1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወቅታዊ ሁኔታ የኦሮሚያ ክልል መግለጫ

ሰኞ፣ ኅዳር 19 2015

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዓመቱ የመጀመሪያ አራት ወራት በክልሉ የተከናወኑ አበይት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ አተኩረዋል። መንግሥት «ሸኔ» የሚለውና ራሱን «የኦሮሞ ነጻነት ጦር» በሚል ከሚጠራው ቡድን ጋር ለድርድር ለመቀመጥ እቅድ እንደሌለም አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/4KCBQ
Äthiopien Hailu Adugna
ምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ


መንግሥት «ሸኔ» በሚል ስም በአሸባሪነት ከፈረጀው «የኦሮሞ ነጻነት ጦር» በሚል ራሱን ከሚጠራው ቡድን ጋር ለድርድር ለመቀመጥ ምንም እቅድ እንደሌለ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በስፋት ታጥቆ የሚንቀሳቀሰውና በተለያዩ ጊዜያትም በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ብዙ ይዞታዎች ስለመያዙ ከሚነገረው ቡድኑ ጋር መንግሥት በሰላማዊ መንገድ ኦሮሚያ ውስጥ ለተባባሰው ግጭት እልባት እንዲሰጥ ይጠየቃል። ይሁንና ቡድኑ ማዕከላዊ አዛዥ የሌለው መሆኑ ከወታደራዊ እርምጃ ውጪ ሌላ አማራጭ እንዳይወሰድ እንቅፋት መሆኑን የክልሉ መንግሥት ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል፡፡ የክልሉ መንግሥት በዛሬው መግለጫው በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተባባሰ ለመጣው አለመረጋጋትም «ሸኔ» እና «የአማራ ጽንፈኛ ኃይል» ያላቸውን በግጭት ቀስቃሽነት ከሷል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዓመቱ የመጀመሪያ አራት ወራት በክልሉ የተከናወኑ አበይት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ አተኩረዋል። አሁን አሁን በተለያዩ አቅጣጫዎች አለመረጋጋቶች ቀጥለው በሚስተዋልበት በክልሉ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ7 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ከ22 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ባለፉት አራት ወራት መሰብሰብ መቻሉ ተነግሯል። በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሻለ ስኬትን በዘንድሮ ዓመት አሳክቷል በሚባልለት በክልሉ በ2014/15 የምርት ዘመን 209 ሚሊየን ኩንታል የተለያዩ የእህል ምርቶች እንደሚሰበሰቡና እየተሰበሰቡም መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የቢሮው ኃላፊው አቶ ኃይሉ አዱኛ በመግለጫቸው እንዳመለከቱትም ግብርናን ጨምሮ የልማት ሥራዎቹ የተሳኩት የፀጥታ ችግሮች ባሉባቸው የክልሉ አከባቢዎች ጭምርም መሆኑን ነው ያመለከቱት።በኦሮሚያው ግጭት የአብንና የኦፌኮ ውዝግብ
 «ለአብነት የፀጥታ ችግር ባለባቸው በአራቱም የወለጋ ዞኖች የመንግሥት ገቢ መሰብሰብ ከነበረበት 95 በመቶ በላይ መሰብሰብ ተችሏል። በዓመቱ በኦሮሚያ ክልል ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ1.5 ቢሊየን ብር በላይ ሲሰበሰብ ገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ከተሳካባቸው አከባቢዎች የወለጋ ዞኖች በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። የግብርና ሥራውም በተመሳሳይ በሁሉም ቦታ ታርሷል» ብለዋል። 
ይሁንና «የጠላቶቻችን ግብ አንግቦ ይንቀሳቀሳል» በሚል የከሰሱት «ሸኔ» ያሉት «የኦሮሞ ነጻነት ጦር» በሚል መጠሪያ በኦሮሚያ በሰፊው የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ከሚደርስ ጥቃት ጀርባ ያለ ነው ብለውታልም። «አሸባሪ» በማለት የጠሩትን ታጣቂውን ቡድን ለተቀላቀሉት የሰላም ጥሪ በክልሉ መንግሥት በይፋ ቀርቧልም ነው ያሉት። 
በሰሜን ኢትዮጵያ ለድፍን ሁለት ዓመታት የቆየውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በቅርቡ የሰላም ስምምነት በመንግሥት እና በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል መደረሱን ተከትሎ በኦሮሚያም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል የሚሉ ድምጾች በጉልህ ሲሰሙ ነበር። ከዚሁ በመነሳት መንግሥት በኦሮሚያ እስካሁን መሻሻል ያላመጣውን የፀጥታ ሁኔታ እልባት ለመስጠት በውይይት በዳበረ መንገድ በሰላም ለችግሩ እልባት ለመስጠት ያልማል ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኃይሉ አዱኛ፡ «ቡድኑን ለተቀላቀሉና ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ለሚፈልጉ ወጣቶች የቀረበ ጥሪ እንጂ እንደ መንግሥት ከቡድኑ ጋር ለሰላማዊ ንግግር የመቀመጥ እቅድ የለም» ነው ያሉት። ለዚህም ያቀረቡት ምክንያት በታጣቂ ቡድኑ መካከል አንድነት እና ማዕከል የለም የሚል ነው። የኦሮሚያ ክልል አለመረጋጋት እና የዜጎች ሰቆቃ
በቅርቡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) በኦሮሚያ ውስጥ በሚካሄደው ግጭትና ጦርነት ንጹሐን ሰለባ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፤ መንግሥት በዚህ ረገድ ኃላፊነቱን በተገባ መንገድ አልተወጣም ሲሉ ወቅሰዋል። በተለይም ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ እና አሙሩ ወረዳዎች ውስጥ በርካቶችን ስላፈናቀለውና ሕይወትን ስለቀጠፈው ግጭትም ተጠይቀው በአከባቢው ሸኔ ያሉት ኃይል እና የአማራ ጽንፈኛ ያሉዋቸው አካላትን በግጭት አነሳሽነት ወቅሰው፤ አብሮ የተዋደቀ ያሏቸው ወንድማማች የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብን የሚያጋጭ አጀንዳ የለም ብለዋል። 
«የሽብር ኃይል ሸኔ እና በአማራ በኩል ያሉ ጽንፈኞች ሰላማዊውን ህዝብ በተለያዩ ጊዜያት ለማጋጨት ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል። ህዝባችን መረዳት ያለበት የሁለቱም ውጥን አብሮ ተዋድቆ የአገር ልዓላዊነትን የሚያስከብረውን ወንድማማች ህዝብ ማባላት ነው። ምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ውስጥ የተስተዋለውም ይሄው ነው። ኅብረተሰቡ ነቅቶ አንድነቱን ከጠበቀ ሁለቱን ህዝብ የሚያጋጭ የለም» ሲሉም ኃላፊው ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በነዚህ አከባቢዎች በየጊዜው በሚያገረሹ ግጭቶች በሁለቱም ማኅበረሰቦች በኩል በርካቶች ሲገደሉ ሀብት ንብረታቸው ወድሞባቸው የተፈናቀሉም ቁጥራቸው የበዛ መሆኑ በተደጋጋሚ መዘገቡ አይዘነጋም።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ