1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የቀጠለዉ የድሮን ጥቃት

ሐሙስ፣ የካቲት 14 2016

“የሞቱትን አንድ ሁለት ብለን ባንቆጥርም ባለው መረጃ ፣ 40 ነው የተባለው፣ እናት ሞታለች፣ አባት ቤት ይጠብቁ ስለነበር ወደ ቦታው ባለመሄዳቸው ተርፈዋል፣ በእለቱ ክርስትና የተነሳው ህፃኑ ሁለቱም አያቶች፣ አክስት አጎት፣ ሞተዋል፣ ህፃኑ አልሞተም ተርፏል፡፡” አንድ የአካባቢው ነዋሪ

https://p.dw.com/p/4ckHr
Karte Äthiopien Amhara ETH

የድሮን ጥቃት በአማራ ክልል

ባለፈው ሰኞ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላ ድንጋይ ከተማ አቅራቢያ ሰላ መገንጠያ በተባለ ቦታ ላይ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ንፁሐን መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ ህፃንን ክርስትና አስነስተው ሲመለሱ አደጋ ከደረሰባቸው መካከል የህፃኑ እናትም ህይወቷ ማለፉ ተነግሯል፣ በተመታው መኪና ውስጥ ከነበሩ ተሳፋሪዎች መካከል 2 ልጆቻቸው እንደተገደሉባቸው አንድ አባት ገልጠዋል፡፡

ባለፈው ሰኞ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ  ልዩ ስሙ “ሰላ መገንጠያ” በተባለ አካባቢ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱ በተፈፀመበት አካባቢ የነበሩና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሰላ ደንጋይ ነዋሪ በሰጡን አስተያት  ሳሊት ከተባለ ከተማ የህፃን ልጅ የክርስትና ጥምቀት ፈፅመው በአይሲዙ የጭነት መኪና ተሳፍረው በመመለስ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ የድሮን ጥቃት ደርሶ እስከ 10 ዓመት አድሜ ያላቸው ህፃናትና ሌሎች ንፁሀን ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል፡፡

“ክርስትና ነበር፣ የተሰበሰቡ እናት፣ እህት፣ ወንድም አክስት፣ የዘመድ ልጆች ነበሩ፡፡ የክርስትናውን ድግስ በልተውና ጠጥተው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ነበሩ፣ አይሱዙ መኪና ነበረች፣ በዚያች መኪና ወላዷና ሌሎችም ሰዎች ተጭነው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ የድሮን ድምፅ ተሰማ፣ ከተማው ላይ ነበርን እኛም ሰማን፣ በመኪናው ውስጥ የነበሩ ንፁሀን ናቸው፣ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፣ ከ10 ዓመት በታች ሁሉ ህፃናት ነበሩበት፡፡” ነው ያሉት፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪው “በጥቃቱ ክርስትና አስነስታ ስትመለስ የነበረች እናት ህይወቷ ያለፈ ሲሆን ህጻኑ ደግሞ በተዓምር ከሞት አምልጧል” ብለዋል፡፡ ሌሎች 40 ያክል ሰዎች ደግሞ በጥቃቱ መገደላቸውን መስማታቸውን መልክተዋል፡፡

“የሞቱትን አንድ ሁለት ብለን ባንቆጥርም ባለው መረጃ ፣ 40 ነው የተባለው፣ እናት ሞታለች፣ አባት ቤት ይጠብቁ ስለነበር ወደ ቦታው ባለመሄዳቸው ተርፈዋል፣ በእለቱ ክርስትና የተነሳው ህፃኑ ሁለቱም አያቶች፣ አክስት አጎት፣ ሞተዋል፣ ህፃኑ አልሞተም ተርፏል፡፡” ብለዋል፡፡

ሌላ የሰላ ድንጋይ ከተማ አስተያት ሰጪ በበኩላቸው በጥቃቱ የሞቱትን ቁጥር በትክክል መናገር ባይችሉም ከአንድ ቤተሰብ እስከ 7 ሰዎች መገደላቸውን በስልክ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

“ጉዳት የደረሰው ከእኛ አካባቢ ከክርስትና ሲመለሱ ሰኞ እለት አይሱዙ ተሳፍረው በነበሩ ሰዎች ላይ ሰላ መገንጠያ ላይ ነው፡፡ ክርስትና ሲያስነሱ የነበሩ ቤተሰቦች እንዳለቁ ነው ያለው መረጃ፣ ምን ያክል ሰው እንደሞተ ባይታወቅም በጣም ብዙ ሰው እንደተጎዳ ነው መረጃ ያለው፣ ከአንድ ቤተሰብ እስከ ሰባት ሰዎች እንደሞቱ ከባለክርስትናው ቤተሰብ ተነግሯል፣ (በእለቱ)ጦርነት የነበረው ከእኛ ከሳሲት ከተማ ጋውና ወርዶ ፊላ ገነት ነው፣ ይህም ወደ 15 ኪሎሜትር ይርቃል፡፡”

የክርስትና ስነርዓቱ ተካፋይ ያልነበሩ ነገር ግን “ፊላ ገነት” በተባለው አካባቢ ጦርነት ስለነበረና ጦርነቱ ሊደርስባቸው ይችላል በሚል  ከሳሲት ከተማ ልጆቻቸውን  የትራንስፖርት ገንዘብ ከፍለው በክርስትና ስነስዓት ላይ የነበሩ ሰዎችን አሳፍሮ በነበረው የጭነት መኪና እንዲሳፈሩ ያደረጉ አንድ አርሶ አደር አባት ሁለት ህፃናት ልጆቻቸው በእለቱ በጥቃቱ እንደተገደሉባቸውና ቀብራቸው እንደተፈፀመ ገልጠዋል፡፡

“ ... ተማሪዎች ናቸው፣ ተኩስ ስለነበር (ፊላ ገነት) እነሱን አሸሻለሁ ብየ ነው፣ ንፁሀን ናቸው፣ ከጦርነቱ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም (ጥቃቱ) የ10 ዓመትና የ8 ዓመት ተማሪዎች ናቸው፣ ሴትና ወንድ ናቸው፣ ቀብር ተከናውኗል፣ ብዙ ሰው ደግሞ ቆስሏል፡፡”

ጥቃቱ ከተፈፀመበት ሰላ መገንጠያ በግምት ከ15 እስከ 20 ኪሎሜትር  ቦታ ላይ በእለቱ በፋኖና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ጦርነት እንደነበርም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክተን ተጨማሪ አስተያት ለማካተት ለአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታና ለክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊዎች ብንደውልም ስልካቸው አይነሳም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለው ነገርም የለም ።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ኂሩት መለሰ