«ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትም የምልመላው ሰለቦች መሆናቸውን አረጋግጠናል»
ዓርብ፣ ግንቦት 28 2018
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብት የተባለ አገር በቀል የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ነው ባለው አስገዳጅ ወታደራዊ የምልመላ ድርጊትን እንዲያወግዝና እንዲያስቆም ጥሪ አደረገ። የፌደራል መንግስትም ለግጭቶች ገፊ ሊሆኑ የሚችሉ እንደ ተፈናቃዮችን ወደቀያየቸው የመመለስና ነዳጅንና በጀትን ጨምሮ ተገቢ አገልግሎቶች እንዲያቀርብም ጥሪ አድርጓል። የሕወሐት ቃል አቀባይ ግን የድርጅቱን የምርመራ ዘገባ «ውሸት» ሲሉ አጣጥለውታል።
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብት ባወጣው የምርመራ ዘገባና ለዶይቼቬለ በሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ በትግራይ እየተካሄደ ነው ያለውን አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሕገ መንግስትን፣ የአፍሪካ መብቶች ቻርተርና የዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የሚጥስ ነው ብሎታል። አቶ መብርሒ ብርሃነ የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር።
ከ18 ዓመት በታች ስለመመልመላቸው
«የአይን እማኞች፣ ወጣቶች፣ መልማዮች እና ቤተሰቡች ቃለ መጠይቅ በማድረግ ነው ሥራውን የሰራነው።»
ምክትል ዳይሬክተሩ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትም የምልመላው ሰለቦች መሆናቸውን በምርመራ ማረጋገጣቸውን አክለዋል።
«ከ 18 ዓመታ በታች የሆኑ ለምሳሌ አንድ ቦታ ላይ የ 16 ዓመት ወጣት፤ እንደዚሁም ሌላ ቦታ የ15 ዓመት፤ እንደዚሁም ካመለጡት ደግሞ ዕድሜኃቸው 17 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች ያሉበት መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል።»
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች በፅሑፍ ባሰራጨው የምርመራ ዘገባ በትግራይ እየተካሄደ ነው ያለውን አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እንዲቆም፣ ለዚሁ ተግባር በየትምሕርት ቤቱና ወታደራዊ ካምፖች የተሰባሰቡ ወጣቶች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል።
የህወሐትቃልአቀባይ ምላሽ
በዚህ ጉዳይ ላይየህወሐትቃል አቀባይ አቶ ሚኪኤለ አስገዶምን አነጋግረናል። አቶ ሚኬኤለ የትግራይ ወጣት ለመብቱ ሲል በፍላጎቱ የመታገል ልምድ ማዳበሩን ገልጸው ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ በማስረጃ ያልተደገፈና፤ የገለልተኝነት መርሕን ያልተከተለ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
«አንድ አካባቢ ቁጭ ብሎ ቦታውን ሳያስስ መረጃም ሳይኖረው፤ ሆን ብሎ ለማጠልሸትና ትግራይ ላይ የሌለ ነገር እንዳለ አድርጎ እየዘገበ ነው የሚገኘው።»
የድርጅቱ መግለጫ እርስዎ እንዳሉት እንደሐሰት ቢቆጠር እንኳን በርካታ የትግራይ ወጣቶች በየግል የማሕበራዊ መገናኛ መረቦቻቸው አስገድዶ ለውትድርና የመውሰዱ ሁኔታ እየተቃወሙ ነው። ይህንስ እንዴት ያዩታል አልናቸው።
«በጣም በርከት ያሉ የትግራይን ሕዝብ ደው ወደ አዲስ አበባ የመሸጉ የብልጽግና ተልዕኮ ይዘው የሚሰሩ በጣም ብዙ ብር እየበተኑ ትግራይ ውስጥ የውሸት ትርክት እንዲሰራጭ በቲክቶክም በማሕበራዊ ሚድያም በብዙ ነገሮች እኮ እየታገሉ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው።»
በማሕበራዊ መገኛኛ ብዙኃን ከሚሰራጩ ድምጾች አንዱ
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ፤ከአሁን በኋላ ሊካሄድ የሚችለውን ጦርነት የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ በርካታ የትግራይ ወጣቶች ከአሁን በኋላ የሚካሄድ ጦርነት እንደማይወክላቸውና መሳተፍም እንደማይፈልጉ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲገልፁ ተመልክተናል። ከነዚህም መካከል ተከታዩ አስተያየት ይገኝበታል።
« እኔ ሞቼ እናቴ እሚያነሳት አጥታ ሐዘን ውስጥ እንደምትኖር እያወቅኩኝ፤ እኔ እግሬን ተቆርጬ እሚያነሳኝ አጥቼ ጎዳና ላይ ወጥቼ እንደምለምን እያወቅኩኝ፤ እኔ እራስቅሌ ውስጥ የአረር ቅሪት ተሸክሜ ማሳከሚያ አጥቼ እየተሰቃየሁ እንደምኖር እያወቅኩኝ፤ አገሬ ከታገለላት ያውደለደለን እንደምታኖር እያወቅኩኝ፤ መሞቴ እኮ አይቀርም፤ ግን ! እናቴን አሳዝኜ ጎረቤትን ለማስደሰት አልሞትም!»
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብት በመግለጫው ወጣቶች እግር ኳስ ከሚያዩባቸው የመዝናኛ ቦታዎች፣ የጸበል ቦታዎች፣ የቢንጎ መጫወቻዎችና በባሕላዊ መንገድ ወርቅ ከሚለቅሙበት እንደሚለቀሙ አመልክቷል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ፀሐይ ጫኔ