በትግራይ የነዳጅ እጥረት
ረቡዕ፣ ሰኔ 29 2014በትግራይ በነዳጅ አቅርቦት እጦት ምክንያት የህዝብ አገልግሎቶች እና እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ ተገለፀ። የክልሉ መንግስት እንደሚለው በነዳጅ አቅርቦት እጦት ምክንያት በዓለምአቀፍ ተቋማት ወደ ትግራይ የገባ የምግብና መድሃኒት እርዳታ፥ ከመቐለ መጋዝኖች ወደ ተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች አጓጉዞ ለተቸገረዉ ህዝብ ማዳረስ አልተቻለም። የነዳጅ እጦቱ የሕክምና ተቋማትን ስራም ማደናቀፉ ተገልጿል። በነዳጅ እጦት ምክንያት በትግራይ የህዝብ ትራንስፖርት ዋጋ ከ400 እስከ 500 በመቶ መጨመሩን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ከመቀሌ ዘግቧል።
የትግራይ የአደጋዎች ቅድመ ጥንቃቄ እና ምላሽ ዳይሬክቶሬት እንደሚገልፀው በነዳጅ አቅርቦት እጦት ምክንያት በዓለምአቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ወደ ትግራይ የገባ የምግብና መድኃኒት ድጋፎች ከመቐለ መጋዝኖች ወደ ተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች አጓጉዞ አደጋ ላይ ለወደቀ ህዝብ ማዳረስ አልተቻለም። የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ ለዶቼቬለ እንዳሉት "ከእያንዳንዱ የዕርዳታ ኮንቫይ ጋር ለስርጭት የሚረዳ በቂ ነዳጅ ሊገባ ነበር የሚጠበቀው። ሆን ተብሎ ነዳጅ እንዳይገባ ክልከላ ተደርጎ ስላለ እርዳታ ወደ ህዝብ ማዳረስ አልተቻለም።
የነዳጅ አቅርቦት እጦቱ በትግራይ የሚገኙ የሕክምና ተቋማት ስራንም ያደናቀፈ ሆንዋል። ከጤና ጣብያ እስከ ሪፈራል ሆስፒታል ደረጃ ያሉ የሕክምና ተቋማት ነዳጅ ባለማግኘታቸው የአምቡላንስ አገልግሎት አቋርጠዋል፣ አማራጭ ሀይል የሚያገኙበት ስርዓት ተስተጓጉሏል። በትግራይ ትልቁ የሕክምና ተቋማ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በነዳጅ እጦት የአምቡላንስ አገልግሎት ካቋረጠ ወራት አልፈዋል።
በነዳጅ እጦት ምክንያት በትግራይ የትራንስፖርት ዋጋ ከነበረው ከ400 እስከ 500 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች የገባ የተባለ ቤንዚን እና ናፍታ በሊትር እስከ 400 ብር በጎዳናዎች ይሸጣል። ለትራንስፖርት ችግሩ እንደመፍትሄ የሚመስል ለዓመታት ጠፍተው የነበሩ በእንስሳት ጉልበት የሚሰሩ ጋሪዎች አሁን አሁን በመቐለ ጎዳናዎች የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ መመልከት የተለመደ ሆንዋል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ