1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

1447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በድሬደዋ እና ሀረር ከተሞች ተከብሮ ዋለ።

መሳይ ተክሉ
ዓርብ፣ መጋቢት 11 2018

447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በድሬደው እና ሀረር ከተሞች ተከብሮ ዋለ። በድሬደዋ ከንጋት ጀምሮ እስከ ረፋድ ድረስ በዘነበው ዝናብ ሳቢያ የከተማዋ የእስልምና እምነት ተከታዮች የኢድ ሰላትን በየመስኪዶች እንዲያከናውኑ አስገድዷቸዋል።

https://p.dw.com/p/5AnRo
1447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በድሬደው እና ሀረር ከተሞች ተከብሮ ዋለ። 
1447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በድሬደው እና ሀረር ከተሞች ተከብሮ ዋለምስል፦ Mesay Teklu/DW

የዒድ አልፈጥር በዓል በድሬዳዋ እና አካባቢው ተከብሮ ውሏል

1447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በድሬደው እና ሀረር ከተሞች ተከብሮ ዋለ። 

በድሬደዋ ከንጋት ጀምሮ እስከ ረፋድ ድረስ በዘነበው ዝናብ ሳቢያ የከተማዋ የእስልምና እምነት ተከታዮች የኢድ ሰላትን በየመስኪዶች እንዲያከናውኑ አስገድዷቸዋል።

በረመዳን የፃም ወቅት የታየውን መረዳዳት እና መደጋገፍ በኢድ በዓልም መጠናከር እንደሚገባው ተገልጿል ።

1447 ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት በድሬደዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች አንዱ የሆኑት ሼህ ኢብራሂም ኢማም "ረመዳን ከእስልምና መሰረቶች አንዱ ስለመሆኑን" ተናግረዋል።

የኢድ በዓል የፃሙ ወቅት በሰላም በመጠናቀቁ የእምነቱ ተከታይ በጋራ ተሰባስቦ የሚሰግድበት ምስጋና የሚያቀርብበት መሆኑን የገለፁት ሼህ ኢብራሂም ሰላምን ጨምሮ የተለያዩ መልዕክቶች የሚቀርቡበት መሆኑን አስረድተዋል ።ስለሰላም ሁሉም ፀሎቱን እንዲቀጥል ጥሪ በማቅረብ።

በምስራቅ ኢትዮጵያዋ የድሬደዋ ከተማ ከንጋት ጀምሮ እስከ ረፋድ ድረስ በዘነበው ዝናብ ሳቢያ የከተማዋ የእስልምና እምነት ተከታዮች የኢድ ሰላትን በየመስኪዶች ማከናወናቸውንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የፃሙን ወቅት እርስ በእርስ በመደጋገፍ በጥሩ ሁኔታ ማሳለፋቸውን የምትገልፀው የሀረር ከተማ ነዋሪዋ ሙንታ አህመዲንየኢድ በዓልን ከጎረቤት እና ከጓደኞቿ ጋር እንደምታሳልፍ ገልፃለች። 

በአሉን በጋራ በኢድ አደባባይ ላይ በአንድነት ማክበራቸውን የገለፀው ወጣት ሁሴን በበኩሉ በኢድ  መረዳዳት እና መደጋገፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል።

የረመዳን ወር 

የእስልምና እምነት ተከታዮች በናፍቆት ከሚጠብቋቸው ጊዜያት አንዱ የረመዳን የፃም ወቅት ነው። 

በአመት አንድ ጊዜ የሚመጣው የረመዳን ወርፃም "ከእስልምና መሰረቶች አንዱ"ስለመሆኑ የሚናገሩት ከድሬደው እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አመራሮች አንዱ የሆኑት ሼህ ኢብራሂም ኢማም ይህን የፃም ወር "በጣም ትልቅ ቦታ ያለው ነው" በማለት ገልፀውታል።

በፃሙ ወር "ብዙ ትርፍ ብዙ ሀጅር አለ " የሚሉት ሼህ ኢማም ሙስሊሙ ማህበረሰብ የረመዳንን ወቅት በናፍቆት የሚጠብቅበት ብዙ ምክንያቶች አሉት ብለዋል።

አንድ ወር ያህል በቆየው የዘንድሮ የረመዳን የፃም ወር መረዳዳት እናመደጋገፍ ይበልጥ ጎልቶ የታየበት ስለ ሰላም በስፋት ፀሎት የተደረገበት መሆኑ ተገልፃል።

በድሬደዋ የረመዳን ወር በክርስትና እምነት ተከታዮች የተዘጋጀውን የአደባባይ የአፍጥር ዝግጅት ጨምሮ የማህበረሰቡን እርስ በእርስ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጎሉ ኩነቶች የተካሄዱበት ነበር። 

በተመሳሳይ በሀረር ከተማ የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች የረመዳን የፃም ወርን በበጎ ስራዎች ማሳላፋቸውን ገልጸዋል ።

ድሬደዋን ጨምሮ በምስራቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዘንድሮ የረመዳን የፃም ወር ያበቃበት የኢድ አልፈጥር በዓል በኢድ ሰላት መከበሩን የተለያዩ አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል። 

በዓሉ በአንዳንድ አካባቢዎች ለቀናት በተለያየ መልኩ እንደሚከበር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
መሳይ ተክሉ
ታምራት ዲንሳ
ጸሐይ ጫኔ