኔ 30 2018
በትግራይ ወጣቶችን አስገድዶ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖች የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የተባለ አገር በቀል የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አስታወቀ። በመቐለና አዲስ አበባ የሚኖሩ ወጣቶችም ለዶይቼቨለ በሰጡት አስተያየት አፈሳው ለሕይወታቸውና ቤተሰቦቻቸው ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ተናግሯል። አንድ የሕወሓት ባለሥልጣን ግን ድርጊቱን አልፈጸምንም ሲሉ አስተባብሏል።
ቦታው መቐለ በተለምዶ ቀበሌ 05 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው። አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመልውን በመቃወም፤ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ መናኻሪያ አካባቢ ካደሩበት ሆቴሎችና ከመናኻሪያው ውስጥ በአስገዳጅ ለወታደራዊ ምልመላ የተያዙ ወጣቶች በአውቶቡስ ተጭነው ሊሄዱ ሲሉ የአካባቢው እናቶች በኡኡታና ወደ መኪናው ድንጋይ በመወርወር ተቃዎሞአቸውን ማሰማታቸውን አንድ የመቐለ ከተማ ነዋሪ የሆነ ወጣት ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።
«ከተለያዩ በታዎች የታፈሱ ወጣቶች ዒላላ ትምርት ቤት የሚባል ነው ታጉረው የነበሩት። ከዚያ አውጥተው ሲወስዷቸው እናቶች እያለቀሱ፤ ህጻናትም ወጣቶችም ሳይቀሩ ድንጋይ እየወረሩ ነበረ።»
ይሁንና የእናቶቹ ተቃውሞና ጩኸት ወጣቶችን መታደግ እንዳልቻለ ወጣቱ አጫውቶናል። እሱም መሄጃ አጥቶ መጪውን የሚሆነውን በመጠባበቅ ላይ እንዳለ በማከል።
የአስገዳጅ ምልመላውን የተቃወሙ ወጣቶች ወደ አዲስአበባና ወደ ተለያዩ የስደት መዳረሻዎች እየሄዱ እንደሆነ ዘገባዎች ያመላክታሉ። ወደ አዲስ አበባ ከሄዱት ወጣቶች አንዱ ወጣቶቹ አፈሳውን ፈርተው ያለበቂ ዝግጅት ስለሚመጡ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጡ እንደሆነ አጫውቶናል።
የህወሓት ምላሽ
በትግራይ አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን የሐገር ውስጥና የውጭ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋማት በማስረጃ አስደግፈው እያወገዙት ይገኛሉ። በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተነፈገውህወሓት የሥራ አስፈጻሚ ኮኒቴ አባል ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ግን ድርጊቱን አልፈጸምንም ሲሉ በቅርቡ ለክልሉ የመገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።
« አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመል አስመልክቶ ከተወሰነ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ አካላት እየተስተጋባ ያለው ጉዳይ ፈፅሞ ከትግራይ ሁኔታ ጋር የሚሄድ አይደለም። ህወሓት የ 50 ዓመታት ታሪክ ያለው ድርጅት ነው። ዓላማውን አሳምኖ ነው ሕዝብን ከጎኑ የሚያሰልፈው። ስለዚህ ይህ አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ የሚባል ነገር ሆን ተብሎ በትግራይ እየተካሄደ ያለውን ትግልን ጥላሸት በመቀባት በትግራይ ሌላ ሽብር ለመፍጠር የሚደረግ የጠላት ዘመቻ ነው። ትክክል አደለም። ህወሓት ከዚህ ቀደምም አስገድዶ አያውቅም፤ አሁንም አያስገድድም።»
የሰብአዊ መብት ተሟጓች ምልከታ
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ከአንድ ወር በፊት በማስረጃ አስደግፎ ድርጊቱን ያጋለጠው ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያየተባለ አገር በቀል የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ግን ከሪፖርቱ በኃላም አፈሳው ተጠናቅሮ መቀጠሉን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ።
« ከአንድ ወር በፊት አስገዳጅ ምልመላ እየተካሄደ እንደሆነ በማስረጃ አስደግፈን ሪፖርት ማቅረባችን ይታወሳል። ከዚያ በኃላ ባለው ጊዜም ክትትል ስናደርግ ነበር። የክትታላችን ውጤት እንደሚያመላክተው በትግራይ አስገጅ ወታደራዊ ምልመላው ተጠናክሮ መቀጠሉን ያሳያል።»
በተለያዩ የትግራይ ከተሞችና ገጠሮች የአስገዳጅ አፈሳውን በመቃወም ተቃዎሞዎች እየተካሄዱ እንደሆነና በተለይ በገጠር አካባቢዎች ወጣቶች በጫካዎች ለመኖር መገደዳቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ አክለዋል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ታምራት ዲንሳ