የርገን ክሎፕ ሊቨርፑል እንደሚለቅ አስታወቀ
ዓርብ፣ ጥር 17 2016ጀርመናዊዉ የሊቨርፑል እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ በዉድድሩ ዘመን መጨረሻ ከሊቨርፑል ዋና አሰልጣኝነት እንደሚለቅ አስታወቀ። ሊቨርፑልን የእግር ኳስ ቡድንን ከጎርጎረሳዊዉ 2015 ጀምሮ በዋና አሰልጣኝ የተቀላቀለዉ የርገን ክሎፕ ቡድኑ የአውሮጳ ቻምፒየንስ ሊግ እና ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ ስድስት ጨዋታዎችን ለአሸናፊነት ያበቃ ነው። ዮርገን ከአሰልጣኝነት የምለቀዉ ስለደከመኝ ነዉ ብሏል።
« የዉድድሩ ዘመን ሲያበቃ ክለቡን እለቃለሁ። ይህ ዜና ለአብዛኛዉ ወዳጆቻችን አስደንጋጭ እንደሆነ አዉቃለሁ። ጉልበቴ እያለቀ ነው። ይህን ደግሞ አንድ ቀን በይፋ ወጥቼ መናገር እንዳለብኝ አዉቃለሁ። ስራውን ደጋግሜ መስራት እንደማልችል አውቃለሁ። በዚህ ቡድን ዉስጥ ሁሉን ነገር እወዳለሁ። ስራችንን ሁሉ እወዳለሁ ግን ስራዬን ደግሜ ማራዘምም ሆነ መቀጠል አልችልም። ለቡድኑ ከፍተኛ ፍቅር አለኝ። ለቡድኑ ማድረግ የምችለዉ ትንሽ ነገር እዉነት ብቻ ነዉ። እዉነቱ ደግሞ ይህ ነዉ። »
ክሎፕ በጎርጎሪያኑ 2022 ሚያዝያ ወር ኮንትራቱን እስከ ጎርጎሪያኑ 2026 ያራዘመ ቢሆንም የእንግሊዙ የእግርኳስ ቡድን የሊቨርፑል የስኬት ማዕበል በተወሰነ ደረጃ ማሽቆልቆሉ ተመልክተዋል። የቦርሲያ ዶርትመንድ የቀድሞ ዋና አሰልጣኝ በጎርጎሮሳዉያኑ ጥቅምት ወር 2015 ሊቨርፑልን ተቀላቅሎ በ2019 የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን እና በ2020 የእንግሊዝ ሻምፒዮንሺዮናን አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ሊቨርፑል በባለፈው የእንግሊዝ ኤፍ ኤካፕ የፍጻሜ ውድድር ቸልሲን ዌምብሌይ ስታዲየም ውስጥ በፍጹም ቅጣት ምት መለያ የጠበበ ልዩነት አሸንፎ ዋንጫ ለመውሰድ ብዙ ታግሏል ። በፕሬሚየር ሊጉም መሪ ቢሆን እንደ ቀድሞው የውድድር ዘመን ግን ብዙም የነጥብ ልዩነት አላሳየም። እናም አንዳንድ ተንታኞች ክሎፕ ከሊቨርፑል መልቀቁ ተገቢ ወቅት ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። ከምንም በላይ ግን ሊቨርፑል ከፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫ ለሦስት አሥርተ ዓመታት የራቀውን ዋንጫ በእጁ እንዲያስገባ በማስቻሉ ምንጊዜም በሊቨርፑል ታሪክ ስሙ ጎልቶ የሚነሳ ያደርገዋል።
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ