1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያው ግጭት የአብንና የኦፌኮ ውዝግብ

ረቡዕ፣ ኅዳር 14 2015

ኦሮሚያ ክልል በብዙ አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማስቆም መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ሊያውጅ ይገባል ሲል የአማራ ብሔራዊ ንቅማቄ (አብን) አሳሰበ። ተቃዋሚ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ነገሮች እንዲባባሱ ያደርጋሉ ሲልም ከስሷል። የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ ለችግሮች መባባስ አብንን ይወቅሳል፡፡

https://p.dw.com/p/4JxOw
Logo | National Movement of Amhara

በኦሮሚያ የቀጠለው ግጭት


ከቅርብ ወራት ወዲህ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ከየአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ የአማራ ተወላጆች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ችግሩ የከፋ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የብሔራዊ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተክለማሪያም ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
«በኦሮሚያ ክልል በተለይ በሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ በምሥራቅ ሸዋ፣ በወለጋ፣ ያለው ነገር እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው። የታጠቀ ሠራዊት ኦነግ ሸኔ፣ በኪራሙ በደራ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና ፖሊስ ጭምር በጥቃቱ እየተሳተፉ ነው፡፡ በተለይ ምሥራቅ ወለጋ ውስጥ ብዙ ሰዎች ሞተዋል፣ አንድ ሳምንት ሆኖታል፡፡» እንደ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተቃዋሚ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ችግሩ እንዲባባስ ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ነው፣ «የአማራ ፋኖም ሆነ የአማራ ልዩ ኃይል በአካባቢዎቹ አሉ» የሚባለውንም ፈፅሞ ሀሰት ነው ብለዋል፡፡

በነቀምቴ ተፈጸመ የተባለው ጥቃት
«በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ኦፌኮን ኦነግን ጨምሮ ከኋላ ሆነው ይህንን ስለሚያራግቡ የአማራ ፋኖ የአማራ ልዩ ኃይል በኦሮሚያ ውስጥ እያጠቃ ነው የሚል የዘር ማጥፋት ምክንያት ነው እየሰጡ ነው ያሉት፣ የአማራ ፋኖና የአማራ ልዩ ኃይል በጭራሽ በዚያ አካባቢ እንደሌለ የታወቀ ነገር ነው፣ ሊገባም አይችልም፣ ምንም የታወቀ ነገር ነው፣ ምክንያት ነው፡፡»
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሙላቱ ገመቹ ግን የተባለውን አይቀበሉም፣ ይልቁንም አብንና ደጋፊዎቹ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ ናቸው በማለት ተናግረዋል፡፡
«ፋኖ አለ አይደል እንዴ! በሁሮ ጉድሩ በኩል አስገብቶ ህዝብ በጠቅላላ የሚናጠው በዚያ በኩል ባለው ነው፣ እነሱ እኮ ጦርነት ውስጥ ተካፍለዋል፣ አብን፣ እኛ ጦርነትን ስናወግዝ የሰሜኑን ጦርነት ሁሉ ተካፍለውበታል፣ ሕገመንግሥቱ ይከበር ስንል ሕገመንግሥቱ እንዳለ ይፍረስ የሚሉ ሰዎች ናቸው እኮ ይህን ሁሉ የሚያደርጉት፣ በአገሪቱ ውስጥ ሁል ጊዜ ግጭት እንዲኖር የሚቀሰቅሱት የእነሱ አባላት ናቸው፡፡» ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል ግጭትና የመንግሥት ማስተባበያ
የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግሥታት እንዲሁም በአማራ ስም የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ችግሩን ማስቆም እንደሚኖርባቸውም ዶ/ር ቴዎድሮስ አሳስበዋል፡፡ የኦፌኮው ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙላቱ ገመቹ በዚህ ዘመን ጠመንጃ አንስቶ መገዳደል ተገቢ ባለመሆኑ ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ መፈታት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የአብን ሥራ አስፈፃሚ አባል ዶ/ር ቴዎድሮስ ተክለማሪያም በበኩላቸው አሁን የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ እንዲታወጅና መከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ ጠይቀዋል፡፡ አንደኛው የሌላውን ታጣቂ ተጠያቂ በሚያደርገው በሰሞኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች ግጭቶች የአማራም ሆነ የኦሮሞ ንፁሐን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለመፈናቀል ተገድደዋል፡፡ ስለተፈጠረው የሰላም መደፍረስና ስለዜጎች ስቃይ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት የአማራንም ሆነ የኦሮሚያን ክልል ባለሥልጣናትን ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት አልተሳካም፡፡
ዓለምነው መኮንን

Äthiopien Oromo Federalist Congress
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ጽሕፈት ቤት ምስል Seyoum Getu/DW

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ