1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካቲት 11 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 11 2016

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑልና አርሰናል ተፋጠዋል ። ማንቸስተር ሲቲተስተካካይ ጨዋታውን ድል አድርጎ ሊቨርፑልን መጣሁልህ ሊለው ጓግቷል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ የባዬር ሙይንሽን ሽንፈት ደጋፊዎቹን አስደንግጧል ። የሻምፒዮንስ ሊግ፤ የአውሮጳ ሊግና ኮንፈረስ ሊግ ግጥሚያዎች በቀጣይ ቀናት ይከናወናሉ ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ተቀዳጅተዋል ።

https://p.dw.com/p/4caIO
Borussia Dortmund - AC Mailand
ምስል Vitalii Kliuiev/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ሊቨርፑል እና አርሰናል ተፋጠዋል ። ማንቸስተር ሲቲም ተስተካካይ ጨዋታውን ድል አድርጎ ከሊቨርፑል እግር በእግር ለመከተል ጓግቷል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ የባዬር ሙይንሽን ሽንፈት ደጋፊዎቹን አስደንግጧል ። የሻምፒዮንስሊግ፤ የአውሮጳ ሊግ እና ኮንፈረስ ሊግ ግጥሚያዎች በቀጣይ ቀናት ይከናወናሉ ። በአትሌቲክሱ ዘርፍ ኢትዮጵያውያን በዓለም መድረክ እንደተለመደው ድል ተቀዳጅተዋል

አትሌቲክስ

ስፔን ሴቪያ ውስጥ ትናንት በተከናወነ የማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ አሸናፊ ሆነዋል ። በወንዶች ምድብ በተደረገው ውድድር ዴሬሳ ገለታ 2:03:27 በመሮጥ የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር አሸናፊ ሆኗል። በውድድሩ ፈረንሳያዊው ሞራድ አምዶኒ ሁለተኛ ሲወጣ፤ ትውልደ ኢትዮጵያ እስራኤላዊ ጋሻው አየለ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ።

በሴቶች ምድብ በተደረገው ውድድር አትሌት አዝመራ ገብሩ 2:22:13 በሆነ ሰዓት አሸንፋለች። በውድድሩ ኬንያውያኑ ጆሴፊን ቼፕኮች እና ማግዳሊኔ ማሳይ ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን አዝመራን ተከትለው ገብተዋል።

ለአራት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የአፍሪቃ የአገር አቋራጭ ውድድር በአፍሪቃ የአትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን (CAA) አዘጋጅነት  ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ የፊታችን እሁድ ቱኒዚያ ውስጥ ይካሄዳል ። ለዚህ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ልምምድ መጀመሩን ዐስታውቋል ። በዚህ ውድድር ከ20 ዓመት በታች በሴቶች 6ኪሜ እና በወንዶች 8ኪሜ፣ በአዋቂዎች 10ኪ.ሜትር ወንድና ሴት እንዲሁም ድብልቅ ሪሌ ይከናወናል ። ኢትዮጵያ ለዚህ ፉክክር 14 ሴቶች እና 14 ወንዶች በአጠቃላይ 28 አትሌቶችን እንደምታሳትፍ ተገልጧል ።

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ
የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ከፊል ገጽታ ። ላትሲዮ ሮም ከባሼርን ሙይንሽን ጋ ሲጋጠም ፤ ፎቶ ከማኅደርምስል Alberto Pizzoli/AFP/Getty Images

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ

በበርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቀው የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ነገ እና ከነገ በስትያ ይቀጥላል ። በነገው እለት የሆላንዱ ፒኤስቪ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድን ያስተናግዳል ። የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ጣሊያን ውስጥ በዝነኛው ሳን ሲሮ ስታዲየም ከኢንተር ሚላን ጋ ይፋለማል ።  ረቡዕ ዕለት ደግሞ፦ የፖርቹጋሉ ፖርቶ በሜዳው ኤስታዲዮ ዶ ድጋዎ የእንግሊዙ አርሰናልን ይገጥማል ። በተመሳሳይ ሰአት የጣሊያኑ ናፖሊ በቀድሞ ዝነኛ ተጨዋቹ በሰየመው ስታዲዮ ዲዬጎ አርማንዶ ማራዶና ስታዲየም የስፔኑ ኃያል ባርሴሎናን ይፋለማል ። 

የካራበባዎ ፍፃሜ፥ የሊቨርፑል ሥጋት የቸልሲ መልካም አጋጣሚ

ሊቨርፑል በካራባዎ ወይንም የእንግሊዝ ሊግ የፍፃሜ ግጥሚያ የፉታችን እሁድ ለዋንጫ ሲፋለም በርካታ ተጨዋቾቹ በጉዳት አይሰለፉም ። ያም ብቻ አይደለም ከፍፃሜ ተፋላሚው ቸልሲ በተለየ ለፕሬሚየር ሊጉም ቅዳሜ እለት መጫወት ግድ ይለዋል ። በአንፃሩ ቸልሲ በአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) ደንብ መሠረት በዚህ ሳምንት የነበረው የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ለሌላ ጊዜ ተላልፎለታል ። 

በርካታ ተጨዋቾቻቸው የተጎዱባቸው ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ
በርካታ ተጨዋቾቻቸው የተጎዱባቸው ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በካራባዎ የዋንጫ ግጥሚያ ይሳካላቸው ይሆን?ምስል Propaganda Photo/IMAGO

የጥር 20 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ ቸልሲ በፕሪሚየር ሊጉ የለንደኖቹ ቶትንሀም ሆትስፐሮችን የፊታችን ዐርብ ስታምፎርድ ብሪጅ ውስጥ ሊያስተናግድ ቀጠሮ ተይዞለት ነበር ። ሆኖም ማክሰኞ፥ ረቡዕ እንዲሁም ሐሙስ የአውሮጳ ሻንፒዮንስ ሊግ፤ የአውሮጳ ሊግ እና የአውሮጳ ኮንፈረነስ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች አሉ ። በስካይ ስፖርት ሊተላለፍ ቀጠሮ የተያዘለት የቸልሲ ግጥሚያ በነዚህ ጊዜያት ሊከናወን አይችልም ። በዚህ የተነሳም ቸልሲ ለካራባዎ የዋንጫ ፍልሚያ ከሊቨርፑል በተለየ መልኩ ሰፋ ያለ የመዘጋጃ ጊዜ አለው ።

ሊቨርፑል ለፕሬሚየር ሊጉ የፊታችን ቅዳሜ በሜዳው አንፊልድ ሉቶን ታወንን  ሊገጥም የተያዘለት ቀጠሮ ወደ ረቡዕ ተላልፎለት ነበር ። በእለቱ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ እግር ኳስ ግጥሚያ አለ ። በዚህ መሠረትም ቸልሲ ለካራባዎ ይእሁዱ የፍፃሜ ጨዋታ ሰፋ ያለ የመዘጋጃ ቀን በማግኘቱ ከሊቨርፑል አንፃር እጅግ ተጠቃሚ ነው ።

ሊቨርፑል ለካራባዎ ፍፃሜ በቂ የመዘጋጃ ጊዜ አለማግኘቱ ብቻ ሳይሆን፥ በርካታ ወሳኝ ተጨዋቾቹ መጎዳታቸውም ያሰጋዋል ። በእርግጥ ሊቨርፑል ቅዳሜ እለት በፕሬሚየር ሊጉ ግጥሚያ ብሬንትፎርድን በሰፋ 4 ለ1 ውጤት ማሸነፉ  የሊግ መሪነቱን እንዲጠብቅ አስችሎታል ። በዳርዊን ኑኔዝ፣ በአሌክሲስ ማክ አሊስተር፣ ሞሐመድ ሣላህ እና ኮዲ ጋክፖ በተቆጠሩት ግቦች የነበረው ደስታ ግን ተጨማሪ ሁለት ተጨዋቾቹ ለጉዳት ስለተዳረጉበት ደብዝዟል ። በእለቱ ኩርቲስ ጆንስ እና ዲዬጎ ጆታ በጉዳት ከሜዳ ለመውጣት ተገደዋል ። ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ  ኡራጋዊውን አጥቂ ዳርዊዝ ኑኔዝንም ስጋት ስለገባቸው ለመቀየር ተገደው ነበር ።

ሊቨርፑል በቅዳሜው ግጥሚያ የተጎዱበት ሁለቱ ወሳኝ ተጨዋቾቹ ቀደም ሲል የተጎዱት እነ ዶሚኒክ ሶቦስላይ፣ ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ፣ ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር እና ቲያጎ አልካንትራን ተቀላቅለዋል ። የሊቨርፑል በርካታ ተጨዋቾች መጎዳት እና ለፕሬሚየር ሊጉ ቅዳሜ የሚኖራቸው ግጥሚያ ለቸልሲ እጅግ መልካም አጋጣሚ ሆኖለታል ። በሳምንቱ ከልምምድ ውጪ አንድም ጨዋታ የሌለው ቸልሲ ዌምብሌይ ውስጥ ለሚኖረው የካራባዎ የፍፃሜ ፍልሚያ ለሊቨርፑል ስጋት ይሆን? ወይንስ ሊቨርፑል ዐሥራ አንድ ምርጦቹን በቀጥታ ወደ ሜዳ በማስገባት ጨዋታውን ጀምሮ በፍፃሜው የቸልሲን መልካም አጋጣሚ ያበላሽ ይሆን? ሁሉንም እሁድ በፍፃሜው የምንመለከተው ይሆናል ።

ለንደን ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቶትንሀም ሆትስፐር ስታዲየም
የቶትንሀም ሆትስፐር ስታዲየምምስል Adam Davy/empics/picture alliance

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ሊቨርፑል 57 ነጥብ ሰብስቦ በመሪነቱ እንደገሰገሰ ነው ። በነገው ዕለት ማንቸስተር ሲቲ ወሳኝ ጨዋታውን ከብሬንትፎርድ ጋ ያደርጋል ። ቅዳሜ ዕለት በቸልሲ ከመሸነፍ ለጥቂት ነው የተረፈው ። ማንቸስተር ሲቲ በእግርጥ በጨዋታ ብልጫ ቢያሳይም እስከ 83ኛው ደቂቃ ድረስ በቸልሲ 1 ለ0 እየተመራ ነበር ። የማታ ማታ ግን በሮድሪ ግብ አቻ መውጣት ችሏል ። ለቸልሲ ራሒም ስተርሊንግ ተከላካዮችን አተረማምሶ 42ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል በሁለት ነጥብ ይበለጣል ።

የጥር 13 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ የባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአጠቃላይ አንድም ጊዜ ያልተሸነፈው አርሰናል ቅዳሜ ዕለት በርንሌይን ተርፍ ሙር ስታዲየም ውስጥ 5 ለ0 ቀጥቶ ተመልሷል ። አርሰናል አንደኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሊቨርፑል በሁለት ነጥብ ርቀት ይከተላል ። አስቶን ቪላ 49 ነጥብ ሰብስቦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ቶትንሀም ሆትስፐር በ47 ነጥብ የአውሮጳ ሊግ 5ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ትናንት ሉቶን ታወንን በሜዳው 2 ለ1 ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ 44 ነጥብ ይዞ በ6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።  በትናንትናው እለት ብራይተን ሼፊልድ ዩናይትድን በሜዳው 5 ለ0 በመቅጣት በግብ ተንበሽብሿል ።

ቮልፍስቡርግ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋ ሲጋጠም
በጀርመን ቡንደስሊጋ ቮልፍስቡርግ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋ ሲጋጠምምስል Darius Simka/regios24/IMAGO

ቡንደስ ሊጋ

በቡንደስሊጋው ትናንት ፍራይቡርግ እና አይንትራኅት ፍራንክፉርት 3 እኩል ተለያይተዋል።  ቦሁም ምንም እንኳን በጨዋታ ይዞታ በባዬር ሙይንሽን 70 በመቶ ቢበለጥም 3 ለ2 ድል አድርጎ ደጋፊዎቹን አስደንግጧል ። ባዬርን ሙይንሽን 87ኛው ደቂቃ ላይ በሔሪ ኬን ሁለተኛውን ግብ ባያስቆጥር ኖሮ ሽንፈቱ በ3 ለ1 ይጠናቀቅም ነበር ። ጃማል ሙሳይላ 14ኛው ደቂቃ ላይ ለባዬርን ሙይንሽን አስቆጥሯል ።  በዚሁ ጨዋታ የባዬር ሙይንሽኑ ዳዮት ኡፓሜካኖ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።  ቦሁም፦ በታኩማ አሳኖ፤፣ ኬቪን ሽሎቴርቤክ እና 78ኛው ደቂቃ ላይ በፍጹም ቅጣት ምት በኬቪን ሽቶይገር ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ባዬርን ሙይንሽንን ኩም አድርጓል ።

ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች፦ ላይፕትሲሽ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ0 ድል አድርጓል ። ዳርምሽታድት አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ በተሰናበተበት ሽቱትጋርት የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ሆፈንሀይም ዑኒዮን ቤርሊንን፤ አውግስቡርግ ማይንትስን 1 ለ0 ድል አድርገዋል ። ሆፈንሀይም እና ዑኒዮን ቤርሊን አንድ አንድ ተጨዋቾቻቸውን ለቀይ ካርድ ገብረዋል።    ሐይደንሃይም በባዬር ሌቨርኩሰን የ2 ለ1 ሽንፈት ሲገጥመው፤ ቮልፍስቡርግ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋ አንድ እኩል ተለያይቷል ። ኮሎኝ በሜዳው በቬርደር ብሬመን የ1ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል ።

ባዬር ሌቨርኩሰን በደረጃ ሠንጠረዡ ከባዬርን ሙይንሽን በ8 ነጥብ ርቆ በ 58 ነጥቡ አንደኛ ደረጃ ላይ ተኮፍሷል ።  ሽቱትጋርት በ46 ይከተላል።  41 ነጥብ ያለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ላይፕትሲሽ በ40 እንዲሁም አይንኅራኅት ፍራንክፉርት በ33 ነጥብ የአውሮጳ ሊግ እና የአውሮጳ ኮንፈረንስ ደረጃን ይዘዋል ።

የሻምፒዮንስሊግ፤ የአውሮጳ ሊግ እና ኮንፈረስ ሊግ ግጥሚያዎች በቀጣይ ቀናት ይከናወናሉ
የሻምፒዮንስሊግ፤ የአውሮጳ ሊግ እና ኮንፈረስ ሊግ ግጥሚያዎች በቀጣይ ቀናት ይከናወናሉ ምስል Salvatore Di Nolfi/KEYSTONE/dpa/picture alliance

የአውሮጳ ሊግ

የጥር 6 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ ለአውሮጳ ሊግ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ስምንት የመልስ ግጥሚያዎች የፊታችን ሐሙስ ይከናወናሉ ። በዚህም መሠረት፦ ፍራይቡርግ ከሌን፤ ሬኔ ከሚላን እንዲሁም ቱሉስ ከቤኔፊካ፣ ቃራባግ ከብራጋ ጋር ይገጥማሉ ። ስፓርታ ፕራኅ ከጋላታሳራይ፤ ስፖርቲንግ ከያንግ ቦይስ እንዲሁም ማርሴይ ከሻካታር ዶኒዬትስክ እና ሮማ ከፌዬኖርድ ጋር ይፋለማሉ ። 

የአውሮጳ ኮንፈረንስ ሊግ

ለአውሮጳ ኮንፈረንስ ሊግም ሐሙስ እለት ስምንት ጨዋታዎች ይኖራሉ ። በዚህ ውድድር ከሚሳተፉ ቡድኖች መካከል የጀርመኑ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከቤልጂጉ ዑኒዮን ሶን-ጊሎ ጋ የሚያደርገው ግጥሚያ  በምሽቱ የመጨረሻው ጨዋታ ነው ። ሁለቱ ቡድኖች ቀደም ሲል ሁለት እኩል ተለያይተዋል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ኂሩት መለሠ