የጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ጉብኝት
ዓርብ፣ መጋቢት 4 2018
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት ሓሙስ ወደ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከማቅናታቸው አስቀድመው ከልዑክ ቡድናቸው ጋር በጅቡቲ የቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ስለማድረጋቸው ጽህፈት ቤታቸው አሳውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤምሬትስ ጉዞአቸውን ከማድረጋቸው በፊት ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር በስልክ ስለመምከራቸውም ተነግሯል፡፡ ዐቢይ ከሩቢዮ ጋር አራት ወራት እንኳ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በስልክ መልሰው የተወያዩት “በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታን የማስፈን የጋራ ጉዳዮች ላይ ነው” ሲል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳውቋል፡፡ ውይይት የተባለው የባለስልጣናቱ የስልክ ውይይት ስለየዘው ዝርዝር ጉዳይ ግን እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡
ይህ መረጃ ከተሰማ ከሰዓታት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መድረሳቸው ነው የተሰማው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አቡዳቢ አየር ማረፍያ ሲደርሱ በወታደራዊ ዘብ አቀባበል እንደተደረገላቸዉ የሚያሳይ ፎቶግራፍም ከመረጃዉ ጋር አብሮ ይፋ አድርጓል። የኤሜሬትስ የዜና ወኪል ባሰራጨዉ ዜናየኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቡዳቢ ዓለም አየር ማረፍያ ሲደርሱ በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ፍትህ ሚኒስትር አብዱላህ ሲልጣን ቢን አዋድ አል ሁኢሚ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። መካከለኛው ምስራቅ አሜሪካ እና እስራኤል ባንድ ወገን ሆነው ኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ ከፍተኛ ውጥንቅጥ ውስጥ በገባበት ባሁን ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ወደ “ወዳጅ አገር” ለማምራት ወደዱ የሚለው ጥያቄ ግን በበርካቶች ተነስቷል፡፡
የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ከዲፕሎማሲውም ሆነ ከኢኮኖሚው አጋርነት አኳያ የኢትዮጵያ ወቅታዊው ወሳኝ ወዳጅ መሆኗ አያጠያይቅም የሚሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ የቁርጥ ቀን ወዳጅነትን የሚያሳይ ውሳኔ ይመስላል ብለዋል፡፡ “ይሄኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ የረጅም ጊዜ ጥቅም ለማግኘት የአጭር ጊዜ መስዋእትነት መክፈል” ተብሎ ልገለጽ ይችላል ያሉት ተንታኙ፤ ጉዞው እጅ ቆራጥነት አሊያም ድፍረት የተሞላበት፤ ነገር ግን ደግሞ ትልቅ የወዳጅነት መገለጫ ተደርጎ ሊገለጽ የሚችል ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ አሁን ላይ በቀጣናው ባለው ጦርነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከምትገኘው ኢምሬትስ ከበሬታንና ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ዋጋን የሚያስገኝላቸውም ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሜሪካ እና እስራኤል በጥምረት ኢራን ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ኢራን በአጸፋው ተባበሩት አረብ ኢምሬቶችን ጨምሮ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ ሚገኝባቸውን የባህረሰላጠውና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ላይ የአጸፋ ጥቃት በምትወስድበት ባሁን ወቅት ኢምሬትስ የደረሱ የመጀመሪያው የአገር መሪም ናቸው፡፡ በኢራን የአጸፋ ጥቃት የበረራ እቀባ ውስጥ ጭምር የምትገኘው የተባበሩት አረብ ኢምሬትን አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ክፉኛ ከሚጎዱም አገራት ተጠቅሳለች፡፡
የፖለቲካል ኢኮኖሚው ተንታኝ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን በአፍሪካ ቀንድ ቀጠናው የስበት መአከል ናት ያሏት ኢትዮጵያ በተቅላይ ሚኒስትሩ የመካከለኛ ምስራቅ ጉዞ ከፍ ሊል እንደሚችልም ነው በአስተያየታቸው የጠቆሙት፡፡ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የስበት ማዕከል ናት” ያሉት ባለሙያው፤ በተለይም አሁን ላይ በውስጥ ያለውን አለመረጋጋት መፍታት ከተቻለ የኢትዮጵያ ተጽእኖ በአዎንታዊነት ልጎላ እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡
ወደ መካከለኛው ምስራቅ ጉዞያቸው ከማቅናታቸው አስቀድሞ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የስልክ ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቀደም ብለው ከኩዌት ንጉስ ጋርም ስለ አገራቱ ሉዓላዊነት መደፈር አንስተው መነጋገራቸው ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር