የዒድ አከባበር በሰበታ ከተማ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2014መሃመድ ኑር ሀሰን በኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ አቶ መሃመድን አግኝቼ ያነጋገርኳቸው ዛሬ በመላው ዓለም በድምቀት ተከብሮ የዋለውን የ1443ኛው ዓመተ ሂጂራ በሰበታ ከተማ ፉሪ አካባቢ ሲያከብሩ ነው፡፡ በወርሃ ረመዳን አቅማቸው የፈቀደላቸው የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በሙሉ ስርዓተ ጾሙን ያከናውናሉ፡፡ አቅማቸው ያልፈቀደላቸው አረጋውያን እና ህሙማንም ቢሆን ባይጾሙ እንኳ ሃይማኖቱ በሚደነግገው መልኩ መክፈል ያለባቸውን ከፍለው በዚህች የኢድ አልፈጥር ቀን ተካፋይ ይሆናሉ፡፡ የፉሪ 25 መስጊዶች እና የኢድ ሰብሳቢ ሲራጅ ፈድሉ ያሲን እለቱን አስመልክተው አስተያየታቸው ያጋሩን የሃማኖቱ መሪ ናቸው፡፡ እንደ የሃይሞኖት መሪው ማብራሪያ ይህቺ የረመዳን ወር ፍጻሜ የኢድ ቀን ልዩ ትርጉምና ስፍራ እንዳላትም አብራርተውልናል፡፡ የእምነት አባቶቹ እና የሃይማኖቱ ተከታዮች በአስተያየታቸው አክለውም በቅርቡ በኢትዮጵያ እያገረሸ የመጣው የሃሞኖት ግጭት አገርንም ሆነ ሃማኖቶቹን ሚጎዳ በመሆኑ በስክነት ሊያዝ የሚገባው ነው ብለዋል፡፡ ዛሬ ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ በርካታ ሕዝበ ሙስሊም ወደ አደባባይ በወጡበት በዚህ ሰበታ ከተማ የተከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ ነው የተጠናቀቀው፡፡ ሁሉም ሙስሊም ቅዱሱን የረመዳን ወር በፆም አሳልፈው በህብረት ሶላት በማድረስ የሚያከብሩት በዓሉ በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም ተከብሮ ውሏል።
ስዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ