1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ጨው እና ወርቅ ላይ ተኝተን በርሃብ እየሞትን ነው»

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ጥቅምት 2 2016

አሁን ያለው የአፋር መንግሥትን የሚቃወሙ ወጣቶች ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው እንደሆነ ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል። በወጣቶች ዓለም ዝግጅት ያነጋገርናቸው ወጣቶች እንደሚሉት ከሆነ፤ ከሰሜኑ ጦርነት በደንብ ባላገገመው አፋር ክልል ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር እጦት አለ፣ ወጣቶች ላይም እስራት እና አፈና ይካሄዳል። የክልሉ መንግሥት ይህን ያጣጥላል።

https://p.dw.com/p/4XUOy
ተቃውሞ የወጡ ወጣቶች
በአፋር በርሀሌ ወረዳ ተቃውሟቸውን ለማሰማት ጎዳና የወጡ ወጣቶችምስል Privat

በአፋር ክልል ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች

የአፋር ክልል አስተዳደርን የሚቃወሙ ወጣቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ ነው። የሚያነሷቸው ጥያቄዎች የእኩልነት ፣ፍትሀዊነት እና የመልካም አስተዳደር እጦት ናቸው።   
አሚን በአፋር ክልል ጭፍራ አካባቢ የሚኖር ወጣት ነው። ችግሩ እሱ በሚኖርበት ከተማ ብቻ ሳይሆን «በአጠቃላይ አፋር ክልል የሚስተዋል ነው» ይላል። « መጀመሪያ ላይ የጎርፍ አደጋ ነበር። ቀጥሎ ኮሮና መጣ ከዛ ጦርነት ነበር። እያለ የአፋር ክልልን ፈተና ይዘረዝራል። « ሁሉንም አብረን ማለፍ እንችል ነበር። ነገር ግን የመልካም አስተዳደር ችግር ያ ሁሉ እንዲባባስ አድርጓል። ወጣቶች እየታሰሩ ነው። ሚዲያ ላይ የመናገር ነፃነት ተነፍጓል። ፌስ ቡክ ላይ ላይክ ያደረገ ሳይቀር ይታሰራል» ይላል። የተወሰኑ ወጣቶችም ወደ አዲስ አበባ እና ጅቡቲ እንደተሰደዱ አሚን ይናገራል።  በተለይ የንግድ እና የመንግሥት ስራ « በመንግሥት ባለስልጣናት እጅ ነው ያለው» ሲል ይወቅሳል። ድምፃቸውን የሚያሰሙ ወጣቶች ከስራ እንደሚፈናቀሉ ይናገራል።

የአፋር ክልል ወታደሮች
በሰሜኑ ጦርነት የአፋር ክልል ወታደሮችምስል Seyoum Getu/DW

ለትግራይ ክልል ቀረብ በምትለው የአፋሯ በርሀሌ ወረዳ ባለፈዉ ማክሰኞ ዕለት ሰልፍ ተካሂዶ ነበር። በዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከተካፈሉት መካከል አንዱ አካድር ይባላል። እሱም እንደሌሎች ወጣቶች የአፋር ክፍል አስተዳደራዊ ስርዓትን ይቃወማል። ሰልፉ የተካሄደ ዕለት በስልክ አግኝተንዋል። « ከ500 በላይ ይሆናሉ በሰልፉ ላይ የተሳተፉት ሰዎች፤ እዛ ላይ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ፣ በርሃብ የተጎዱ ሰዎች እንዲረዱ ጠይቀናል» የሚለው አካድር «ጨው እና ወርቅ ላይ ተኝተን በርሃብ

እየሞትን ነው» ይላል። 
ፋሲ በበርሀሌ ወረዳ፣ ዞን 2 በተካሄደው ሰልፍ ላይ ባትገኝም በክልላችን እየደረሰ ነው የምትለውን ችግር ለዶይቸ ቬለ በስጋት ገልፃለች። ከዚህ ቀደም ጨው በማረት ሥራ ተሰማርታ ነበር የምትኖረው። « አራት ወር ሙሉ ክፍያ አልተሰጠኝም» ይሔ ብቸኛ ችግሯ አይደለም። የ 6 ልጆች እናት እና የ 22 ዓመት ወጣት እንደሆነች የገለፀችልን ፋሲ  ባለቤቷ በእስር ላይ ይገኛል። « እሱ አሁን ከታሰረ ሁለት ወሩ ነው። በፌስ ቡክ ስለክፍያው ስለተናገረ ነው የታሰረው» የምትለው ፋሲ ሌሎች በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ለዶይቸ ቬለ ትናገራለች።
ያዩ መሀመድ ፤ የአፍዴራ ከተማ ተወላጅ ነው። እሱ በሚኖርበት አካባቢ ጨው ይመረታል።  እሱም ከአምራቾች አንዱ ሲሆን ደሞዙን ወይም ክፍያውን ለማግኘት ግን እስከ ስድስት ወራት መጠበቅ እንደነበረበት ነው የነገረን። ይህንንም ለተለያዩ ባለስልጣናት አቤት ብለናልም ይላል። « በአፋር ክልል አቤቱታ አቅርበናል። መፍትሔ አላገኘንም። በዚህም የተነሳ ባለፈው ሳምንት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ ሄደናል። መፍትሔ አልተገኘም። ችግር ላይ ነው ያለነው። » ሌላው ችግር ደግሞ አንድ ኩንታል ጨው ሸጦ በሚያገኘው ገንዘብ መግዛት የሚችለው አንድ ኪሎ ሽንኩርት ነው።  ይባስ ብሎ አሁን ስራ የለውም።  ምንም ዓይነት አቅርቦት ስለሌለ ገንዘብ ያለው እንኳን የሚፈልገዉን ገዝቶ መኖር እንደማይችል ነው የበርሀሌ ነዋሪው አካድርም የገለፀልን። እሱም ቢሆን እንደአብዛኞቹ ያነጋገርናቸው ወጣቶች በአሁኑ ሰዓት

ሴቶች ከህፃናት ጋር ቁጭ ብለው
አፋር ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮችምስል Seyoum Hailu/DW

ስራ የለውም። ኮማንደር፣ አፋር  ዞን ሶስት የሚባለው አካባቢ ነው የሚኖር የጤና ጣቢያ ባለሙያ ነው። ሀሳቡን በነፃነት በመግለጹ እንደውም  ለወራት ታስሮ እንደነበር ይናገራል። « ሚስቴ ምጥ ላይ ሆና ከሆስፒታል ተወስጄ ታስሬ ነበር። በፌስ ቡክ ለምን ተናገርከን ብለው ነው። የሌላ ፓርቲ ሆኖ ብልጽግናን እቃወማለሁ ማለት አይቻልም። » የሚለው ኮማንደር እንዲስተካከል የሚፈልገው « በክልሉ ለውጥ እንዲደረግ፤ ፕሬዚዳንት እንዲቀየርልን፤ ወጣት እና የተማረ እንዲመራን ነው የምንፈልገው። አሁን ክልሉን የሚመሩ አመራሮች እንዲቀየሩልን ነው የምንፈልገው። » ይላል።
የጭፍራ ነዋሪው አሚንም የአፋር ክልል ለውጥ ይፈልጋል። ወጣቱ ለደህንነቱ የሚያሰጉ በርካታ ምልዕክቶች ቢኖርም ከመናገር ወደኃላ ማለት አይፈልግም።  «ነፃነት በነፃ አይገንም። ከተማሩ ወጣቶች አንዱ ነኝ ቢሆንም ወደ ገጠር ሄጄ ነው ይህንን መናገር የቻልኩት። ግን እስርን እና አፈናን በመፍራት ያለውን ሁኔታ መደበቅ አይቻልም።»
የአፋር ወጣቶች አቤቱታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአፋር ክልል የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ መሐመድ ዓሊ በወጣቶቹ የተነሱትን ወቀሳዎች በሙሉ ያስተባብላሉ። « ከዚህ ቀደምም በጨው ጉዳይ ላይ ለዶይቸ ቬለ ምላሽ ሰጥተናል። ከዚህ የተለየ ምላሽ የለንም።  የበርሀሌውን ጉዳይን በተመለከተ ግልፅ መሆን ያለበት ነገር ሰልፍ ሲያደርጉ የነበሩት በክልሉ ያለውን ለውጥ በደንብ ያውቃሉ። ከለውጡ በፊት የዲሞክራሲ ጥያቄ ነበር፤ የነፃነት እና የማልማት ጥያቄ ነበር፣ የሀብት ክፍፍል ጥያቄ ነበር። ከለውጡ በኋላ ግን እነዚህ ጥያቄዎች አንድ በአንድ እንዲፈቱ በተደረጉ ሪፎርሞች ክልሉ በለውጥ ጎዳና ላይ ነው ያለው። » በማለት በክልሉ ባለፉት አራት አመት ተኩል ትልቅ ለውጥ እንዳለ አቶ መሐመድ ይናገራሉ። የሀብት ክፍፍልን በተመለከተ « በትክክል ምላሽ ያገኘበት ሁኔታ ነው ያለው። ዛሬ የአፋር ወጣት ስራ እንዲያገኝ ክልሉ እየሰራበት ነው ያለው» ይላሉ።  በርሀሌው የተቃውሞ ሰልፍ የወጡትን ሰዎች በተመለከተ « ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ፍላጎታቸው ስላልተሳካ እና የራሳቸውን ፍላጎት ማሳካት የሚፈልጉ ናቸው» በማለት ሰልፈኞቹ «ሰላም ፈላጊ አይደሉም» ሲሉ ወጣቶቹን የአፋር ክልል የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ መሐመድ ይወቅሳሉ። አቶ መሐመድ በክልሉ ድርቅ አለ በሚለው ግን ይስማማሉ።
 መፈክር እና የታሰሩ ወጣቶችን ምስሎችን ይዘው በበርሀሌው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከተገኙ ወጣቶች 10 ያህሉ መታሰራቸውን አርብ ዕለት ዶይቸ ቬለ ጥቆማ ደርሶታል። 

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ