1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 3 2013

አኩፎ አዶ ምርጫውን ማሸነፋቸው ሲታወጅ ለተቀናቃኛቸው NDC በአንድነት የመሥራት ጥሪ ቢያቀርቡም NDC ብዙም ሳይቆይ ነው ውጤቱን እንደማይቀበል ያሳወቀው። በወታደሩ ጣልቃ ገብነት በአንዳንድ የምርጫ ወረዳዎች ውጤቶች እንዲቀየሩ ተደርጓል ሲሉ  የ62 ዓመቱ የቀድሞ የጋና መሪ ማሃማ ከሰዋል።ድርጊቱንም የጋናን ሕዝብ ሉዓላዊነት የሚጋፋ ብለውታል። 

https://p.dw.com/p/3mbYe
Ghana Präsident Nana Addo Dankwa Akufo-Addo
ምስል Anthony Anex/KEYSTONE/picture alliance

የጋና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትና ውዝግቡ

የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ በጠባብ ልዩነት ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ተመርጠዋል ። የጋና የምርጫ ኮሚሽን የ 76 ዓመቱ አኩፎ አዶ ማሸነፋቸውን ባለፈው ረቡዕ ነው ያሳወቀው።የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ጆን አዱክዌይ ሜንሳ ይፋ ባደረጉት ውጤት መሠረት የመሃል ቀኙ «አዲስ አርበኞች ፓርቲ» በምሃጻሩ NPP መሪ አኩፎ አዶ 6 ሚሊዮን 730 ሺህ 413 ወይም 51.59 በመቶ ድምጽ ነው ያሸነፉት።ተቀናቃኛቸው የመሀል ግራው ፓርቲ የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ምክር ቤት በምህጻሩ NDCው ጆን ማሃማ ደግሞ 6 ሚሊዮን 214 ሺህ 889 የመራጭ ድምጽ ወይም 47.36  በመቶ ድምጽ ነው ያገኘው። አኩፎ አዶ ከድሉ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ህዝቡ በርሳቸው ላይ ለጣለው እምነት አመስግነው በሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው ምንም አይመጣም ብለው ዘና እንደማይሉ ነው የተናገሩት።
ጋናውያን ወገኖቼ በዚህ ድል እጅግ አድርጌ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።በእኔ ላይ ላሳደራችሁት እምነት ጥልቅ ስሜት ነው ያለኝ።ይህንንም በቀላሉ የማየው ጉዳይ አይደለም።ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን መምራቱን ላረጋገጠ፣ በሥልጣን ላይ ለነበረ ፕሬዝዳንት ነገሮችን አቅሎ የማየትና የመዝናናት አዝማሚያ ሊኖር ይችላል።ምክንያቱም የሚያጣው ወይም ማሳመን ያለበት ጉዳይ አይኖርም ።ሆኖም እኔ የተለየ ባህርይ ነው ያለኝ።»
የጋና የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት መሠረት የአኩፎ አዶ ፓርቲ NPP በሃገሪቱ ምክር ቤት  ያገኘው መቀመጫ ተቀናቃኙ NDC ካሸነፈው በአንድ ብቻ ነው የሚበልጠው። NPP  137 መቀመጫዎች ሲያገኝ NDC ደግሞ 136ቱን ወስዷል።  ፓርቲዎቹ በፓርላማው ያገኙት መቀመጫ በአንድ ብቻ መበላለጡን መነሻ በማድረግ ይመስላል፣አኩፎ አዶ ውጤቱ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል ብለዋል።
«የጋና ሕዝብ፣ ሁለቱ ፓርቲዎች NPP እና NDC ለሀገራቸው ደኅንነት ሲሉ በተለይ በርላማው ውስጥ በጋራ መስራት እንዳለባቸው የምርጫው ውጤቶቹ ግልጽን የማያወላዳ አድርገውታል። ጋና የሚገባት ቦታ ላይ እንድትደርስ፣ሁላችንም የፖለቲካ ወገንተኝነታችንን ትተን አንድ የምንሆንበት እጅ ለእጅ የምንያያዝበት ጎን ለጎን የምንቆምበት እና ጠንክረን መሥራት ያለብን አሁን ነው።» 
ምንም እንኳን አኩፎ አዶ ምርጫውን ማሸነፋቸው ሲታወጅ ለተቀናቃኛቸው ለNDC ይህን ጥሪ ቢያቀርቡም NDC ግን ብዙም ሳይቆይ ነው ውጤቱን እንደማይቀበል ያስታወቀው።የፓርቲው ሊቀ መንበር የቀድሞው የጋና መሪ ጆን ማሃማ 
«የህዝቡ የተቀደሰ ውሳኔ መከበር አለበት፤መጠበቅም አለበት።የጋና ህዝብ ተወካይ ሆኜ ህዝቡን ለመጥቀም ባገለገልኩባቸው ዓመታት ይህን ማድረግ ደስታዬ ነበር።ለዚህም ነው ዛሬ ምሽት  የፈጠራና የስህተት ምርጫ ውጤትን ላለመቀበል ከፊታችሁ የቆምኩት ።»
የምክር ቤት አባላት ምርጫ ውጤት ሙሉ በሙሉ ባይገለጸም NDC ፣ያሸነፍኩት የምክር ቤት መቀመጫ ብዛት 140 ነው ሲል አስታውቋል። በወታደሩ ጣልቃ ገብነት በአንዳንድ የምርጫ ወረዳዎች ውጤቶች እንዲቀየሩ ተደርጓል ሲሉ  የ62 ዓመቱ ማሃማ ከሰዋል።ድርጊቱንም የጋናን ሕዝብ ሉዓላዊነት የሚጋፋ ብለውታል። 
«ከምርጫው በኋላ ከ140 ው የምርጫ ወረዳዎች አምስቱን ዒላማ አድርጎ የመስረቅና የህዝቡን ውሳኔ የመቀልበስ ሙከራ ሆነ ተብሎ ተደርጓል።በምርጫ ወረዳዎቹ የሆነውን በቅርበት መመልከትና ዝርዝር ምርመራም ማድረግ ፣ ዴሞክራሲያችን ላይ ጥቁር ደመና እንዲያንዣብብ አድርጓል። »
የጋና ምርጫ ታዛቢዎች ምርጫው በጥቅሉ ነፃና ትክክለኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።የአውሮጳ ኅብረት ዋና ታዛቢ ዣቭየር ናርት ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጋናውያን በነጻነት ድምጻቸውን ሰጥተዋል ሲሉ መስክረዋል። ናርት በአንዳንድ አካባቢዎች ሁከቶች እንደነበሩም አልሸሸጉም ደረጃቸው ግን ታዛቢው እንዳሉት መጠነኛ ነበር።በምርጫው እለትም ሆነ ከዚያ በፊት በተካሄዱት የምርጫ ዘመቻዎች የግጭት ስጋት የነበረ ቢሆንም እንደ መታደል ሆኖ አልተከሰተም ብለዋል ናት። ያም ሆኖ የተወሰኑ በተባሉ ከምርጫ ጋር በተያያዙ ሁከቶች የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስራ ዘጠኝ ደግሞ መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታውቋል። 
የጋና፣ዴሞክራሲ 30 ዓመት አስቆጥሯል።በነዚህ ዓመታት በሃገሪቱ ሰባት ሰላማዊ ምርጫዎችና የሥልጣን ሽግግሮች ተካሂደዋል።  በዚህ ሳምንቱ የጋና ምርጫ ኮሮና ተጽእኖ ያሳደረ አይመስልም።ለመምረጥ ከተመዘገበው 79 በመቶው ማለትም 13 ሚሊዮን 434 ሺህ 574ቱ ድምጹን ሰጥቷል። ማሃማ እና አኩፎ አዶ በሁለት ምርጫዎች ተፎካክረዋል። ማሃማ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2016 ለ4 ዓመታት የጋና ፕሬዝዳንት ነበሩ።አኩፎ አዶ  በዛሬ አራት ዓመቱ ምርጫ አሸንፈዋቸው ሥልጣን ያዙ።ያኔ ም እንደአሁኑ በጠባብ ልዩነት ነበር  ማሃማ የተሸነፉት።ጋና በአኩፎ አዶ ዘመነ ሥልጣን ከፍተኛእድገት ማስመዝገቧ ነው የሚነገረው። በዚህ ወቅት ኤኮኖሚው እንደ ከዚህ ቀደሙ በካካዋ ምርት ላይ ብቻ ጥገኛ ሳይሆን ነዳጅ ዘይትና ወርቅንም የውጭ ንግድ አማራጭ የገቢ ምንጮች አድርጓል።ምንም እንኳን ጋና ብዙ ተራምዳለች ቢባልም፣ አብዛኛዎቹ ጋናውያን እጅግ የከፋ የድህነት አዘቅት ውስጥ ነው ያሉት።ንጽህ የመጠጥ ውኃም ሆነ መብራት አያገኙም። በኮሮና ወረርሽኝ ክፉኛ በተጎዳችው የ30 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ ጋና አሁን እድገቱ በ30 ዓመት ታሪኳ ዝቅ ያለ እንደሚሆን ነው የሚገመተው።አኩፎ አዶ የሃገሪቱን እድገት ለማፋጠን የ17 ቢሊዮን ዶላር መርሃግብር አቅደዋል።ይሁንና በጠባብ ልዩነት ማሸነፋቸው እቅዳቸውን ለመተግበር ፈተና ሳይሆንባቸው እንደማይቀር ይገመታል።

Ghana Wahl l Anhängerin der New Patriotic Party (NPP) in Accra
ምስል Pius Utomi Ekpei/AFP
Afrika Ghana Präsidentschaftswahlen  John Dramani Mahama
ምስል Nipah Dennis/AFP/Getty Images

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ