ዶናልድ ትራምፕ ስለ ኢራን ጦርነት ለህዝባቸው ያስተላለፉት መልዕክት
ሐሙስ፣ መጋቢት 24 2018
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጦር በኢራን ላይ ሲካሄድ የቆየውን ወታደራዊ ዘመቻ ዋና ዋና ግቦቹን ማሳካቱን በመግለጽ፣ ዘመቻው በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ሳምንታት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል። ፕሬዚዳንቱ ትናንት ለህዝባቸው ባሰሙት ንግግር የኢራን ወታደራዊ አቅም መዳከሙንና አመራሮቿ መመታታቸውን እንደ ትልቅ ስኬት ጠቅሰዋል።
ጦራችንን ወደ አገራችን እንመልሳለን።» የሚለው ቃል ለደጋፊዎቻቸው ትልቅ ተስፋ የሰጠ ቢሆንም፣ የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋቱ ከቀጠለ ግን ኢራንን "ወደ ድንጋይ ዘመን" እንደሚመልሷት መዛታቸው ደግሞ ንግግራቸው በተቃርኖዎች የተሞላ አንድ የተጨበጠ አቅጣጫን ያልያዘ እንደሆነ አመላካች ነው።
የሃገር ውስጥ ደጋፊዎቻቸው ይህንን የፕሬዝዳንቱን መልዕክት እንደ ድል ብስራት ሲቆጥሩት፣ ተቃዋሚዎች ግን የነዳጅ ዋጋ መናርን፣ የባህር ላይ ንግድ መስተጓጎልን እና አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ ያለግብ እና ዓላማ መግባታቸውን እንደ ትልቅ ውድቀት ይጠቅሳሉ።እስራኤል የኃይል ሚዛኑ መቀየሩን ብታምንም አሜሪካ ስትወጣ ለሚመጣው አጸፋዊ ጥቃት እየተዘጋጀች እንደሆነ ነው የተገለጸው።
በሌላ በኩል ኢራን የአሜሪካን መውጫ የጊዜ ሰሌዳ እንደ ድካም በመቁጠር ጥቃቷን እንደምትቀጥል ምልክት አሳይታለች። ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን በታላቅ በራስ መተማመን የሰጡ ቢሆንም፣ የዓለም ገበያ፣ የፖለቲካ ተንታኞች እና የዚሁ ጦርነት ገፈት ቀማሽ የሆኑ ባለድርሻ አካላት ግን ጦርነቱ በርግጥ መቆሙን ወይም ወደ ሌላ አደገኛ ምዕራፍ መሸጋገሩን በእርግጠኝነት ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
አበበ ፈለቀ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ