1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይሎች የደቡብ አፍሪካ የሰላም ንግግር አንድምታ እና ተግዳሮቶች

ሐሙስ፣ መስከረም 26 2015

በደቡብ አፍሪካ ለሚደረገው የሰላም ንግግር የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ፐምዙሌ ምላቦ ኑካ አደራዳሪ እንደሚሆኑ ዲፕሎማቶች ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ባለሥልጣናት በመካከላቸው የበረታውን የመተማመን እጦት እንዴት ይፈቱታል?

https://p.dw.com/p/4HrUR
Kombobild | Uhuru Kenyatta, Olusegun Obasanjo, Phumzile Mlambo-Ngcuka

ከአቶ ባይሳ ዋቅወያ ጋር የተደረገ ቃለመጠይቅ

ለ23 ወራት አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ የሚል ግን ደግሞ ደም አፋሳሽ ውጊያ በኋላ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የትግራይ አስተዳደር ባለሥልጣናት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ንግግር ለመጀመር ተዘጋጅተዋል። የአፍሪካ ኅብረት ሁለቱን ወገኖች ወገኖች ለማደራደር ያቀረበውን ግብዣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እና ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የትግራይ አስተዳደር መቀበላቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመሩት ተደራዳሪ ቡድን አቋቁሟል። የትግራይ አስተዳደር በወገኑ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ እና አቶ ጌታቸው ረዳ የተካተቱበት የተደራዳሪ ቡድን ሰይሟል። ከተሳካ ውጊያ ከተቀሰቀሰበት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ወዲህ የመጀመሪያው መደበኛ ድርድር ይሆናል።

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የተካተቱበት የተደራዳሪዎች ቡድን ማቋቋሙን ገለጸ

ሁለቱ ወገኖች ተኩስ አቁመው ልዩነቶቻቸውን በድርድር ግፊት ከሚያደርጉ ዲፕሎማቶች አንዷ የሆኑትን የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔተ ቬበር ባለፈው ነሐሴ ኢትዮጵያ ደርሰው ከተመለሱ በኋላ አነጋግሪያቸው ነበር። አኔተ በወቅቱ እንደተናገሩት በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው "የመተማመን እጦት" ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው ድርድር "ዋና እንቅፋት" ሆኗል። በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ይኸው የመተማመን እጦት በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና በትግራይ መስተዳድር ባለሥልጣናት መካከል ሊደረግ ለሚችል ድርድር ፈተና መጋረጡን በተመሳሳይ ተናግረው ነበር። 

ለድርድር "የመተማመን እጦት ዋና እንቅፋት" እንደሆነ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑክ ተናገሩ

አሁን የአፍሪካ ኅብረት፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታ እና ሌሎች በማደራደር ሒደቱ ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቁ ወገኖች ይኸን እንቅፋት ለማስወገድ ምን መሳሪያ አላቸው?የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባልደረባ እና የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ አቶ ባይሳ ዋቅወያ በጉዳዩ ላይ ለዶይቼ ቬለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከአቶ ባይሳ ዋቅወያ ጋር የተደረገውን ቃለመጠይቅ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ