ኤርትራ በአስቸኳይ ሰራዊቷን ከሉአላዊ ግዛቶቿ እንድታስወጣ ኢትዮጵያ አሳሰበች።
ኤርትራን «ግልጽ ጥሰት በመፈጸም» በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ከሚንቀሳቀሱ አማጽያን ጋር አብራለች ስትል ኢትዮጵያ ከሳለች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጤሞትዮስ ትናንት ቅዳሜ ለኤርትራው አቻቸው በላኩት ግልጽ ደብዳቤ “ባለፉት ጥቂት ቀናት የታዩት ክስተቶች የኤርትራ መንግሥት ተጨማሪ ግጭት የማባባስ መንገድ መምረጡን ያሳያሉ” ብለዋል። ጌድዮን በመልዕክታቸው አሥመራ “ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ግዛት እንድታስወጣና ከአማጽያን ጋር የምታደርገውን ማንኛውንም ዓይነት ትብብር እንድታቆም” ጠይቀዋል።
ድርጊቶቹ “ተራ ትንኮሳዎች ሳይሆኑ የቀጥታ ወረራ ተግባራት ናቸው” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን “የጥልና ያለመተማመን አዙሪቱን” በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መግታት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ደብዳቤው ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነም ኢትዮጵያ "የባሕር አገልግሎት ጉዳዮችን እና በአሰብ ወደብ በኩል የባሕር መዳረሻን ጉዳይ ጨምሮ ሁሉንም የጋራ ጥቅም ጉዳዮችን ለመፍታት በቅን ልቦና በድርድር ለመሳተፍ ፈቃደኛ" መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌድዮን ለጻፉት ደብዳቤ የኤርትራ መንግሥት ወዲያው መልስ አለመስጠቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
ሁለቱ ሃገራት ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም በነበረው የትግራይ ጦርነት አንድ ላይ አብረው በትግራይ ኃይሎች ላይ ቢዘምቱም ኤርትራ ያልተሳተፈችበት የሰላም ስምምነት በፕሪቶሪያ ከተፈረመ በኋላ ግንኙነታቸው ተበላሽቶ ቆይቷል።
በሰሜናዊ ናይጄሪያ ካዱና ግዛት ታጣቂዎች በአንድ የኃይማኖት አባት መኖሪያ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ሦስት ሰዎች ተገደሉ።
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ አንድ የካቶሊክ ቄስን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን አግተው መውሰዳቸውን የቤተክርስቲያንና የፖሊስ ምንጮች ገልጸዋል። ዛሬ የተሰማው የአማጽያኑ ጥቃት የተፈጸመው የጸጥታ ኃይሎች በሌሎች ሁለት የካዱና አብያተ ክርስቲያናት ላይ በታጣቂዎች ተጠልፈው የነበሩትን 166 ምዕመናን ማስለቀቃቸው ከተነገረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
መሰል ጥቃቶች የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ትኩረት የሳቡ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ የናይጄሪያ መንግስት ክርስቲያኖችን መጠበቅ ተስኖታል ሲሉ ይከሳሉ። ምንም እንኳ አቡጃ ክሱን ብታስተባብልም።
የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ "የሽብርተኞች ኢላማዎች" ባሏቸው ቦታዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸማቸው ይታወሳል።
በሰሜናዊ ናይጄሪያ ለዓመታት በተደጋጋሚ ለሚደርሱ ጥቃቶች እና የሰላማዊ ሰዎች ዕገታ ቦኮ ሃራም የተሰኘው ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ኃላፊነት ሲወስድ ቆይቷል።
ደቡብ አፍሪቃ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን እንደምታስወጣ የፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጽህፈት ቤት ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
ራማፎሳ ለተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ እንደተናገሩት፣ ከዚህ ውሳኔ ላይ ደቡብ አፍሪቃ የደረሰችው የራሷን የጦር ኃይሎች "እንደገና ማደራጀት" አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው።
"ደቡብ አፍሪካ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመተባበር የጎርጎሪዮሱ 2026 ከመጠናቀቁ በፊት ወታደሮቿን የማስወጣት ስልቶችን ለማጠናቀቅ ትሰራለች" ሲል መግለጫው አክሏል።
ደቡብ አፍሪቃ በኮንጎ ለ27 ዓመታት የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልኮዋን ስትወጣ የቆየች ሲሆን ከ700 በላይ የሰላም አስከባሪ ወታደሮችም በኮንጎ ተሰማርተው ይገኛሉ።
የተባበሩት መንግስታት የኮንጎ ተልዕኮ በአጠቃላይ ወደ 11,000 የሚጠጉ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች እና ፖሊሶች እንዳሉት የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ኤኤፍፒ ዘግቧል ።
አሜሪካ በትውልድ ሃገራቸው መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ በማሴር የጦር መሣሪያ ሲያዘዋውሩ ደርሼባቸዋለሁ ያለችውን ደቡብ ሱዳናዊ በእስራት ቀጣች።
ነዋሪነታቸውን አሜሪካ ያደረጉት ደቡብ ሱዳናዊው ፒተር ቢያር የጦር ሰራዊት ደረጃ የተሰጣቸውን የጦር መሣሪያዎች ወደ ደቡብ ሱዳን ለማጓጓዝ በመሞከር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሁለት ዓመት በፊት መጋቢት 2016 ዓ/ም ነበር። ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ሊያስገድሉኝ ሞክረዋል በሚል ከ2012 ዓ/ም አንስቶ በአሜሪካ በጥገኝነት መኖር እንደጀመሩ የተነገረላቸው ፒተር ቢያር የታዋቂው የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ለዓለም ባንክ የሚያገለግሉ የኤኮኖሚ ባለሞያ ናቸው።
በአሪዞና ግዛት የተሰየመው የፌዴራል ችሎት ፐተር ቢያር ግብረ አበራቸው ነበሩ ከተባሉ ትውልደ ደቡብ ሱዳናዊ አሜሪካዊ አብረሃም ቾል ኬች ጋር የጦር መሣሪያዎችን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ወደ ውጭ መላክን የሚቆጣጠሩ ህጎችን በመጣስ ጥፋተኛ ብሏቸዋል። የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ ባለፈው ዐርብ ባወጣው መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ ጥፈተኛ በተባሉበት ክስ እያንዳንዳቸው የአራት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።
ከየካቲት 2015 እስከ የካቲት 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ሁለቱ ግለሰቦች 4 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ "ወታደራዊ ደረጃ ያላቸው የጦር መሣሪያዎችን" አከማችተው መገኘታቸውን መግለጫው አመልክቷል።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት መሣሪያ አቅራቢዎች መስለዋቸው ከአሜሪካ የፌዴራል ስውር ወኪሎች ጋር ለአንድ ዓመት ያህል ድርድር ሲያካሂዱ ከቆዩ በኋላ ነው።
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረሱ ስምምነቶች ዋጋ አይኖራቸውም ሲሉ አንድ የእስራኤል ሚንስትር ተናገሩ ።
የእስራኤል የኢነርጂ ሚንስትር ኤሊ ኮሄን እንዳሉት አሁን ከስምምነት ይልቅ ወታደራዊ ግጭት ሊፈጠር የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ነው።
በድረ ገጽ ዜና የሚያሰራጨው የእስራኤሉ የመገናኛ አውታር 'ynet' ዛሬ ባወጣው ዘገባው ሚኒስትሩ "አሁን ካለው አገዛዝ ጋር የሚደረግ ስምምነት ምንም ዋጋ የለውም" ማለታቸውን ዘግቧል። "በቴህራን የአገዛዝ ለውጥ መምጣቱ በኢራን ዙሪያ ላሉ ሙስሊም አገራት ሁሉ ጥቅም አለው" ማለታቸውንም አክሏል።
አሜሪካ እና ኢራን ባለፈው አርብ በኦማን መዲና ሙስካት ቀጥታ ያልሆነ ንግግር መጀመራቸው ተዘግቧል። ሃገራቱ በንግግራቸው በጎ እምርታ መታየቱን ከመግለጻቸው ያለፈ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ንግግሩ መቼ ቀጥሎ እንደሚካሄድም የተባለ ነገር የለም። እንደዚያም ሆኖ የእስራኤል የኢነርጂ ሚንስትር እንደሚሉት በሃገራቱ መካከል "ስምምነት ቢኖር እንኳ በእስራኤል ላይ ስጋት ከተደቀነ እርምጃ እንወስዳለን" ማለታቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዲፒኤ ዘግቧል።
የኢነርጂ ሚንስትሩ ኮሄን አባል የሆኑበት የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ላይ እንደሚሰበሰብ ተገልጿል።