1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለድርድር "የመተማመን እጦት ዋና እንቅፋት" እንደሆነ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑክ ተናገሩ

ዓርብ፣ ሐምሌ 29 2014

የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔተ ቬበር ከኢትዮጵያ "መንግሥት በኩል የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር ምልክት ከሰጠ ወይም ካስጀመረ ህወሓት በጠረጴዛ ዙሪያ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በመቐለ ጉብኝታችን ተረድቻለሁ" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ቬበር እንደሚሉት ለድርድር "የመተማመን እጦት ዋና እንቅፋት" ነው።

https://p.dw.com/p/4FCSc
Dr. Annette Weber
ምስል SWP

በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል ያለው "የመተማመን እጦት" ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው ድርድር "ዋና እንቅፋት" እንደሆነ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔተ ቬበር ተናገሩ። ልዩ ልዑኳ ከኢትዮጵያ መልስ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በትግራይ ክልል የተቋረጡ አገልግሎቶችን ማስጀመር ለድርድሩ መንገድ እንደሚጠርግ እምነታቸውን ገልጸዋል። 

ወደ አዲስ አበባ እና ወደ መቐለ አቅንተው ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከትግራይ ክልል ባለሥልጣናት የተነጋገሩት አኔተ ቬበር "አንዱ ከሌላው ጋር በቅን ልቦና እየተደራደሩ ለመሆናቸው የበለጠ መተማመኛ እንደሚፈልጉ ሁለቱም ግልጽ አድርገዋል። ሁለቱ ወገኖች ዝግጁነታቸውን ከማሳወቅ ባሻገር ወደ ድርድሩ እንዲመጡ የሚያስፈልገውን መተማመን [የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ] ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ያጠናክራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ለድርድሩ "መንግሥት ተጨማሪ ቅድመ-ሁኔታዎች እንደሌሉት አረጋግጧል" ያሉት ልዩ መልዕክተኛዋ "ከመንግሥት በኩል የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር ምልክት ከሰጠ ወይም ካስጀመረ ህወሓት በጠረጴዛ ዙሪያ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በመቐለ ጉብኝታችን ተረድቻለሁ" ሲሉ አስረድተዋል። 

ባለፈው ሣምንት በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ምኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ደመቀ መኮንን ተገናኝተው ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች መካከል ይኸው የድርድር ጉዳይ አንዱ ነበር። ልዩ ልዑኳ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓትን ለማደራደር የአፍሪካ ኅብረት የሚያደርገውን ጥረት "ለመደገፍ" ከአሜሪካ አቻቸው ማይክ ሐመር ጋር ወደ መቐለ ተጉዘው ከትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ተነጋግረዋል። 

አኔተ ቬበር እና በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ባለፈው ሐምሌ 26 ቀን 2014 ባወጡት መግለጫ የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የተቋረጡ አገልግሎቶችን ሥራ ለማስጀመር ወደ ክልሉ ለሚሔዱ ባለሙያዎች የደህንነት ማረጋገጫ የሚሰጥ ደብዳቤ ለፌድራል መንግሥት መላካቸውን ገልጸው ነበር። 

የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን ትላንት ሐሙስ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት መንግሥታቸው በትግራይ ክልል የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ ማረጋገጡን ገልጸዋል። ይኸ "አሁን፤ እጅግ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ አኔተ ቬበር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ማስጀመር በሁለቱ ወገኖች መካከል ለሚደረግ ድርድር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ልዩ ልዑኳ እምነታቸው ነው። "መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ መጀመራቸውን እየተጠባበቅን ነው። በዚህ ረገድ ከአዲስ አበባም ሆነ ከመቐለ የተቀየረ ነገር ካለ አልሰማሁም። ነገር ግን ይኸ በማንኛውም ቀን ተግባራዊ ይሆናል ብዬ እጅግ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል። 

የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ወደ ነበረበት ለመመለስ በሶስት ማዕቀፎች የተከፋፈሉ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል። በትግራይ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ ማስጀመር እና ያለ ገደብ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቀርብ ማመቻቸት በመጀመሪያው ማዕቀፍ የተካተቱ ናቸው። ሁለተኛው የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀፍ የተኩስ አቁም እና የፖለቲካ ውይይትን ሲካትት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በመፈጸም የሚጠረጠሩን ተጠያቂ ማድረግ ሶስተኛው ነው። ተኩስ በማቆም እና በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ረገድ የታየውን መሻሻል የአውሮፓ ኅብረት እንደሚያደንቅ የገለጹት አኔተ ቬበር የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ሥራ ማስጀመር እንደሚያሻ ጠቁመዋል። 

አኔተ ቨበር እና ማይክ ሐመር በጥምረት ያወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥትን አበሳጭቷል። የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ሬድዋን ሑሴን ልዩ ልዑካኑ ህወሓትን "በማያሻማ መልኩ ለሰላም ድርድር ቁርጠኛ እንዲሆን ግፊት ማድረግ አልቻሉም" ሲሉ ተችተዋል። ሁለቱ ልዩ ልዑካን ህወሓትን "ማባበል እና ቅድመ ሁኔታዎቹን ማሟላት" ላይ እንዳተኮሩ የጠቀሱት ሬድዋን የአፍሪካ ኅብረት በመንግሥታቸው ተመራጭ የግንኙነት መንገድ እንደሆነ ጥቆማ ሰጥተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ልዩ ልዑካን በጋራ ባወጡት መግለጫ ሁሉም ወገኖች ከጥላቻ ንግግር እና ቀስቃሽ መግለጫዎች እንዲታቀቡ ጭምር ጥሪ አቅርበዋል። አኔተ ቬበር እንደሚሉት "የጥላቻ ንግግርን እና አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚሰነዝሩትን ፕሮፖጋንዳ ማርገብ" በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ለሚደረገው ድርድርም ሆነ ዘላቂ ሰላም ለማውረድ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። "የግጭቱ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔው አካል እንደሆነ ወገን የጥላቻ ንግግርን ማርገብ፣ እርስ በርስ መከባበር እጅግ ጠቃሚ ነው" የሚሉት ልዩ መልዕክተኛዋ በተለያዩ ብሔሮች መካከል ውጥረት "ቀስቃሽ ንግግሮችን ማርገብ ወደ ድርድር ለማምራት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሰላም ለማምጣትም አስፈላጊ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።   

የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ሊደረግ ይገባል የሚል አቋም አለው። ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የትግራይ ክልል በአንጻሩ በመጪው ሣምንት በሚካሔደው የኬንያ ምርጫ ሥልጣናቸውን የሚያስረክቡትን ፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታን በአደራዳሪነት መርጧል። የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ልዩ ልዑካን በጥምረት ባወጡት መግለጫ "በአፍሪካዊ የሚመራ ድርድር ለመደገፍ ዝግጁ" መሆናቸውን ገልጸዋል።

አኔተ ቬበር በኢትዮጵያ ጥቅምት 24 ቀን 2013 የተቀሰቀሰውን እና ሶስት ክልሎችን ያዳረሰው ውጊያ ዳግም እንዳያገረሽ "ሁለቱ ወገኖች በቅን ልቦና በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የመደራደል ዕድል እንዲያገኙ ሁላችንም ማረጋገጥ አለብን" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

"ኢትዮጵያ ወደ ተሐድሶ መርሐ ግብሯ ለመመለስ ሰላም ትፈልጋለች። የትግራይ ሕዝብ ወደ መደበኛ ሕይወቱ ለመመለስ ሰላም ይፈልጋል" የሚሉት ቬበር ሁለቱ ወገኖች "ዳግም ወደ ጦርነት ከተመለሱ ይኸ ሁሉ አደጋ ላይ ይወድቃል። ከጦርነት የሚያተርፍ የለም" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።  አኔተ ቬበር በአፍሪቃ ቀንድ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑክ ሆነው የተሾሙት በሰኔ 2013 ሲሆን ከዚያ በኋላ ኃላፊነታቸው ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ተራዝሟል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ