የደቡብ አፍሪቃው መጤ ጠል እንቅስቃሴ ኢትዮጵያውያንን አስግቷል
ዓርብ፣ ሚያዝያ 23 2018
በደቡብ አፍሪካ ባለፈው ማክሰኞ አራት ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎች ከተገደሉ በኋላ የመጤ ጠል አራማጆች እንቅስቃሴ እየበረታ መጥቷል ፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች በሚገኙ ጎዳናዎች ላይ ወጣቶች ሽመሎችን በመያዝ ፀረ ስደተኛ ሥልፎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል ፡፡ እንደቲክቶክ በመሳሰሉ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ኢትዮጵዊያንን ጨምሮ በርካታ ጥቁር አፍሪካዊያን ሲደበደቡ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እየወጡ ይገኛሉ ፡፡
በሥጋት ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን
በደቡብ አፍሪካ እየተባባሰ በመጣው የመጤ ጠል ጥቃት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኛ ተናግረዋል ፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ እንዳሉት የመጤ ጠል አራማጆች በሚያደርሱት ዛቻ የተነሳ አሁን ላይ የሥራ ቦታቸውን ዘግተው ከቤት ለመዋል ተገደዋል ፡፡
ነዋሪነታቸውን በጆሃንሰበርግ ያደረጉት አቶ ገዛኻኝ ሱማሞ ትውልድ ለትውልድ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራች እና የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ፎረም አባል ናቸው ፡፡ አሁን ላይ የመጤ ጠል አራማጆች በሚያደርሱት ዛቻ ከፍተኛ ሥጋት ላይ መውደቃቸውን ነው አቶ ገዛኻኝ ለዶቼ ቬለ የገለጹት ፡፡
ሰዎች በተለያዩ ከተሞች ላይ ዘግተው መቀመጣቸውን የጠቀሰው አቶ ገዛኻኝ “ ሥጋቱ የከፋ ነው ፡፡ በተለይ ቆንጨራ የያዙ ወጣቶች የሚያሳዩት ዛቻ ሥነ-ልቦናን እየጎዳ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ በደቡብ አፍሪካ ለበርካታ ዓመታት ከማህበረሰቡ ጋር ተግባብቼ እየኖርኩ ነው ብዬ ነበር የማስበው ፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም ፡፡ ከነዋሪው የሚወጡ ቃላቶች ስደተኛውን የሚጎዱ ናቸው “ ብለዋል ፡፡
የፖለቲከኞች እና የአንቂዎች ተፅእኖ
በፕሪቶሪያ ከተማ በአንድ የጋራ ህንጻ ላይ እሱን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያንተሰባስበው እየኖሩ እንደሚገኙ የጠቀሰው አንድ ሌላ ኢትዮጵያዊ በበኩሉ ከጥቃት አድራሾቹ ለኢትዮጵዊያኑ የዛቻ መልዕክት እንደደረሳቸው ተናግረዋል ፡፡ አብዛኞቹ ጥቃቶችና ዛቻዎች ከጀርባ በአንዳንድ ፖለቲከኞች እና ተፅኖ ፈጣሪ ሰዎች የሚደገፉ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪው ጠቁሟል ፡፡
አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲ ፖለቲከኞች የወጣቱን ትኩረት ለመሳብ ፀረ ፍልሰተኛ ንግግር እንደሚያደርጉ የተናገረው ይሄው አስተያየት ሰጪ “ ይህም ጥቃቶች እንዲባባሱ ምክንያት እየሆነ ይገኛል ፡፡ በተለይ የአገሪቱ ፖሊሶች ሰዎች ሲደበደቡ ቆመው ከመመልከት ውጭ ለማስጣል እና ሥርዓት ለማሲያዝ ሙከራ እንኳን ሲያደርጉ አይታይም “ ብለዋል ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ በጥቃቶቹ ዙሪያ
በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያዊያን ላይ እየተፈጸመ በሚገኘው ጥቃት ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት አሥፈላጊውን የዲፕሎማሲ ጥረቶችን እንዲያደርግ ፍልሰተኛ ኢትዮጵያዊያን ሲጠይቁ ቆይተዋል ፡፡ ትናንት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው መንግሥታቸው ፍልሰተኞችን ከጥቃት ለመጠበቅ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል ፡፡
በተለይ ፕሪቶሪያ በሚገኘው ኢምባሲ በኩልለዜጎች መረጃዎችን እያቀረበ መቆየቱን የጠቀሱት አምባሳደር ነብያት “ የደቡብ አፍሪካ መንግሥትም አስፈላጊውን ከለላ እንዲያደርግ በኢምባሲ በኩል ጥያቄዎች ቀርበዋል ፡፡ ለችግሩ እልባት እንደሚሰጥና ጥፋተኞችንም ተጠያቂ እንደሚያደርግ ሙሉ እምነት አለን ፡፡ በእኛ በኩል ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን ከጥቃት እንዲጠብቁ ድጋፍ እናደርጋለን “ ብለዋል ፡፡
መንግሥታዊ ካልሆነውና ከደቡብ አፍሪካ የማህበረሰብ ጥምረት ከተባለ ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑወቅት ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ እየኖሩ ይገኛሉ ፡፡ኢትዮጵያዊያኑ በየጊዜው በሚደርስባቸው ጥቃቶች ለሞት መዳረጋቸው ዶቼ ቬለ በተከታታይ ሲዘግብ መቆየቱም ይታወቃል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ