1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

በትግራይ ክልል የነዳጅ አቅርቦት ከፍላጎት አንጻር ሲቃኝ

ሰኞ፣ ጥር 8 2015

ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በኃላ ወደ ትግራይ መደበኛ የነዳጅ አቅርቦት መግባት ጀምሯል። በዚህም ተዘግተው የነበሩ ነዳጅ ማደያዎች ስራ የጀመሩ ሲሆን በክልሉ ተስተጓጉሎ የቆየ የትራንስፖርት፣ የአምቡላንስና የፅዳት አገልግሎቶች መሻሻል እየታየባቸው ስለመሆኑም ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/4MFrz
Äthiopien | Treibstoffversorgung in Mekele
ምስል Million Haileselassie/DW

በትግራይ ክልል የነዳጅ አቅርቦት እና ፍላጎት ገና አልተጣጣመም

ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በኃላ ወደ ትግራይ መደበኛ የነዳጅ አቅርቦት መግባት ጀምሯል። በዚህም ተዘግተው የነበሩ ነዳጅ ማደያዎች ስራ የጀመሩ ሲሆን በክልሉ ተስተጓጉሎ የቆየ የትራንስፖርት፣ የአምቡላንስና የፅዳት አገልግሎቶች መሻሻል እየታየባቸው ስለመሆኑም ተነግሯል።  ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ ተላልቅ፣ መካከልና ዝቅተኛ አምራች ኢንዳስትሪዎች መሰረታዊ አገልግሎቶች መቀጠላቸው ተከትሎ ወደ ስራ እየተመለሱ ሲሆን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ለማሻሻል እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ስራ ያቆሙ ፋብሪካዎች ለመመልከት የኢንዳስትሪ ሚኒስቴር ልኡክ ዛሬ በመቐለ ጉብኝት አድርጓል።

ወደ ትግራይ መደበኛ የነዳጅ አቅርቦት የቆመው በ2013 ዓመተምህረት ሰኔ ወር ነበረ። በየወሩ እስከ 12 ሚልዮን ሊትር ነዳጅ የሚፈልገው ትግራይ ክልል ላለፊት አንድ ዓመት ከስምንት ወራት መደበኛ የነዳጅ አቅርቦት ባለመገኘቱ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ቋሟል፣ የአምቡላንስ እና ፅዳት አገልግሎት ተስተጓጉሏል፣ ሌሎች በርካታ ስራዎች ተደናቅፈው ቆይተዋል። ወደ ክልሉ በኮንትሮባንድ ንግድ ይገባ ነበር የሚባለው ነዳጅ በሊትር እስከ 600 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የሰላም ስምምነቱ ተከትሎ በትግራይ የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች አቅርቦት እንዲያገኙ ተደርጎ ቤንዚን እና ናፍጣ ወደ ክልሉ መግባት ጀምሯል።በትግራይ የነዳጅ እጦት ያሳደረው ተጽእኖ

በትግራይ ንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ካሳሁን ክንደያ ለዶቼቬለ እንደገለፁት፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መደበኛ የነዳጅ አቅርቦት ወደ ትግራይ መግባት የጀመረ ሲሆን፣ መጠኑን በየቀኑ እያደገ ስለመሆኑ ገልፀዋል። የኤጀንሲው ባለስልጣን አቶ ካሳሁን "የነዳጅ አቅርቦት ቀስበቀስ እየገባ ነው። እስከ አሁን 19 ነድጅ የጫኑ መኪኖች ወደ መቐለ ገብተዋል። ወደ ሌሎች ከተሞችም እንዲቀርብ ከነዳጅ ማደር ባለቤቶች ጋር እየተነጋገርን ነው። በፌደራል መንግስቱ በኩል ቅድሚያ እንሰጣቹሃለን ተብለን ጥሩ መተባበር ነው እየተደረገ ያለው። ከመቐለ በተጨማሪ ወደ ሞኾኒ፣ አጉላዕ ነዳጅ የጫኑ መኪኖች ገብተዋል። ወደ ውቅሮም መንገድ ላይ ነው። ሁሉም ማደያዎች ስራ እንዳይጀምሩ ግን በመሰረተ ልማቱ ላይ የደረሰ ጉዳት አለ" ብለዋል።

ከነዳጅ አቅርቦቱ ጋር በተያያዘ የሸቀጦች ዋጋ ይቀንሳል፣ የጤና አገልግሎት ይሻሻላል፣ የንግድና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ስራው ያንሰራራል ተብሎ እንደሚጠበቅ በባለስልጣኑ ተገልጿል። አሁን ላይ ባለው ሁኔታ በወር ከሚፈለገው 12 ሚልዮን ሌትር የገባው ነዳጅ 800 ሺህ ሊትር ብቻ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህም ለጤና ዘርፉ፣ ለመንግስት ስራ እና ሌሎች ቅድሚ የሚገባቸው ተግባራት እንዲዳረስ እየተደረገ ስለመሆኑ ተነግሯል። በአጭር ግዜ ለሁሉም ነድጅ ፈላጊዎች ነዳጅ እንዲያገኙ ለማድረግ አቅርቦቱ ለማሻሻል ከአስመጪዎች ጋር እየተሰራ መሆኑ ተገልጿልትግራይ ክልል 7 ወራት ያለ ነዳጅ

በመቐለ በሚገኝ የቶታል ማደያ ድርጅት የሚሰራው ወጣት አብርሃ ብርሃነ የነዳጅ አቅርቦት በመቆሙ ለረዥም ግዜ ስራ ውጭ ሆኖ መቆየቱ የሚገልፅ ሲሆን በዚህ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር መጋለጡ ያስረዳል። አብርሃ "ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ግዜ ከስራ ውጭ ሆነን ነው የቆየነው። ስራ ባቆምንበት ግዜ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ነው የገጠመኝ። ኑሯችን ተጎሳቁሎ ነው የቆየው። አሁን ይህ ሁሉ አልፎ ወደ ስራ መመለሳችን ደስታ ፈጥሮብኛል" ብሎናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ የሚገኙ አምራች ድርጅቶች በሂደት ወደ ስራ እየተመለሱ ይገኛሉ። በጦርነቱ እንዲሁም በአቅርቦት እጦት ምክንያት ከስራ ውጭ ሆነው የቆዩ ተቋማት ለመመልከት እና ለመደገፍ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ልኡክ ዛሬ በመቐለ ጉብኝት አድርጓል። በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ 12 ሺህ ፍቃድ ያላቸው አምራች ድርጅቶች ከስራ ውጭ ሆነው መቆየታቸው እና በዚህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ስራ አጥ ሆነው መቆየታቸው የክልሉ አስተዳደር ይገልፃል። የሰላም ስምምነቱ ተከትሎ መሰረታዊ አገልግሎቶች እየተመለሱ በመሆኑ አምራች ተቋማቱ ወደ ስራ ሊመለሱ በብዙሃን ይጠበቃል።

Äthiopien | Treibstoffversorgung in Mekele
መቀሌ የሚገኝ ነዳጅ ማደያ በስራ ላይ ምስል Million Haileselassie/DW

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ታምራት ዲንሳ 

ኂሩት መለሰ