ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ምን ይላሉ?
ዓርብ፣ ግንቦት 28 2018
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደገለፀው ሰኞ ግንቦት 24 ቀን በትግራይ ክልል 38 ምርጫ ክልሎች እና በአማራ ክልል በ 8 ምርጫ ክልሎች ምርጫ አልተካሄደም። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ እንደተናገሩት “በጸጥታ ምክንያት ወደ 143 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች” የምርጫው ዕለት አልተከፈቱም ፤ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ የምርጫ ክልሎችም የድምጽ አሰጣጥ ከተጀመረ በኋላ በጸጥታ ችግር ተቋርጧል።
በዚህ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለማሳተፍ ፈታኝ ነበር። አንዳንዶች ጮርሶ አለመናገርን ሲመርጡ ፤ ሌሎች ፍቃደኛ ሆነው እንኳን በኔትወርክ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። ፍቃደኛ የሆኑት ደግሞ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል። ስማቸውን እንዳንገልፅ እና ድምፃቸውን እንድንቀይር፤ ከእነዚህ አንዷ
ምርጫ ሙሉ በሙሉ ያልተካሄደበት የትግራይ ክልል ነዋሪ ወጣት ናት፤ ስሟን ለዚህ ዝግጅት ትዕግስት ብለነዋል።
ዘንድሮ ጨርሶ በክልሉ ምርጫ አልተካሄደም። ከስድስት ዓመት በፊትም በክልሉ ፣ ያለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ የተካሄደው ምርጫም እውቅና አልተሰጠውም። ትዕግስት የትግራይ ህዝብ ድምጽ አለመካተቱን አጥብቃ ትኮንናለች ። «ይሔ ደግሞ አንደኛ ተገቢነት ያለው ነገር አይደለም ፤ ሁለተኛ ሊሆን የማይገባው አይነት ሲስተሞችን፤ ወይም ደግሞ አምባገነናዊ የምንላቸውን ሲስተም እንደማለማመድ ነው የሚታየኝ። በዚህ ደረጃ በይፋ ምርጫ መካሄድ እያለበት ፤ ምርጫ አለማካሄድ መቻል ምን ያህል ፤ የሆነ ሰው ኃይል ኖሮት ከማህበረሰቡ ፍላጎት ውጪ ነገሮችን ማስቀጠል እንደሚችል ነው የሚያሳየው እና፤ አንዲሞክራቲክ የሆነ ነገርን እንደማለማመድ እንደሆነ ይታየኛል፤» ትላለች።
ጥያቄ ፦ አሁን ትግራይ ውስጥ ባለው ሁኔታ ትግራይ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ይቻል ነበር?
«ይቻል ነበር ብዬ አምናለሁ።» ትላለች ትዕግስት ቀጥላ ስታብራራም «ምክንያቱም ከምርጫው በፊት መሰራት የነበረባቸው የቤት ስራዎች ተሰርተው ቢሆን ኖሮ፤ ለምሳሌ ክልሉ ላይ ያሉ ሁሉም ፓርቲዎች መወዳደር እንዲችሉ እድሉ ክፍት ቢሆን ኖሮ፤ ያው ለምንድን ነው እንዲወዳደሩ ያልተፈቀደው ሌላ ጉዳይ ቢሆንም ግን የተወሰነ ደጋፊ ካላቸው፤ የመወዳደር መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ በግሌ ስለማምን እድሉ በዛ ደረጃ ክፍት ቢደረግ ኖሮ፣ ትግራይ ውስጥ ሁሉም ቦታዎች ላይ አይደለም ግን አብዛኛው ቦታዎች ላይ ለምሳሌ መቀሌ ፣ ሽሬ፣ አክሱም፤ አድዋ እንደዚህ አይነት ቦታዎች ላይ ምርጫ ማካሄድ ይቻል ነበር። ትንሽ አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ምዕራብ ትግራይ ላይ ነው። ቋሚ ነዋሪው እስካልተመለሰ ድረስ እዛ አካባቢ ላይ የሚደረጉ ምርጫዎችን እንደ ህጋዊ መውሰድ ከባድ ነው የሚሆነው። ስለዚህ እንደዛ አይነት ቦታዎች ላይ ይገባኛል ፤ ምርጫ ማካሄድ ከባድ ነው። ከዛ ውጪ ያሉ ቦታዎች ላይ ግን ምርጫ መካሄድ ይችል ነበር። መካሄድም ነበረበት።»
ከትግራይ ክልል ውጪ ዘንድሮ በአማራ ክልል ሥምንት ምርጫ ክልሎች ላይም ምርጫ ሳይካሄድ ቀርቷል። ከእነዚህም ቦታዎች መካከል ምዕራብ ጎዳም ዞን የሚገኘው ደጋ ዳሞት ወረዳ እና ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው አምባሰል ወረዳ ተጠቃሽ ናቸው።
ሌላው ያነጋገርነው ወጣት ለደህንነቱ ሲል ስሙን እንዳንጠቅስ ፤ ድምፁን እንዳንቀይር ብቻ ሳይሆን የጠየቀን፤ በአማራ ክልል የሚገኝበትን ቦታም እንዳንጠቅስ ነው። ስጋቴ በሁለቱም ወገን ነው ይላል። የፋኖ ተዋጊዎችን እና የመንግሥትን ወገን! በነበረበት ቦታ የምርጫ ዕለት የነበረውን እንዲህ ሲል ገልፆልናል።
«እኔ ከምኖርበት አካባቢ አልተካሄደም። ከጠዋት አንስቶ እስከ አራት ሰዓት አካባቢ የመሣሪያ ልውውጥ ነበር። በዚያን ሰዓት ሰው (ለምርጫ) ወጥቷል አልወጣም አላውቅም። እዛ አካባቢም አይደለም የምርጫ ጣቢያ ያለው። ከዛ በኋላ ወደ 9 ሰዓት አካባቢ ነው እኔ የወጣሁት፤ የዛን ሰዓት እንግዲህ ትንሽዬ ሰዎች በመስመሩ ወጥተናል፤ ወክ አድርገናል። ከዛ ውጪ ከተማ ስላለው ነገር አላውቅም።»
ይላል ከዚህ በፊትም ድምፅ ሰጥቶ የማያውቀው ይህ ወጣቱ፤ ባለመምረጡም የሚጎድልበት ነገር እንደማይኖር ይናገራል። የእሱ ምኞት ሰላም ነው! በአማራ ክልል ያለው ግጭት ምን ያህል የማህበረሰቡን የዕለት ተዕለት ህይወት እየፈተነ እንደሆነ ይናገራል።«ግጭት እኮ ካለ ሰው የመስራት ተስፋው ይሟጠጣል ፤ የመኖር ተስፋው ይሟጠጣል። ሰላም ከሌለ ፣ ግጭት ካለ አንድ ጥይት እኮ ጮኸ ማለት ብዙ ነገር ነው እንትን የሚለው። ስለዚህ ሰላም ከሌለ ለየትኛውም ወገን ጠቃሚ አይደለም። ያለውም ያለውን እያጣ ነው፤ የሌለውም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ አይደል ኑሮዋችን፤ በኑሮዋችን ሌላ ቀውስ ውስጥ እየገባን ነው። ሰላም ከሌለ ምን ተስፋ አለ? »
ፀጥታ ችግር ምክንያታት ምርጫ የተቋረጠባቸው የኦሮሚያ ክልል ቦታዎች
ሌላው ያነጋገርነው ወጣት በፀጥታ ችግር ምክንያታት ምርጫው የተቋረጠበት አካባቢዎች እንዳሉ ከተገለፀበት ሌላኛው ክልል ፣ ኦሮሚያ ነው። እሱም ስሙን እንዳንገልፅ እና ድምፁ እንዲቀየር ጠይቆናል። «ምርጫ ወደ ከተሞች አካባቢ ነው እንጂ እኔ በማቃቸው የገጠር አካባቢዎች የተካሄደ አይመስልም። በፀጥታ ችግር ምክንያት ፤ እና የሰው ስጋት (ፍላጎት) ምርጫ ሳይሆን ሰላም የሚመጣበትን ሁኔታ ነው እንጂ፤ ለምርጫው ያን ያህል የተጨነቀ አይመስልም። መንግሥትም ያን አካባቢ ያን ያክል ብዙ አልተጨነቀበትም፤ ምርጫ ጣቢያዎች የሉም። ሰውም ምርጫ ሳይሆን በዚህ ፀጥታ እና የህይወት ጉዳይ ላይ ነው ትኩረት የሰጠው።»
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቀርሳ ማሊማ ወረዳ እና ሰደን ሶዶ ወረዳ ያለውን በምሳሌነት ያነሳው ይኼው ወጣት ፣ እሱም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ መምረጥ አለመቻሉ ቁጭት እንደማይፈጥርበት ነው አክሎ የገለፀው፤«በአሁኑ ጊዜ ምርጫ አልመረጥኩም ወይም ዲሞክራሲያዊ አልሆነም ፤ እገሌ አልተመረጠም፤ እገሌ ተመርጣል ሳይሆን ፤ ሰላም እንዴት ይስፈን? ወጥተን መግባት እንዴት እንችላለን ነው። ወጣቱም በአብዛኛው እዛ አካባቢ የለም። ወጣቱ ወደ ከተማ ወጥቷል ወይም አንዱ ጋ፤ መንግሥት ጋር ወይም ታጣቂዎች ጋር ነው ያለው። በሰላማዊ መንገድ እየሰራ የሚኖር ወጣት በቁጥር በጣም አነስተኛ ነው። ተደብቆ ወቶ፤ ተደብቆ ገብቶ ነው የሚነግደው ወይም የሚያርሰው። ስለዚህ የወጣቱ ትኩረት አሁን ምርጫ ሳይሆን በህይወት የመኖር፤ ሰላም የማግኘት ፤ ሰርቶ የመኖር ጥያቄ ነው። ምርጫ በአሁኑ ጊዜ ያን ያህል የሚያስቆጨው አይደለም፤ እውነቱን ለመናገር»
ከመንግሥት ጦር ጋር የሚዋጉት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ በየፊናቸው ምርጫውን በመቃወም ፤ እንዲሁም እንቅስቃሴዎችን በመገደብ ጥብቅ ማስጠንቀቂያዎችን ከምርጫው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ማውጣታቸው ይታወሳል።
ምርጫ ያልተካሔደባቸው የምርጫ ክልሎች ድምፅ የመስጠት ዕድል ያገኙ ይሆን?
በኢትዮጵያ የአውሮጳ ኅብረት ልዑክ እና በአዲስ አበባ የሚገኙ የኅብረቱ አባል ሃገራት ኤምባሲዎች ዕሮብ ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ምርጫ ያልተካሔደባቸው የምርጫ ክልሎች ድምፅ የመስጠት «ዕድል ይሰጣቸዋል» የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል። በርግጥ በእነዚህ አካባቢዎች ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። እስከዛው ከምርጫ ውጪ የተደረጉ ወጣቶች የፖለቲካ አመለካከታቸው እንዴት ማንጸባረቅ ይችላሉ? ማህበራዊ ሚዲያ ለወጣቱ አንዱ አማራጭ ነው ትላለች ትዕግስት፤
«ማህበራዊ ሚዲያ ለወጣቱ አንዱ አማራጭ ነው»
«ከምርጫ ውጭ ፖለቲካል አይዶሎጂውን ማራመድ የሚቻልበት፤ ያው ሶሻል ሚዲያ መድረኮች ናቸው መሆን የሚችሉት። በተለይ ወጣቱ እዛ ነገሮች ላይ አክቲቭ ስለሆነ፤ ግን ያን ያህል ተፅዕኖ ያመጣሉ ወይ? በርግጥ ክልሉ ላይ አሉ ፤ የተለያዩ ሚዲያዎች ላይ አክቲቭ የሆኑ፤ የራሳቸውን አመለካከት የሚያራምዱ ብዙ ወጣቶች አሉ፤ ከባለፈው ጦርነት በኋላም ብዙም የፖለቲካ አይዶሎጂ ለውጦች አሉ።ወጣቱ ላይ። ለሁለት አመታት የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ ማህበረሰቡ፤ በተለይ ወጣቱ ከዛ በፊት ከነበረው የፖለቲካ አይዶሎጂ አንፃር ሲታይ በጣም ትልቅ ለውጥ አለ። ለውጥን የመፈለግ፤ የራሱ የሆነ የፖለቲካ አይዶሎጂ የማራመድ ነገሮች አሉ»
የዘንድሮውን ምርጫ ያን ያህል በቅርበት ባልከታተለውም ዋና ዋና የሚባሉትን ነገሮች ከመገናኛ ብዙኃን አያመልጡኝም የምትለው ትዕግስት ፤ እስካሁን የነበረውን ሂደት እንዴት ትገመግመው ይሆን?
« በመላው ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ያን ያክል ገዢውን መንግስት ሊቀራረብ የሚችል ውጤት ማምጣት የሚችል፤ ሁሉም ቦታ ላይ ተወዳዳሪ ማድረግ የቻለ ፓርቲ አለ ብዬ ማለት አልችልም፤ እስካሁን ባለኝ መረጃ። ተዓማኒነቱን በተመለከተ ምርጫውን እያካሄደ ያለው ምርጫ ቦርድ ከሚሰጠን መረጃ እና ታዛቢ ነን ብለው ከተቀመጡ ሰዎች አንፃር ነው መናገር የምንችለው፤ ግን በመላው ኢትዮጵያ ከዚህም በፊት ይካሄዱ ከነበሩ ምርጫዎች አንፃር፤ ከነበረን ታሪክ አንፃር ፤ ያን ያክል ታማኝ በሚል ደረጃ በግሌ አልጠብቅም፤ ብዙም እምነቱም የለኝም።»
ከምርጫው ከተገለሉት ወጣቶች አንዷ የሆነችው ትዕግስት፣ ወደፊት የሚካሄዱ ምርጫዎች ሁሉን አሳታፊ እንዲሆኑ እና ሁሉም ዜጋ ድምፁን መስጠት እንዲችል ትመኛለች። ለአሸናፊ ፖለቲከኞችም ተከታዩን መልዕክት ታስተላልፋለች። «አንደኛ ጠንካራ የሆነ ተቋም ሊኖረን ይገባል፣ ምርጫ ቦርድ በደንብ ጠንካራ ፤ገለልተኛ እና የሚወስናቸውም ውሳኔዎች ገዢውንም መንግሥት ጨምሮ አስገዳጅ መሆን የሚችሉበት አይነት ጥንካሬ እና ቁመና ቢኖረው ኖሮ፤ ብዙ ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ እና በደንብ የተቋቋመ ምርጫ ቦርድ ፤ ፍርድ ቤት እና መሰል ገለልተኛ ጠንካራ ተቋም ሊኖረን ይገባል» ትላለች ትዕግስት።
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026