1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የሚፈፀም ድሮን ጥቃት እንዳሳሳቢ ነው ፤ የተመድ

ሰኞ፣ ኅዳር 10 2016

በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው የትጥቅ ውጊያ ምክንያት በሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮኖች የሚደርሱት ጥቃቶች አሳሳቢ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4ZDmd
Kairo UN-Menschenrechtskommissar Türk
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የበላይ ምስል KHALED DESOUKI/AFP

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማሳሰቢያ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል የሚፈፀም ድሮን ጥቃት እንዳሳሰበው ገለፀ

በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው የትጥቅ ውጊያ ምክንያት በሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮኖች የሚደርሱት ጥቃቶች አሳሳቢ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ። 

ጥቅምት 26 በዋደራ ወረዳ በአንድ ትምህርት ቤት ላይ የተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሦስት መምህራንን ጨምሮ 7 ሰዎች፣ ጥቅምት 29 በምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋብር ከተማ በመነሃሪያ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 13 ሰዎች መገደላቸውን የገለፀው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ በክልሉም ይሁን በሌሎች አካባቢዎች የቀጠሉ ያላቸው የመብት ጥሰቶችና የዘፈቀደ እሥሮች አሳሳቢነታቸው መጨመሩን አመልክቷል። መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት በአማራ ክልል

በክልሉ ያለው ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ "እየተባባሰ" የመጣ መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በበኩሉ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሰጠቱ በግጭቱ ውስጥ "ምንም አይነት ተሳትፎ የሌላቸው" ሰዎች ላይ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ ማፈናቀል፣ ጾታዊ ጥቃት እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ተከስቷል ሲል ባወጣው መግለጫ ገልጿል። 

በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ምላሽ ለማግኘት ጥረት ብናደርግም ለዛሬ አልተሳካም። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል ድሮንን ጨምሮ በከባድ የጦር መሣሪያዎች በተሰነዘሩ ጥቃቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱንና 200 ሴቶች መደፈራቸውን በተመለከተ ያወጣውን መግለጫ ከዚህ በፊት ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።


የመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባ ይዘት ምን ይመስላል?


የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል ግጭት ውስጥ ያሉት አካላት ሕገ ወጥ ካላቸው ጥቃቶች እንዲቆጠቡ እና በጦርነቱ ምንም ተሳትፎ የሌላቸው ሰላማዊ ሰዎችን ደህንነታቸውን እንዲጠብቁ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
በተለይ በሰሜን ምዕራብ አማራ እና ሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች የዘፈቀደ እሥራትን ጨምሮ ቀጥሏል ያለው "የሰብአዊ መብት ረገጣ እና የመብት ጥሰት በእጅጉ አሳሳቢ ነው" ሲል አስታውቋል።
የድርጅቱ የሰብአዊ መብት ጽ/ ቤት በሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች እና ሌሎች ጥቃቶች በዚሁ ክልል አስከፊ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ጠቅሷል።
በመንግስት ኃይሎች በተወሰደ ባለው የድሮን ጥቃት ዋደራ ወረዳ የሚገኘኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ሦስት መምህራንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ስለመገደላቸው መግለጫው ያትታል። በክልሉ የተፈፀሙ ሌሎች የድሮን ጥቃቶችን ፣ የደረሰውን የጉዳት ሁኔታ በቦታ እና በቀን ጠቅሶ ያወጣው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የፋኖ ታጣቂዎች በተለያዩ አካባቢዎች የየአካባቢ ባለሥልጣናትን እየገደሉ መሆኑንም ድርጊቱ የተፈፀመበትን ቦታና ቀን ጭምር ጠቅሶ ዘርዝሯል።ያለተጠያቂነት እየተባባሰ የመጣው የሰብአዊ መብት ጥሰት በኢትዮጵያ
በዘለቀው ደም አፋሳሽ የመከላከያ እና የፋኖ የትጥቅ ግጭት ከባድ የጦር መሣሪያዎች በንፁሃን ዜጎች መኖሪያ አካባቢዎች እያረፉ የከፋ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አንድ የቡሬ ከተማ ነዋሪ ለዴቼ ቬለ በቅርቡ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል ግጭት ውስጥ ያሉት አካላት ሕገ ወጥ ካላቸው ጥቃቶች እንዲቆጠቡ እና በጦርነቱ ምንም ተሳትፎ የሌላቸው ሰላማዊ ሰዎችን ደህንነታቸውን እንዲጠብቁ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።ምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መሪያ ቤት
በክልሉ ያለው ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ "እየተባባሰ" የመጣ መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በበኩሉ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሰጠቱ በግጭቱ ውስጥ "ምንም አይነት ተሳትፎ የሌላቸው" ሰዎች ላይ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ ማፈናቀል፣ ጾታዊ ጥቃት እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ተከስቷል ሲል ባወጣው መግለጫ ገልጿል። ምስል Solomon Muchie/DW

 

በክልሉ ያለውን የመብት ጥሰት ለመመርመር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ችግር እንደገጠመው መግለጹ 

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በአማራ ክልል ግጭት ተፋላሚ ወገኖች በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸውን ሰዎችና ንብረቶች ዒላማ ከማድረግ እንዲቆጠቡና ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቋል። ኢሰመጉ በክልሉ ያለው ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን ዘላቂና በቂ መፍትሔ ባለመሰጠቱ ምክንያት ከፍተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ ይገኛሉ ብሏል፡፡
"በግጭቱ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች ላይ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ ማፈናቀል፣ ጾታዊ ጥቃት እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ተከስቷል" ያለው ኢሰመጎ በዚህ ምክንያት የመንግስት የፀጥታ አካላትን እና የታጠቁ ቡድኖችን ለሚደርሱ ጉዳቶች ተጠያቂ አድርጓል።

በግጭቱ ድሮንን ጨምሮ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ባላቸው ከባድ የጦር መሳሪያዎች በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች ማለትም ሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶች ፣ ትምህርት ቤቶች እና የእምነት ተቋማት ኢላማ ሆነዋልም ብሏል። አሳሳቢዉ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታ

የኢሰመጉ ዋና ዳይሬተር ዳን ይርጋ እንዳሉት በክልሉ የደረሱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ምርመራ ለማከናወን ከመደባቸው ሠራተኞቹ አንዱ በፀጥታ አካላት ጥቃት ደርሶበታል። 
ይህንን የምርመራ ስራ ካጠናቀቀ በኋላ ህዳር 05 ቀን 2016 ዓ.ም በታጠቁ ሰዎች ከባድ ድብደባ  ተፍጽሞበታል ፣ የሠራተኛ መታወቂያዎችን ጨምሮ ሌሎች ከስራውና ከምርመራ ስራው ጋር ግነኙነት ያላቸውን ንብረቶች ተወስደውበታል ብሏል።
ሕገ ወጥ እሥር ፣ ድብደባ፣ የቢሮ ሰበራ እና ንብረት ዘረፋ፣ ብርበራ፣ ሕገ ወጥ ክትትል፣ ዛቻ እና ማስፈራራትን ጨምሮ ሌሎች ጫናዎች በተደጋጋሚ እየደረሰበት መሆኑንም በኢሰመጉ አስታውቋል። 
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል ድሮንን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች በተሰነዘሩ ጥቃቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት ስለመድረሱ በኢሰመኮ የሕግና ፖሊሲ ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ታሪኳ ጌታቸው ከዚህ በፊት ለዶቼ ቬለ ገልፀው ነበር።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባላወጣው መግለጫ ላይ ያለውን አቋም ለመጠየቅ ሞክረናል። ይሁንና ለጊዜው ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ኢሰመኮ ከዚህ በፊት ያወጣውን መግለጫ ግን  "አስተማማኝ መረጃ ላይ ያልተመሰረትና ሚዛናዊት የሚጎድለው" በማለት አጣጥለውታል ፣ ኮሚሽኑ ተገቢ እርምት እንዲወስድም አሳስበው ነበር።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች
የኢሰመጉ ዋና ዳይሬተር ዳን ይርጋ እንዳሉት በክልሉ የደረሱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ምርመራ ለማከናወን ከመደባቸው ሠራተኞቹ አንዱ በፀጥታ አካላት ጥቃት ደርሶበታል። ይህንን የምርመራ ስራ ካጠናቀቀ በኋላ ህዳር 05 ቀን 2016 ዓ.ም በታጠቁ ሰዎች ከባድ ድብደባ  ተፍጽሞበታል ፣ የሠራተኛ መታወቂያዎችን ጨምሮ ሌሎች ከስራውና ከምርመራ ስራው ጋር ግነኙነት ያላቸውን ንብረቶች ተወስደውበታል ብሏል።ምስል AP/picture alliance

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር