1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ቤተ-ውበት በአርጎባ 

ሐሙስ፣ ጥቅምት 15 2011

በየትኛውም ባህል ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ውበትን ያደንቃሉ። ስለውበት ተዜሟል፣ ተገጥሟል፣ ተጽፏል። ውበት የአንድ ነገር መስህብ፤ የሚያረካ ወይም የሚያስደስት ገጽታ ነው።ውጫዊ ቅርጽን፣ ቀለምን፣ መጠንን ፣ መልክን፣ ደምግባትንም ያመለክታል። የአርጎባ ብሔረሰብ ሴቶችም ወይባ ጭስን ለውበት መጠበቂያ ይጠቀሙበታል።

https://p.dw.com/p/37CdZ
Argoba  Volksgruppe in Äthiopien
ምስል፦ Nurhussein Mohammed

ቤተ-ውበት በአርጎባ 

የአርጎባ ብሄረሰብ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ማለትም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በሀረሪ ውስጥ ይኖራሉ። አርጎባ  የሚለው የብሄረሰቡ መጠሪያ አረብ ገባ ከሚለው የመጣ መሆኑ ይነገራል። የአርጎባ ቋንቋ ወደ አማርኛ ቋንቋ ዘዬ ወሰድ ቢያደርገውም የተለየና ራሱን የቻለ ቋንቋ ነው። በአማርኛ ቋንቋ ጫና ምክንያት ተዳክሞ በመጥፋት ላይ ያለ ቋንቋ ነው መሆኑን እታገኘሁ አስረስ በያዝነው የኢትዮጵያዊያን አመት ባቀረበችው የአርጎባ ብሄረሰብ አፋዊ ትውፊቶችና መገለጫዎች ጥበቃ በሚለው የጥናት ጽሁፏ ጠቁማለች።

በአርጎባ ብሄረሰብ የአለባበስ፣ የሰርግ ፣ የሀዘን ስርአቱ ሌሎችም ማንነቱን መግለጫ የሆኑ ባህሎች አሉ። የውበት መጠበቂያ ባህሉ ደግሞ አንዱ ነው። ብሄረሰቦች እንደባህላቸው መዋቢያ አድርገው የሚጠቀሙባቸው አሉ። 

ጭስ የአርጎባ የሴቶች ውበት መጠበቂያ መሆኑን ሁለት የብሄረሰቡ ተወላጆች አጫውተውኛል። ወ/ት ጀሚላ አህመድ የባህልና ታሪክ ባለሙያ እና ወ/ሮ ከድጃ መሀመድ እንደገለጸሉኝ፣ ሴቶቹ ለውበት መጠበቂያ በአካባቢው በሚገኙት የወይባ እና አዝጋሮ ይጠቀማሉ። የአጠቃቀሙ ሂደት ምን እንደሚመስል ወ/ት ጀሚላን ጠይቂያት ነበር።

«አንዲት ሴት ለወይባ ስትዘጋጅ መላ ሰውነትዋን ቅቤ ትቀባለች። ወይባውን ትሞቃለች። ከዛም በደንብ ገላዋን ትታጠባለች ። አዝጋሮ የሚባል እንጨት አለ እሱን ትሞቃለች። ወይባ የራሱ የሆነ ሽታ ለመቀየር ጠረንዋ እንዲጣፍጥ አዝጋሮውን ትጠቀማለች።» 

ወይባ ጭስ ከውበት ባለፈ በጤናው በኩል ፍቱን ፈውስ እንደሆነ ወ/ት ጀሚላ ገልጻልኛለች። የወገብ ህመምን ያሻላል፣ የወለደችንም ሴት እንድትጠነክር ያደርጋል። የወይባ ጭስን ለመሞቅ የተለያዩ እቃዎች እንደሚያስፈልጉ እና አንዲት ሴት የመታጠኑን ስርዓት ከመጀመሯ በፊት ልታደርጋቸው የሚገቡ ማድረግ ቅድመ ዝግጅቶች መኖራቸውን ወ/ሮ ከድጃ አስረድተዋል። 
«መሬቱ ይቆፈርና እዛ ውስጥ እሳቱ ይገባል። ሴትየዋን እሳት እንዳይሰማት። ጭሱ ብቻ እንዲሆን ከላይ የበሬ ቁርበት መልበስ ነው።» 
ጭሱ የበለጠ ውበት እንዲኖራትና እንዲያምርባት ያደርጋታል። በወጣትነቷ ጭሱን ትታጠን ከነበረ ውበቷ ብታረጅ እንኳን ወዟ እንዳለና እንዳማረባት ምስክርነት በእይታ መስጠት ይቻላል ትለናለች ጀሚላ። 
«የበለጠ ውበት እንዲኖራት እንዲያምርባት ነው የሚያደርጋት አርጅታ እንኳን።» በተለምዶ የወይባ ጭስን የሚታጠኑት ባለትዳር ናቸው። ነገር ግን ልታገባ ያለች ሙሽራ ከሰርጓ ቀን ቀደም ብላ ወይባ ትሞቃለች።  ውበቷ ለ6 ወር ምንም ሳትጠቀም ሊቆይ እንደሚችል ወ/ት ጀሚላ ገልጻልኛለች። «ሰርጓ የደረሰ ሴት ቀደም ብላ ወይባ ትታጠናለች።»  

Karte Äthiopien englisch

ባልና ሚስት የሚግባቡበት ሚስጢራዊ ቋንቋም ነው። የአርጎባ ሴት ከውበት ማስዋቢያም ባለፈ ለባልዋ ፍላጎቷን የምትገልጽው ጭሱን በመታጠን ነው። ከወይባ ጭስ በተጨማሪ ያሉትን የተቀመሙትን ጭስ ትጠቀማለች። ይህን ጭስ መታጠን ማለት ለባልዋ ትርጉም አለው። ሚስት የጾታዊ ግንኙነት ፍላጎት ሲኖራት በቃላት መግለጽ አይጠበቅባትም እንደአርጎባ ብሄረሰብ። መልካም መአዛ ያለውን ጭስ መሞቅ በቂዋ ይሆናል።  «የአርጎባ ሴት ፍላጎትዋን የምትገልጸው ይሄንን ጭስ በመጠቀም ነው።» እናንተስ ትጠቀማላችሁ ወይ በየስንት ጊዜ አልኳቸው። ወሮ ከድጃ ከ15 አመታቸው ጀምሮ ለተከታታይ 35 አመታት አሁን እስካሉበት እድሜ ድረስ በሳምንት ሁለት 2 ጊዜ የወይባ ጭስ እንደሚሞቁ ነግረውኛል። «እኔ አላገባሁም ሳገባ ግን መጠቀሜ አይቀርም። ያላገባች ሴት ማድረግ አትችልም።» 

አቶ ኑር ሁሴን መሀመድ ሲራጅ ይባላሉ። በአፋር ክልል የአርጎባ ልዩ ወረዳ ባህል ቱሪዝምና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሀላፊ ናቸው። የማንነቱ መገለጫ የሆኑ እሴቶቹን እንዳይጠፋ በመንከባከብ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ በተለያዩ ግንዛቤ በማስጨበጫ መንገዶች ለህብረተሰቡ የማስተላለፍ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸውልኛል። ባህል ቋንቋ ማንነት ስራዎችንም እየተሰራ ነው። ባህል የማንነት መገለጫ መሆኑን  አውቆ እንዲጠብቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረ ነው አቶ ኑርሁሴን እንዳሉት።  

ነጃት ኢብራሂም 

አርያም ተክሌ