1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘንድሮ የሚካሄደው የጋና ምርጫ

ቅዳሜ፣ መስከረም 11 2017

ጋና አብዛኛውን ጊዜ በመፈንቅለ መንግሥት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት በሚታወቀው ምዕራብ አፍሪቃ የዴሞክራሲ ጮራ በመባል ትገለጣለች። ሆኖም ግን ሀገሪቱ በመጪው ታኅሣስ ወር ከምታካሂደው ምርጫ አስቀድማ ባልተፈቱ ጉዳዮች የፊጥኝ ተይዛለች።

https://p.dw.com/p/4kv1L
የጋና ፖለቲከኞች
የጋና ተፎካካሪ ፖለቲከኞች በስተቀኝ፤ የNDCው እጩ ተወዳዳሪ ጆን ድራማኒ ማሀማ በስተግራ፤ የገዢው ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ማሀማዱ ባውሚያምስል Nipah Dennis/AFP/Getty Images, Olympia de Maismont/AFP

ዘንድሮ የሚካሄደው የጋና ምርጫ

 

አንዱ ጉዳይ ደግሞ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ምክር ቤት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ NDC፤ የሰላም ስምምነት አልፈርምም ማለቱ ነው። በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ምርጫ በሚካሄድበት ዓመት ሰላማዊ የድምፅ አሰጣጥ እንዲኖር የሰላም ስምምነት መፈራረም ተለምዷል።

በሀገሪቱ የሰላማዊ ምርጫን አስፈላጊነት የሚያስገነዝበው የጋና ብሔራዊ የሰላም ምክር ቤት የጋና ፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉትን መመሪያዎች ለማክበር ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩ ይፈልጋል። ሆኖም NDC በስምምነቶቹ ለመስማማት አለመፈለጉ፤ ብዙዎች የዘንድሮውን ምርጫ በስጋት እንዲመለከቱት አድርጓል።

የጋና እውነት አጣሪ ተቋም እንደሚለው የዛሬ አምስት ዓመት በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ፤ በተነሳው አመጽ ቢያንስ ስምንት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የጋና ብሔራዊ የሰላም ምክር ቤት ሊቀመንበር፤ NDC ስምምነቱን አልፈርምም ማለቱ ያስከተለውን የምርጫ አመጽ ስጋት ከኅብረተሰቡ ለማራቅ የግድ ምክር ቤቱ ለማግባባት ጥረቱን እንደሚቀጥል ለጋና መንግሥታዊ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

ለምድነው NDC የሰላም ውሉን አልፈርምም ያለው?

 ተቃዋሚው ፓርቲ NDC የጋና ብሔራዊ የሰላም ምክር ቤት በዛሬ አምስት ዓመቱ ምርጫ እምነት እንደማይጣልበት አሳይቷል ሲል ይሞግታል። የፓርቲው ሊቀመንበር ጆንሰን አሴይዱ ናክቲህ « ያለፈው ስምምነት ምንም እንዳላመጣ ሁኑ፤ የሰላም ስምምነቱን መፈረም ለፓርቲያቸውም ምንም ማለት አይደለም።» ነው የሚሉት።

ፓርቲያቸው እንደውም ዛሬም ያኔ በምርጫ ወቅት ለተገደሉት ወገኖች ፍትህ እየጠየቀ መሆኑን ይገልጻል። የፓርቲው ግንባር ቀደም ተጠሪ የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆን ማሃመት የወቅቱን የጋና ፕሬዝደንት ናና አኩፎ አዶን መንግሥት ለዚህ ድርጊት ተጠያቂ ያደርጋሉ። በዚያም ላይ በወቅቱ  በተካሄደውና ገዢው አዲሱ የጀግኖች ፓርቲ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ NPP ባሸነፈበት ምርጫ ተፈጽሟል ስለሚለው የድምፅ ሳጥን ስርቆትም እንዲጣራለት ይፈልጋል። ይህም ብቻም አይደለም NDC፤ ገዢው ፓርቲ በሰላም ስምምነቱ ሰበብ የተቃዋሚዎችን አቋም ለማስለወጥ ይፈልጋል ሲልም ይሞግታል።

ገዢው አዲሱ የጀግኖች ፓርቲ ምላሽ

የ NPP ዋና ጸሐፊ በሰጡት መግለጫ ገዢው ፓርቲ NDC ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ጤናማ ያልሆኑ መግለጫዎችን ከማውጣት እንዲቆጠብ ጠይቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ፓርቲው ባለድርሻ አካላትም የNDCን አካሄድ እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርቧል። ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የያዘውን አቋም ችላ ብለውም በሰላም ምክር ቤቱ መወከላቸውንም ተችቷል። ገዢው ፓርቲ ጋና በመጪው ታኅሣስ ወር የምርጫ ውጤት ምንም ቢሆን፤ ወደጦርነት ልትገባ እንደማትችልም አጽንኦት ሰጥቷል። የሕዝቡ ፍላጎት ይሆናልም ብሏል።

ምሁራንስ ምን ይላሉ?

ካለፈው ዓመት አንስቶ የጋና የምርጫ ኮሚሽን እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ስጋቶች እየተነሱ ነው። ገሚሱ ሕዝብ፤ የተቃዋሚው ፓርቲ NDCን ጨምሮ የምርጫ ኮሚሽኑ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ አለበት ብለው ያምናሉ፤ በዚህም ምክንያት የምርጫ ውጤቱ ላይ ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሥልጣናት ጫና ሊያደርጉ ይችላሉም ባይ ናቸው።

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ጋናዊው የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ጡረተኛው ኮሎኔል ፌስቱስ አቦጌ፤ ችግሩ በከፊል በምርጫ ኮሚሽኑ ላይ ያለው እምነት ማጣት እንደሆነ ይገልጻሉ።

የጋና ጋዜጦች
በምርጫው ዜና ላይ ያተኮሩት የጋና ጋዜጦች ምስል Pius Utomi Ekpei/AFP/Getty Images

«በግል እይታዬ በምርጫ ሂደት ቁልፍ ባለድርሻ የሆነው የምርጫ ኮሚሽኑ ተዓማኒነት አጥቷል። እኔ እንደማስበው የነበረው ታማኝነት ተበላሽቷል። ስለዚህ፤ በመደበኛነት ትልቅ ጉዳይ ባልነበረው የታማኝነት ጉድለት እየተሰቃየ ነው። በዚህም ምክንያት የምርጫ ኮሚሽኑ ሊታመን አይችልም እንዲሁም መታመን የለበትም የሚለው ስሜት፤ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በርካታ ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓል። እንደገና፤ የምርጫ ኮሚሽኑ |ሕገ መንግሥቱ ኮሚሽኑን ገለልተኛ አድርጎ ይገልጸዋል፤ ይህ ማለት የምርጫ ኮሚሽኑ ተጠያቂ አይደለም። እዚህ ላይ ነው ችግሩ ያለው።»

ሰላማዊ ምርጫን የማረጋገጥ ፈተናዎች

የብሔራዊ ሰላም ኮሚሽኑ ሁሉም ፓርቲዎች የሰላም ስምምነቱን በመፈረም፤ ደንቡን ማክበራቸውን የማረጋገጥ ሚና አለው። ሆኖም ግን ፌስቱስ አቦአጋይ፤ የሰላም ስምምነቱን መፈረሙ ብቻ ሰላማዊ ምርጫ እንዲኖር ዋስትና ሊሆን አይችልም ብለው ያምናሉ። ለአስርት ዓመታት የዘለቀው የሰላም ውል በምርጫ ጊዜ ተቀባይነት ቢያገኝም፤ አመጽ ያልተቀሰቀሰበት ምርጫ ግን ተካሂዶ እንደማያውቅም ይናገራሉ። ከሆኑም የከፋው ደግሞ ከአምስት ዓመት በፊት የነበረው ምርጫ እንደሆነም ያስታውሳሉ።

በተቃራኒው ሌሎች ደግሞ የNDC የሰላም ውሉን አለመፈረም በመጪው ምርጫ የፖለቲካ አመጹን ሊያባብሰው እንደሚችል ይፈራሉ። በጋና ተዓማኒ እና ሰላማዊ ምርጫዎችን በማበረታታት የሚደግፈው የሀገሪቱ ብሔራዊ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ታዛቢዎች ጥምረት አስተባባሪ አልበር አርኸን፤ አካሄዱ ለምርጫ አመጽ ፈቃድ እንደመስጠት ነው ይላሉ።

«እኔ እንደምለው፤ NDC እዚህ ላይ የሚለው ነጥብ ሊኖረው ይችላል፤ ሆኖም ግን ሁለት ስህተቶች ትክክል ነገር ሊሠሩ አይችሉም። ምክንያቱም ለመፈረም ፈቃደኛ አለመሆን ማለት፤ ምናልባት እሱም የሆኑ ድርጊቶችን ለመፈጸም ተዘጋጅቻለሁ እንደማለት ነው። ይህ ማለትም ማንም ምንም ቢያደርግ አይቀጣም እያለ ነው። ስለዚህ የእነሱ ሰዎችም ቢሆኑ ምናልባት ሊያደርጉ ይችላሉ።»

የNDC ስጋት ከምርጫው አስቀድሞ መፍትሄ ያገኝ ይሆን?

ለምርጫው ሦስት ወራት ቢቀሩትም ምርመራ ስለመደረጉ የሚያሳይ ምንም ምልክት የለም። ከዚህ በመነሳትም የNDC ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ ያጠራጥራል።

ሌላው በNDC የተነሳው ጥያቄ የፖሊስ ዋና ኢንስፔክተር ለሰላም አስተማማኝ ምልክት እንዲሆን በሰላም ስምምነቱ ላይ ፊርማው ይካተት ነው። አርኸን ግን እንዲህ ያለው ነገር አይቻልም ባይ ናቸው። ኦቦጌ በበኩላቸው ዋናው ስጋት የምርጫ ኮሚሽኑ ሥልጣኑ ስላልተሰጠው፤ ምንም ዓይነት እገዳ መጣል አይችልም። ይህንንም ትልቅ ድክመት ይሉታል።

መፍትሄው ምን ይሆን?

NDC ያቀረበው ጥያቄ ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ የሚያገኝ አይመስልም። ሆኖም ግን በሰላም ስምምነቱ የተወሰነ ስኬት እንዲኖረው ለማድረግ አፈጻጸሙ ላይ ለውጥ መደረግ ይኖርበታል። አርኸን እንደሚሉት፤ ተቃዋሚው ፓርቲ ስጋቶቹ ምላሽ እንዲያገኙ ግፊት እያደረገ ስምምነቱን መፈረም አለበት። አቦጌ ደግሞ በምርጫ ጊዜ የሰላም ውሉ ስኬታማነቱ እንዲጨምር ሕጋዊ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ይበጃል ብለው ያምናሉ። እንዲህ ቢሆን በፓርቲዎች መካከል መተማመን ይኖራል።

 

ሸዋዬ ለገሠ