1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፋር ጦርነት ያወደማቸው መሰረተ ልማቶች አዉታሮች

ሐሙስ፣ ግንቦት 3 2015

በአፋር ክልል የትግራይ ክልል አዋሳኝ ሰሜናዊ ዞን ጦርነት ያወደማቸው መሰረተ ልማቶች ወደ መደበኛ ቦታ አለመመለሳቸው ኅብረተሰቡን አረዋል ። በዞኑ በተለይም ከእረብቲ እና አባዓላ ወረዳዎች አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዎች፦ የችግሩ አሳሳቢነትን ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4RE3d
Krieg betroffene Gebiete in der Afar-Region Äthiopien neu
ምስል Seyoum Getu/DW

ኅብረተሰቡ ወደ መደበኛ ኑሮ ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት ፈትኖታል

በአፋር ክልል የትግራይ ክልል አዋሳኝ ሰሜናዊ ዞን ጦርነት ያወደማቸው መሰረተ ልማቶች ወደ መደበኛ ቦታ አለመመለሳቸው ኅብረተሰቡን አረዋል ። በዞኑ በተለይም ከእረብቲ እና አባዓላ ወረዳዎች አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዎች፦ የችግሩ አሳሳቢነትን ተናግረዋል ። በአካባቢያቸው ቴሌኮሚዩኒኬሽንን ጨምሮ የወደሙ መሰረተ ልማቶች የመልሶ ጥገና እንቅስቃሴ መዘግየት ኅብረተሰቡ ወደ መደበኛ ኑሮ ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት ፈትኖታል ብለዋል ። የአፋር ሰብአዊ መብቶች ድርጅት በበኩሉ በጦርነቱ ወቅት በክልሉ ተቀብረው የቆዩ ፈንጂዎችን የማምከን ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት አለተከናወነም ብሏል ። ያም በመሆኑ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ብቻ የ50 ህጻናት ሕይወት መቀጠፉን ገልጿል ። 

በሰሜን ኢትዮጵያ ተስፋፍቶ ለሁለት ዓመታት ገደማ በቆየው ጦርነት ክፉኛ ከተጎዱ አከባቢዎች የአፋር ክልል ዞን ሁለት ወይም ሰሜናዊ ዞን በዋናነት ይጠቀሳል ፡፡ በአከባቢው እንዳልነበረች የሆነችው የትግራይ ክልል አዋሳኟ ዓባዓላ ከተማን ጨምሮ እንደ እሬብቲ፣ መጋሌ እና ኮኖባ ያሉ ስድስት ወረዳዎች ሰፊ ውድመት ከደረሰባቸው ናቸውም ይባልለታል፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየት የሰጡን የእሬብቲ ከተማ ነዋሪ እንደሚሉት በአከባቢው ከወደሙና እስካሁንም ድረስ በተሟላ ሁኔታ ካልተመለሱ መሰረተ ልማቶች የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ይጠቀሳል፡፡ በአከባቢው ከዚህ ቀደም በስፋት የኔትዎርክ አገልግሎት ሲያገኝ የነበረው አከባቢው አሁን ላይ አገልግሎቱ በከተማ ብቻ ተወስኖ ቀርቷል የሚሉት እኚህ ነዋሪ፤ ማህበረሰቡ ከዚህ በፊት የለመደውን የመረጃ ልውውጥ ልማድን እንኳን አጥቷል ነው የሚሉት፡፡ “ከዚህ በፊት በስፋት ኔትዎርክ ሲያገኙ የነበሩ አከባቢዎች አሁን ላይ እጅግ የደከመ እና በሰኣታት የተወሰነ ኔትዎርክ ነው ሚያገኙት፡፡ ያንን የለመደው ማህበረሰብ አሁን ለመረጃ ልውውጥ እንኳ ብዙ መንገድ መጓዝ የግድ እየሆነበት ነው፡፡”  

በጦርነቱ ክፉኛ ከተጎዱት የአፋር ከተሞች አንዱ
በጦርነቱ ክፉኛ ከተጎዱት የአፋር ከተሞች አንዱምስል Seyoum Getu/DW

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ትምህርት ቤት ያሉ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ቃል ብገባም እስካሁንም ወደ ተግባር የተገባም አይደለም ብለዋልም፡፡ “በርግጥ አሁን ወቅቱ ዝናባማ ስለሆነ ለጊዜውም ቢሆን ህብረተሰቡ የውሃ ችግር ተቀርፎለታል፡፡ ነግር ግን ትምህርት ቤት ጨምሮ የወደሙ ሌሎች መሰረተ ልማቶች አሁንም ድረስ መልሶ የመገንባት ስራ አልተጀመረም፡፡”  
ከአብዓላ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው ነዋሪ እንደሚሉትም ከኤልክትሪክ ጀምሮ ወደ ስፍራው የተመለሰ መሰረተ ልማት አለመኖሩ ከጦርነት ማግስት ተስፋ ኖሮት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ወደ ቀዬው የተመለሰን ህዝብ ፈትኗል፡፡ 

“በዚህ ከተማ ትምህርት ቤት ወድሟል፡፡ ሆስፒታሎችም እንዲሁ ኤሌክትሪክ አልባ በመሆናቸው በቂ አገልግሎት መስጠት አልተቻለም፡፡ ኔትዎርክ እጅግ ደካማ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ነው ያለው፡፡” 
ነዋሪዎቹ በአስተያየታቸው ለወራት እና ለዓመታት ከቤት ቀዬያቸው ተፈናቅለው የቆዩት የአከባቢው ነዋሪዎች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ወደ ቀዬያቸው እየተመለሱ መሆናቸውን በመግለጽ፤ እርዳታም ከሞላ ጎደል ለተቸገሩ የህብረተሰብ አካላት እየተዳረሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ የክልሉ ባለስልጣናት በተለይም የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር እና የኮመኪዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎችን አስተያየት ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት ስልካቸው ባለመነሳቱ ለዛሬ አልሰመረም፡፡ የአፋር ሰብኣዊ መብቶች ድርጅት ኃላፊ አቶ ገዓዝ አህምድ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ግን በክልሉ በተለይም ኪልበርቲረሱ በሚባለው በዚህ የአፋር ዞን ሁለት የችግሩ ስፋት የበርካታ ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚያስፈልገው ነው ብለዋል፡፡

አቶ ገዓዝ በዚሁ ክልል በተለይም ካሳጊታ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ በጦርነት ወቅት የተቀበሩ ፈንጂዎች በጊዜው ባለመምከናቸው ባለፈው ሳምንት ብቻ የ50 ህጻናት ህይወት መቅጠፉንም ተናግረዋል፡፡ መሰል ችግሮችን ከግንዛቤ ያስገባ ስራ መከወን እንዳለበትም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አሳስበዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ