1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፖለቲከኛ ታዬ ደንደዓ መታሰር

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2016

በኢትዮጵያ ሰላም ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ኃላፊነት የነበሩት ፖለቲከኛ ታዬ ደንደዓ ዛሬ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ። የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በላከዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ፤ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉት የሰላም ሚንስትር ዴኤታው ታዬ ደንደአ ለጥፋት ተልዕኮ በመሥራት ጠርጥሬቸዋለሁ ብሏል።

https://p.dw.com/p/4a50Z
አቶ ታዬ ደንዳኣ።
አቶ ታዬ ደንዳኣ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Million Haileselasi/DW

ጠ/ሚን «በሰው ደም የሚጫወቱ» ሲሉ ወርፈዋል

ላለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ሰላም ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ኃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩ ፖለቲከኛ ታዬ ደንደዓ ዛሬ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ ። የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በላከዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ፤ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉት የሰላም ሚንስትር ዴኤታው ታዬ ደንደአ ከተሰጣቸው ኃላፊነት በተቃራኒ «ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች» ጋር በመተባበር ለጥፋት ተልዕኮ በመስራት ጠርጥሬያቿለኁ ብሏል። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ፖለቲከኞች ግን ሁኔታው በአገሪቱ የፖለቲካ ችግር መስፋቱን ያሳያል ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል ።

የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል የዛሬ መግለጫው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ ከለውጡ በፊት የኦነግ አባል እንደነበሩና የለውጡ መንግስት ባደረገላቸው ምህረት ከማረሚያ ቤት ተለቀው በተለያዩ የክልል እና የፌደራል መንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እንዲሠሩ እደል መሰጠቱን አትቷል።

በትናንትናው እለት ከኃላፊነታቸው ስለመነሳታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ደብዳቤ ተጽፎ እንደደረሳቸው ያመለከቱት አቶ ታዬ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን "በሰው ደም የሚጫወቱ” በሚል ወርፈዋቸዋል፡፡ አቶ ታዬ ይህን ያሉት ስለሰላም በመስበካቸውና ሰላም ይስፈን በማለታቸው መሰል ቅጣት እንደማይገባቸው ባስረዱበት በትናንትናው እለት ጽሑፋቸው ነው፡፡

አቶ ታዬ በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለጸው የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል ግን የቀድሞውን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬን "ከሕዝብና ከመንግስት የተሰጣቸዉን ኃላፊነት መወጣት ሲገባቸው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚሰሩ ፀረሰላም ኃይሎች ጋር በመተሳሰር ለጥፋት ተልዕኮ በህቡዕ ሲሰሩ ደረስኩበት” ብሏል፡፡

የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫዉ በተለያዩ አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ሲፈፀሙ በነበሩ የሽብር ተግባራት በተለይም ደግሞ ከእገታ ጋር በተያያዘ የአቶ ታዬ እጅ ይገኛልም ሲል ከሷቸዋል፡፡ ግብረ-ኃይሉ ፖለቲከኛው እኩይ የተባለውን መሰል ዓላማ ሲያራምዱ የቆዩት በመንግስት ቁጥጥር ስር ሊዉሉ እንደሚችሉ ገምተው "ፀረ ሰላም” የተባሉ ጽሑፎችና ንግግሮችን በማሰራጨት ሷቸውም በቁትጥር ስር መዋላቸውን አመልክቷል፡፡

በአወዛጋቢው ሰሞነኛው የፖለቲከኛ ታዬ ደንደአ አስተያየቶችና የተከተሉትን ርምጃ በማስመልከት አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ፤ ነገሩ የሚጠበቅ ነው በማለት የግል ምልከታቸውን ነግረውናል፡፡ "ባጠቃላይ በኔ እይታ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታዬ ኦህደድ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ወደ ብልጽግና ሲመጣ ያየነውን ክፍተት ስንተች ሲሞግቱን ነበር፡፡ ሕገመንግስቱ ሲደፈጠጥ እየተቃወምን ነበር፡፡ አሁን በኋላ ላይ አቶ ታዬ ሲናገሩ የቆዩት ስርዓቱ ወደታቀደለት አቅጣጫ ሳይሆን መስመሩን የሳተ መሆኑን መረዳታቸውን ነው ከጽሑፋቸው የተረዳሁት፡፡ ስርዓቱ ወደ አስከፊ አቅጣጫ እነደሚሄድ ሲነገራቸው ሲተቹም ነበር” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
አቶ ታዬ ደንደኣ በትናንትናው እለት ከኃላፊነታቸው ስለመነሳታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ደብዳቤ ተጽፎ እንደደረሳቸው ገልጸዋልምስል Facebook.com/Office PM Ethiopia

አቶ ታዬን በቅርበት በጓደኝነት እንደሚያውቁአቸውና ከዚህ በፊት በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ አብረው ማስተማራቸውን የገለጹት አቶ መብራቱ ገርጂሶ በበኩላቸው አቶ ታዬ ያመኑበትን ከመናገር ወደ ኋላ የማይሉ ይሏቸዋል፡፡  "ሰውየው ያመኑበትን መትፎም ይሁን ጥሩ ከመናገር ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ይሁንና ስለሰሞኑ ውስጥ ውስጡን እኛ ባናውቅም ከሚጽፉአቸው ነገሮች ተነስተን ካየነው፤ ሰላም ውረድ ነው ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ እንደሃሳብ መፈራት ያለበት ነው ብዬ አላምንም፡፡ ይሁንና መንግስት በራሱ መንገድ ከስልጣን አንስቶአቸዋል፡፡ እንደኔ እምነት ግን ሰላም ብወርድ መልካም ከባቢ ፈጠራል መባሉ መትፎ ተደርጎ መታየት የለበትም ነው የምለው” ብለዋል፡፡ 

ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ በፊናቸው አዝማሚያው ወደመጥፎ እንዳይወስድ የሰጋሉ፡፡ "ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ እሳቸው ደግሞ በሁለት መስመር ደብዳቤ ከስልጣን አንስተውአቸዋል፡፡ ያንን ተከትሎ ግን የሚናገሯቸው ንግግሮች ለአገርም ገንቢ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ ልጆች ጫዋታ እንጂ ተገቢም ነው አልልም፡፡ ፖለቲካው ወደ መትፎ አዝማሚያ እንደሚሄድ ግን ይሰማናል” ነው ያሉት፡፡

የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ግን "መንግስታዊና የፓርቲ መዋቅሩን በሴራ ለመናድ በህቡእ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የቆዩ መሆናቸውን” ባደረኩት ምርመራና ክትትል አረጋግጫለሁ ነው ያለው፡፡ በክትትሉም አቶ ታዬ ደንደአ ከኦነግ ሸኔ አመራሮችና በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር መንግስትን በአመጽ ለመጣል አስሬዋል ነው ያሏቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ
ላለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ሰላም ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ኃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩ ፖለቲከኛ ታዬ ደንደዓ ዛሬ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ ። የአዲስ አበባ ከተማምስል Solomon Muchie/DW

ተጠርጣሪዉ በሕግ ቁጥጥር ሥር ሲውሉ በመኖሪያ ቤታቸው ዉስጥ በተደረገ ፍተሻ፤ በህቡዕ ለሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ሲገለገሉበት የነበሩ 9 ሞባይሎች፣ 4 ላፕቶፖች፣ 3 አይፖዶች፣ በርካታ ፍላሾች፣ 4 የተለያዩ ተሽከርካሪ ሰሌዳዎች እና ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃና ሽጉጦች ከመሰል ጥይቶች ጋር እንዲሁም የኦነግ ሸኔ አርማዎችና በተለያዩ ግለሰቦች ስም የተዘጋጁ የታጣቂ ቡድኑ መታወቂያዎች፣ ሰነዶችና ማስታወሻዎች ማግኘቱንም መግለጫው አትቷል፡፡ በብርበራው ወቅት በመኖሪያ ቤቱ በሶስት መታወቂያዎች የሚጠቀም አንድ የኦነግ ሸኔ አባል ተገኝተው በቁጥጥር ስር ውለዋልም ብሏል መግለጫው፡፡

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ በዚሁ መግለጫው በመንግስትና በፖርቲ መዋቅር ዉስጥ ሆነዉ በእኩይ ዓላማ በተሰማሩ አካላት ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ ጥብቅ ክትትል እያደረገባቸዉ እንደሚገኝና ሕጋዊ ርምጃዎቹን በተከታታይ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ዐስታውቋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ